ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታሪክ ሠሪዋ ጽጌ ዱጉማ
አትሌት ጽጌ ዱጉማ በፓሪስ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው በማይሳተፉበት በ800 ሜትር ርቀት የብር ሜዳሊያ በማሸነፍ ታሪክ ሠራች።
አትሌቷ ያስመዘገበችው ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ በርቀቱ የመጀመሪያው የኦሎምፒክ ሜዳሊያ ሆኖ ተመዝግቧል።
ጽጌ ውድድሩን 1 ደቂቃ 57.15 ሰኮንድ በመግባት አጠናቃለች።
እንግሊዛዊቷ ኪሊ ሃድኪንሰን ውድድሩን በበላይነት በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያውን አሳክታለች።
ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው ኬንያዊቷ ሜሪ ሞራ ሦስተኛ ሆና ውድድሯን አጠናቃለች።
ሌላኛዋ አትሌት ወርቅነሽ መሰለ ስድስተኛ በመሆን አጠናቃለች።
ኢትዮጵያዊያን በማይታወቁበት የ800 ሜትር ማንጸባረቅ የጀመረችው ጽጌ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ታሪክ መሥራቷን ቀጥላለች።
በአፍሪካ ከ20 በታች ሻምፒዮን ላይ ሁለተኛ መውጣት የቻለችው ጽጌ በመላው አፍሪካ ጨዋታ ደግሞ አሸናፊ ለመሆን በቅታ ነበር።
በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና አሸናፊነቷ ማግስት ወደ ፓሪስ አቅንታም የብር ሜዳሊያ በማግኘት ታሪክ ለመሥራት በቅታለች።
ጽጌ ዱጉማ ማን ናት?
በቤኔሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሺ ዞን የተወለደችው ጽጌ በዞን እና በክልል ደረጃ በሚደረጉ ውድድሮች አሸናፊ መሆኗን ተከትሎ አሰላ የሚገኘውን ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ለመቀላቀል በቃች።
ቀጥሎም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብን ተቀላቀለች።
በ100 እና 200 ሜትሮች ትወዳደር የነበረችው ጽጌ አልጄሪያ ላይ በተደረገ የአፍሪካ ከ20 በታች ሻምፒዮን ላይ በ200 ሜትር ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ለማግኘት በቅታለች።
በአገር ውስጥ በተደረጉ የተለያዩ ውድድሮችም በዚህ ዘርፍ ደጋግማ አሸናፊ ለመሆን በቅታለች።
በኋላም በአውሮፓውያኑ 2019 ደግሞ በ400 ሜትር መወዳደር ጀመረች።
ከዓመት በፊት ደግሞ ፊቷን ወደ 800 ሜትር አዞረች።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ ተሳትፋ በ800 ሜትር ቀዳሚ በመሆን አጠናቀቀች
በተጠባባቂነት ወደ ግላስጎው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ውድድር ያቀናችው ጽጌ ውድድሩ ላይ ባለቀ ሰዓት እንድትሳተፍ ተደርጎ አሸናፊ በመሆን ወርቅ ሜዳሊያ ለማግኘት ችላለች።
የጽጌ ዱጉማ ዋና ዋና ስኬቶች
- እአአ 2017 በአፍሪካ ከ20 በታች ሻምፒዮን 200 ሜትር- የብር ሜዳሊያ
- እአአ 2019 በአፍሪካ ከ20 በታች ሻምፒዮን 400 ሜትር- ስድስተኛ
- እአአ 2022 በአፍሪካ ሻምፒዮና 400 ሜትር- ግማሽ ፍጻሜ
- እአአ 2024 አፍሪካ ጨዋታዎች 800 ሜትር- የወርቅ ሜዳሊያ
- እአአ 2024 የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና 800 ሜትር- የወርቅ ሜዳሊያ
- እአአ 2004 የፓሪስ ኦሎምፒክ 800 ሜትር- ብር ሜዳሊያ