ቪላ ከ ዩናይትድ፤ ዌስት ሃም ከ አርሰናል የ24ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ግምቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በ24ኛው ሳምንት ማንቸስተር ዩናይትድ እና አርሰናል ከሜዳቸው ውጪ ተጉዘው አስተን ቪላ እና ዌስት ሃምን ይገጥማሉ።
የሊጉ መሪ ሊቨርፑል በአንፊልድ በርንሊን ያስተናግዳል። ሲቲ ደግሞ ከኤቨርተን በኢትሃድ ይጫወታል።
የቢቢሲ እግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን የዚህን ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ ውጤቶችን እንደሚከተለው ገምቷል።

ማን ሲቲ ከ ኤቨርተን
የኤቨርተን የአጨዋወት ስልት ምን ሊሆን እንደሚችል እናውቃለን። እየተከላከሉ ቆይተው በመልሶ ማጥቃት ጎል ማስቆጠር እንዲሁም ከቆመ ኳስ ዕድላቸውን መሞከረ ነው።
እኔ ግን ግምቴ ሲቲ ምንም ግብ ሳይቆጠርበት በሰፊ የግብ ልዩነት ይህን ጨዋታ እንደሚያሸንፍ ነው።
ግምት፡ ሲቲ 3 - 0 ኤቨርተን
ፉልሃም ከ ቦርንመዝ
ፉልሃም ባለፈው ሳምንት የሁለት ግብ መሪነቱን አሳልፎ ሰጥቶ ከበርንሊ አቻ ተለያይቷል። ቦርንመዝም እንዲሁ ከፎረስት ጋር አቻ ከመለያየት ውጪ አማራጭ አጥተው ታይተዋል።
ምንም እንኳ ፉልሃም ዓመቱን ሙሉ ደካማ ሆኖ ቢቆይም በሜዳው የተሻለ ሆኖ ተመልክቻለሁ።
ቦርንመዝ ባለፉት ሳምንታት ድንቅ ሆኖ መቆየቱን ባውቅም ይህን ጨዋታ ፉልሃም ሊያሸንፍ እንደሚችል እገምታለሁ።
ግምት፡ ፉልሃም 2 - 1 ቦርንመዝ

ሊቨርፑል ከ በርንሊ
ባለፈው ሳምንት ሊቨርፑል በኤምሬትስ ባሳዩት አቋም በጣም ተገርሚያለሁ። ከአርሰናል በፊት ከቼልሲ በነበራቸው ጨዋታ ድንቅ ሆነው ቆይተዋል።
የቀያዮቹ አማካይ ዶሚኒክ ሶቦዝላ ለአንድ ወር በጉዳት ከጨዋታ ውጪ ሆኗል። ይህ ለየርገን ክሎፕ ቡድን ከባድ ቢሆንም በርንሊ ግን ይህን ጨዋታ የማሸነፍ ዕድል አለው ማለት አይደለም።
ከምንም በላይ የሊጉ መሪዎች በጭራሽ ነጥብ መጣል የሌለባቸው ጨዋታ ነው።
ግምት፡ ሊቨርፑል 4 - 0 በርንሊ
ሉተን ከ ሼፊልድ ዩናይትድ
የሉተን አሠልጣኝ ሮብ ኤድዋርድስ በቡድኑ እየሠራ ያለውን በጣም አስደናቂ ነው። ይሁን እንጂ አሠልጣኙ ቡድናቸውን ከፕሪሚየር ሊጉ እንዳይወርድ ለማድረግ ገና ብዙ ፈተና ይጠብቃቸዋል።
ሼፊልድን በተመለከተ፤ በቪላ ወርደት የሆነ ሽንፈት የደረሰበት ቡድን እንዴት ሊያሸነፍ ይችላል ብዬ ልገምት? ለሼፊልድ ይህም ሌላ ሽንፈት ይሆናል ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ ሉተን 2 - 1 ሼፊልድ ዩናይትድ

ቶተነሃም ከ ብራይተን
ሶን ተመልሷል። ተሰልፎ ስለመጫወቱ እርግጥ ባይሆንም ቢያንስ ከቶተነሃም ቡድን ጋር አብሮ ልምምድ እያደረገ ነው። የሶን መመለስ ለሰሜን ለንደኑ ቡድን መልካም ዜና ነው።
ሪቻልሰን ጎል ማስቆጠሩን ቀጥሏል። ከጉዳት የተመለሰው ጄምስ ማዲሰን ወደ ቀደመ ብቃቱ እየተመለሰ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ቶተነሃም በሜዳው እንደመጫወት ይህን ጨዋታ ያሸንፋል ብዬ አስባለሁ።
የአቋም መዋዠቅ ውስጥ ያሉት የሮቤርት ዲ ዘርቢ ቡድን በዚህ ጨዋታ ግብ ሊስያቆጥር ይችላል።
ግምት፡ ቶተነሃም 3 - 2 ብራይተን
ዎልቭስ ከ ብሬንትፎርድ
ብሬንትፎርድ ካለፉት 9 የሊግ ጨዋታዎች በስምንቱ እንደመሸነፋቸው ከዚህ ጨዋታ አዎንታዊ ውጤት ማግኘት በጣም ይፈልጋሉ።
ነገር ግን ቼልሲን በአስደናቂ አቋም የረታውን ዎልቭስ ውጤት ሊያገኝ ይችላል ብዬ ልገምት? ዎልቭስ ጠንካራ ቡድን ከመሆኑም በላይ ፔድሮ ኔቶ በጣም አስፈሪ ተጫዋች ሆኗል።
ግምት፡ ዎልቭስ 2 - 1 ብሬንትፎርድ

ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ኒውካስል
ኒውካስል ጥሩ ወይስ መጥፎ ቡድን ነው የሚለውን መወሰን ከብዶኛል። ከሜዳቸው ውጪ አስተን ቪላን በድንቅ ብቃት አሸንፈው በሜዳቸው ከሉተን ነጥብ የተጋሩት ከኋላ ተነስተው ነበር።
የኤዲ ሃው ቡድን በተደጋጋሚ ብዙ ጎሎች እየተቆጠሩበት ነው። ክሪስ ዉድ በሴንት ጀምስ ፓርክ ኒው ካስል ላይ ሦስት ግቦችን ማስቆጠሩ የሚዘነጋ አይደለም።
ፎረስት እና ኒው ካስል አቻ የሚለያዩ ይመስለኛል።
ግምት፡ ፎረስ 2 - 2 ኒውካስል
ዌስት ሃም ከ አርሰናል
ይህ ጨዋታ አርሰናል ቁጭቱን የሚበቀልበት ሊሆን ይችላል። ኅዳር ላይ ዌስትሃም መድፈኖቹን በሜዳቸው በደጋፊዎቻቸው ፊት አሸንፈዋቸው ነበር።
በዌስት ሃም ሜዳ በሚደረገው ጨዋታም ባለሜዳዎቹ በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር የሚሞክሩ ይመስለኛል።
በዚህ ጨዋታ አርሰናል የተሻለ ዕድል ይፈጥራል ብዬ አስባለሁ። የአርሰናል ተጫዋቾች ወደ ዋንጫ ተፎካካሪነት ስለተመለሱ መሸነፍ አማራጭ ስላልሆነ በወኔ ተጫውተው የሚያሸንፉ ይመስለኛል።
ዌስት ሃም 0 - 2 አርሰናል

አስተን ቪላ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
ዩናይትድ ባለፈው ሳምንት ከዌስት ሃም ጋር የነበረውን ጨዋታ ተቆጣጥሮ ያሸነፈበት መንገድ የሚደነቅ ነበር።
አንዳንዶች ዩናይትድ ወደ ቀደመ አቋሙ እየተመለሰ ነው ይላሉ። እኔ ግን በቪላ የሚጠብቀው ፈተና ቀላል እንደማይሆን አስባለሁ።
ዩናትድ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝን በጉዳት ማጣቱ በተከላካይ መስመሩ ላይ ትልቅ ጫና ይፈጥራል። ዩናይትድ በዚህ ጨዋታ ጎል እንደሚያስቆጥር ባስብም ጨዋታውን ቪላ ያሸንፋል።
ግምት፡ ቪላ 2 - 1 ዩናይትድ
ክርስታል ፓላስ ከ ቼልሲ
ቼልሲ ከሊጉ አስቀያሚ ሽንፈት በኤፍ ኤ ካፕ ወደ ድል ተመልሷል። ቼልሲን የተመለከተ ግምት መስጠት ከባድ ነው ምክንያቱ ደግሞ አቋሙ በየሳምንቱ ስለሚቀያየር ነው።
ፓላስን በተመለከተ ኦሊሴ እና ኤዜ የሚያጋጥማቸው ተደጋጋሚ ጉዳት ለቡድኑ ትልቅ ኪሳራ ነው። እነዚህ ሁለቱ ተጫዋቾች ተሰልፈው አይጫወቱም በሚል ግምት ጨዋታውን ቼልሲ በጠባብ ውጤት ያሸንፋል ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ ፓላስ 0 - 1 ቼልሲ












