ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምንም ዓይነት ምልክቶች ሳያዩ እና ማርገዛቸውን ሳያውቁ ለወሊድ የሚደርሱ ሴቶች
ማርገዛቸውን ሳያዉቁ ከወራት በኋላ ወይም ምጥ ሲጀምራቸው ወይም ሊወልዱ ሳምንታት ሲቀራቸው የሚታወቅ እርግዝና እንዳለ ሰምተው ያውቁ ይሆን?
ሆዳቸው አያስታውቅም፤ የገፋ ነገር አይታይም። የእርግዝና ምልክቶችንም አያዩም።
“ሽልም ከሆነ ይገፋል፤ ቂጣም ከሆነ ይጠፋል” የተሰኘውን አባባል የሚያፈርስ ነው ይህ ሁኔታ።
ክሪፕቲክ ፕሬግናንሲ ወይም “ምሥጢራዊ እርግዝና” ይሰኛል።
የዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪዋ ታዋና በ21 ዓመቷ ልጅ የመውለድ ዕቅድ አልነበራትም።
መዝናናትን አጥብቃ የምትወደው ታዋና በራሷ አገላለጽ “ፓርቲ ብቻ ነው፤ የእብደት ኑሮ” የሕይወት ዘይቤዋን ትላለች።
ሆኖም አንድ ቀን ይህንን የቀየረ ነገር ተከሰተ። ራሷን ስታ መውደቋን ተከትሎ ሆስፒታል ተወሰደች።
ለምን እንደተዝለፈለችም ሆነ ራሷን እንደሳተች አታውቅም ነበር።
ሆኖም ዱብዕዳ የሚባል ዜና ሰማች። በሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች በአራት ሳምንት ውስጥ ልጇን እንደምትገላገል ተነገራት።
ድንጋጤ ብቻ አይደለም የተሰማት “መተንፈስም ከበደኝ” ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች።
ክስተቱን እውነት ነው ብሎ መቀበልም ነው ያዳጋተት።
ባላሳበችውም መንገድ በአራት ሳምንታት ውስጥ ሁኔታዎች እንደሚገለባበጡ ተረዳች።
መጀመሪያ ሆስፒታል በገባችበት ወቅት የኤምአርአይ ስካን ከማድረጓ በፊት የእርግዝና ምርመራ እንድታደርግ ተነግሯት ነበር።
በክንድዋ ላይ የሚቀበር የእርግዝና መከላከያ ስላላት እንዲሁም የእርግዝና ምልክቶች ባለመየቷ ምርመራውን አጣጥላው ነበር።
ከዚያም ምርመራውን ስታደርግ ውጤቷ ‘ነጌቲቭ’ በመሆኑ ነፍሰጡር እንዳልነበረች እርግጠኛ ነበረች።
ነገር ግን ታዋና ነፍሰ ጡር ልትሆን እንደምትችል አንዲት ነርስ ዶክተሩን የአልትራሳውንድ ምርመራ እንዲያደርግላት አሳመነችው።
በዚያም ነው ነፍሰ ጡር መሆኗ የታወቀው።
የልጇ አባት ኢማኑኤል ታዋና ልትወልድ መሆኑን ስትነግረው አላመናትም።
“ምንም ትርጉም የሚሰጥ ነገር አይደለም። ተዓምራዊ ነው የሚመስለው” ብሏል።
እንደ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ ያሉም ሆኑ የሚታይ የሆድ መተለቅ ሳይኖር የሚኖር እርግዝና ክሪፕቲክ ፕሬግናንሲ (ምሥጢራዊ እርግዝና) ይሰኛል።
ብዙም እንዳልተለመደ ዶክተሮች እንደነገሯት የምትናገረው ታዋና “በጥቁሮች ዘንድ ግን ከሁሉም ማኅበረሰቦች በተለየ መልኩ ያጋጥማል” መባሏንም ገልጻለች።
“እንደተነገረኝ ከሆነ በዳሌያችን እና አጥንት አወቃቀር ምክንያት ጽንሱ ወደፊት ሳይሆን ወደ ውስጥ እንደሚያድግ ነው፤ እንዲሁም የጽንሱም አቀማመጥ የተገለበጠ ይሆናል” መባሏንም ታስረዳለች።
መጸነሷ፣ ልትወልድ አራት ሳምንታት መቅረቱ እንዲሁም ጽንሷ ተገልብጦ ይሆናል የሚለው መረጃ ሁሉ ተደራርቦ ከበዳት። በተለይም ቀኑ ሲቃረብ ጽንሱ ተገልብጦ ይሆናል የሚለው ስጋቷ በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ።
ምሥጢራዊ የሚባለው የእርግዝና ዓይነት በምን ያህል ሴቶች ላይ እንደሚያጋጥም አሀዛዊ መረጃ ባይኖርም፤ በለንደን ሳውዝ ባንክ ዩኒቨርስቲ የጤና እንክብካቤ ፕሮፌሰር የሆኑት አሊሰን ሌቪ ከወሊድ እንክብካቤ ጋር በተያያዘ በጥቁሮች እና በሌሎች አናሳ ማኅበረሰቦች ላይ ልዩነት እንዳለ የሚያሳይ ነው ይላሉ።
“ሴቶች በተለይም ጥቁር ሴቶች በእርግዝና ወቅትም ሆነ በወሊድ ወቅት ጥሩ እንክብካቤ እንደማያጋጥማቸው የሚያሳዩ ብዙ ጥናቶች ተካሂደዋል” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በተለይም በጥቁር ሴቶች ላይ የሚከሰተው ይህ ምሥጢራዊ እርግዝናን በተመለከተ ምርምሮች እንዲካሄዱ አጽንኦት ይሰጣሉ።
ይህም ከእርግዝና እና ከወሊድ እንክብካቤ አገልግሎት ጋር መጠናከር እና ተደራሽነት ጋር እንደሚያያዝም ያስረዳሉ።
ባልጠበቀችው ሁኔታ ነፍሰ ጡር መሆኗን የተረዳችው ታዋና ከተነገራት አራት ሳምንት ከአራት ቀናት በኋላ ልጇን ተገላገለች። ልጇንም ሪቨር የሚል ስያሜ ሰጠቻት።
ሆኖም ከወለደች በኋላ ድኅረ ወሊድ ድብርት በሚባለው ህመም ትሰቃይ ጀመር። በዚህ በወጣትነት ዕድሜዋ ባልጠበቀችው ሁኔታ እናት መሆኗንም ለመላመድ ምክር ለመፈለግ ወደ ቲክቶክ ሰፈሮች ማማተር ጀመረች።
ሆኖም በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ እናት የሆነች ሴት ከአንድ አሜሪካዊት በስተቀር አላጋጠማትም።
“በጣም በከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ገባሁ። ምክር የሚለግሰኝም አካል አልነበረም” ትላለች።
“ማንም ስለዚህ ጉዳይ እያወራ አይደለም። አንዲት አሜሪካዊት ብቻ አንድ የሠራችው ቪዲዮ አለ፤ መቶ ዕይታዎች ብቻ ያገኘ። እሷ ብቻ ናት ምክር የሰጠችኝ” ትላለች።
ታዋናም ስለገጠማት አስገራሚ እርግዝና አንድ ቪዲዮ ለመሥራት ወሰነች። ቪዲዮው በከፍተኛ ሁኔታ የታየ ሲሆን 400 ሺህ ሰዎችም ወደውታል።
ይህንን ብቻ አይደለም ከሌሎች እናቶች ጋር በመጣመር ፖድካስት ጀመረች።
ታዋና ታሪኳን ያጋራችው በመጨረሻዋ ደቂቃ ነፍሰ ጡር መሆናቸውን ለሚረዱ ወጣት እናቶች ተስፋን ይሰጣል በሚል ነው።
ታዋና ከእናቷ የገንዘብ ድጋፍ በማግኘቷ ዕድለኛ ብትሆንም ሌሎች ግን እንደ እሷ ዕድለኛ ያልሆኑ እንዳሉ ትገነዘባለች።
የተቸገሩትን ለመርዳት የበጎ አድራጎት ድርጅት ለማቋቋም ሃሳብ አላት።
ክሪፕቲክ ፕሬግናንሲ (ምሥጢራዊ እርግዝና) ምንድን ነው?”
- አንዲት ሴት የእርግዝና ምልከቶችም በማታይበት እንዲሁም ነፍሰጡር መሆኗን የማታውቅበት ነው። አንዳንዶች በምጥ ወቅት እርጉዝ መሆኗን የተረዱ አሉ።
- ከ2500 ውልደቶች መካከል አንዱ በምሥጢራዊ እርግዝና የሚመጣ ነው።
- በዩናይትድ ኪንግደም 300 ውልደቶች በምሥጢራዊ እርግዝና የተረገዙ ናቸው።
- አንዳንዶቹ የእርግዝና ምልክቶች አለመታየት ሴቶች ከሚያሳልፏቸው የጭንቀት ወቅቶች ጋር የተያያዙ ናቸው።
- ወቅቱን ጠብቆ የማይመጣ የወር አበባ ወይም የተቆራረጠ የወር አበባ የሚያጋጥማቸው ሴቶች ሌሎች የእርግዝና ምልክቶችን ሊያዩ ይችላሉ።