ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞው የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኤፕስቲን ጋር በተያያዘ ክስ ቀረበባቸው
የቀድሞው የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶርቢዮርን ጃግላንድ ከአሜሪካዊው የወሲብ ጥቃት ወንጀለኛ ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር በተያያዘ "ሙስና" ፈፅመዋል በሚል ክስ እንደቀረበባቸው ፖሊስ አስታወቀ።
የአውሮፓ ምክር ቤት የጃግላንድ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ካደረገ በኋላ ነው ክሱ የቀረበባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም ዓይነት ወንጀል እንዳልፈፀሙ እና ለትብብር ዝግጁ እንደሆኑ ጠበቃቸው ተናግረዋል።
የአሜሪካ መንግሥት የለቀቃቸው ከኤፕስቲን ጋር የተገናኙ ኢሜይሎች ጃግላንድ ብቻቸውን እና ከቤተሰባቸው ጋር ፓሪስ፣ ኒው ዮርክ እና ፓልም ቢች ወደሚገኙ የኤፕስቲን መኖሪያ ቤቶችን መጎብኘታቸውን ይጠቁማሉ።
ጃግላንድ ጉብኝቱን ባደረገ ወቅት ኤፕስቲን በሕፃናት ላይ በተፈፀሙ ወሲባዊ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብሎ ነበር።
ኦኮክሪም የተባለው የኖርዌይ የወንጀል መርማሪ ቡድን ሶስት የጃግላንድ መኖሪያ ቤቶችን መበርበሩን አስታውቆ ግላሰቡ ጣቢያ ቀርበው ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጡ ገልጿል።
ጃግላንድ በአውሮፓውያኑ ከ1996 እስከ 97 ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከማገልገላቸው በተጨማሪ የኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴ ኃላፊ ነበሩ። ለዓመታት የአውሮፓ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሆነው አገልግለዋል።
የአውሮፓ የዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት ተቆጣጣሪ የሆነው ምክር ቤት ፀሐፊ በመሆናቸው ያለመከሰስ መብት ተሰጥቷቸው ቆይተዋል።
ኦኮክሪም ግለሰቡ ከ2011 እስከ 2018 ባለው ጊዜ ሙስና ፈፅመዋል ብሎ በያዝነው ወር ምርመራ በመጀመሩ የሰውየው ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ጠይቋል።
የኤፕስቲን መዛግብት ሟቹ የፋይናንስ ባለሙያ ጃግላንድ ላደረጉት ጉብኝት ወጪ መሸፈኑን ያሳያሉ።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ከቤተሰባቸው ጋር ካሬቢያን ወደሚገኘው የኤፕስቲን ደሴት ለመሄድ አቅደው የነበረ ቢሆንም ኤፕስቲን በወቅቱ ሕመም አጋጥሞት ስለነበር ሰርዘውታል።
ኤንአርኬ የተባለው የኖርዌይ ጣቢያ እንደዘገበው ጃግላንድ የባንክ ብድር ለማግኘት ከኤፕስቲን እርዳታ እንደጠየቁ የኢሜይል ልውውጣቸው ቢያሳይም ብድር ያግኙ አያግኙ የሚታወቅ ነገር የለም።
ፖሊስ ይህ ጉዳይ ከሙስና ክሱ ጋር ስለመካተቱ ማረጋገጫ አልሰጠም።
የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስቴር በለቀቀው የኤፕስቲን መዛግብት ውስጥ ስማቸው የተካተተ ሰዎች ወንጀል ፈፅመዋል ማለት አይደለም።
ሚኒስቴሩ መዛግብቱን ይፋ ካደረገ በኋላ ፖለቲከኞች፣ ታዋቂ ሰዎች እና የንጉሣዊ አገዛዝ አባላት ስማቸው በመካተቱ ጉዳዩ ትልቅ መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጓል።
ባለፈው ወር የተለቀቁት መረጃዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኢሜይል ልውውጦች፣ ምስሎች እና የኤፍቢአይ ምርመራዎችን የያዙ ናቸው።
ኤፕስቲን ሕፃናትን ለወሲብ በማዘዋወር ክስ ቀርቦበት ችሎት ፊት ይቀርባል ተብሎ እየተጠበቀ ሳለ በአውሮፓውያኑ 2019 መሞቱ ይታወሳል።
የኖርዌይ ልዕልት አልጋ ወራሽ ሜቴ-ማሪት፣ ዲፕሎማቶቹ ሞና ጁል እና ቴርየ ሮድ-ላርሰን እና የዓለም ምጣኔ ሀብት ፎረም ዋን ሥር አስፈፃሚ ቦርጌ ብሬንዴ በኤፕስቲን መዛግብት ውስጥ ስማቸው ተነስቷል።