በሁለት ክሶች ነጻ የተባሉት አቶ ታዬ፤ ጠ/ሚ ዐቢይ እና አምባሳደር ሬድዋን ችሎት ይቅረቡልኝ አሉ

ከቀረቡባቸው ሦስት የወንጀል ክሶች በሁለቱ ነጻ የተባሉት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ አቶ ታዬ ደንደአ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕምድ እና አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ችሎት ፊት እንዲቀርቡ አቤቱታ አቀረቡ።

የቀድሞ ሚኒስትር ዲኤታ እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል፤ ፀረ ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ እና ጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት በሚሉ ወንጀሎች ተከሰው ጉዳያቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲታይ መቆየቱ ይታወሳል።

ዐቃቤ ሕግ አቶ ታዬ ደንደኣ መገናኛ ብዙኃን እና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ሁከት የሚያስነሱ እና “ፀረ ሰላም የሆኑ የኦነግ-ሸኔ እና ፋኖ” ዓላማዎችን የሚያሳኩ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ ነበር በማለት ሁለት ክሶች ከፍቶባቸው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት በአቶ ታዬ ላይ ተከፍቶ የነበረ ሦስተኛው ክስ ነው።

አቶ ታዬ ግን በቀረቡባቸው ክሶች ጥፋተኛ አለመሆናቸውን እና ወንጀል አለመፈጸማቸውን ለችሎት ቃል ሰጥተው ነበር።

የቀደሞ የሰላም ሚኒስቴር ዲኤታው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያጋሯቸው ጽሑፎች የሰላም ጥሪ እንጂ ሁከት ቀስቃሽ አለመሆናቸውን እንዲሁም በመኖሪያ ቤታቸው የተገኘው ጦር መሳሪያ መንግሥት ለደኅንነታቸው ሲባል ያስታጠቃቸው መሆኑን በመናገር ከዚህ ቀደም ተከራክረዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግሥት እና የሽብር ወንጀል ችሎት በዛሬው ውሎው አቶ ታዬ በመገናኛ ብዙኃን እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያስተላለፏቸው መልዕክቶች ሁከት የሚያስነሱ መሆን አለመሆናቸውን፣ “የኦነግ ሸኔ እና የፋኖ” ዓላማን ለማሳካት ያለሙ መሆን አለመሆናቸውን እንዲሁም መልዕክቶቹ የሕዝብ ሞራል እና የግለሰቦች መብትን የሚጣረሱ መሆን አለመሆናቸውን መመርመሩን ገልጿል።

በዚህ መሠረት አመጽ መቀስቀስ እና ፀረ ሰላም ኃይሎችን መደገፍ በሚል የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው አቶ ታዬ ነጻ ተብለዋል።

ይሁን እንጂ ችሎቱ ከጦር መሳሪያ አያያዝ አዋጅ ጋር ተያይዞ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ውሳኔ አስተላልፏል።

'ጠ/ሚ ዐቢይ እና አምባሳደር ሬድዋን ይጠየቁ'

ከዚህ ቀደም በጠበቆቻቸው ላይ ማስፈራርት እየደረሰ በመሆኑ ብቻቸውን ችሎት ፊት ቀርበው የነበሩት አቶ ታዬ፤ በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎም ያለ ጠበቃ ነበር በችሎት የተገኙት።

በዛሬው ችሎት አቶ ታዬ፤ “በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ጠበቃ እንዳይቆምልኝ፤ የቆሙልኝ ጠበቆችም ጥለው እንዲሄዱ አድርጓል” ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ታዬ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ችሎት ፊት ቀርበው ይጠየቁ ሲሉ ጠይቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አቶ ታዬ፤ ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች መካከል በሁለቱ ነጻ መባላቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የዋስ መብታቸው እንዲጠብቅላቸው ጠይቀዋል።

ይሁን እንጂ የአቶ ታዬ አንዲከላከሉ የታዘዙበት ክስ እስከ 20 ዓመት የሚያስቀጣ ነው በማለት የዋስትና ጥያቄያቸውን ዐቃቤ ሕግ ተቃውሞ ተከራክሯል።

ፍርድ ቤቱም ከሰዓት በኋላ በነበረው ችሎት የዋስትና ጥያቄውን ሳይቀበለው የቀረ ሲሆን፣ ተከሳሸ አቶ ታዬ መከላከያን ለመመልከት ለቀጣይ ዓመት ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።