ስለ አሜሪካ እና ዩክሬን የማዕድን ድርድር እስካሁን ምን እናውቃለን?

ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ እና ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር ስታደርግ የቆየችውን የማዕድን ድርድር ለመፈረም ዝግጁ መሆናቸውን የተናገሩት በነጩ ቤተመንግሥት በተገኙበት ወቅት ከዶናልድ ትራምፕ እና ምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ጋር የጋለ ክርክር ውስጥ በመግባታቸው እንዲወጡ ከተደረገ ከቀናት በኋላ ነው።

መጀመርያ ስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያኖራሉ ተብሎ የተጠበቀው ዜሌንስኪ ዋሽንግተንን በሚጎበኝበት ወቅት የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን በጋዜጠኞች ፊት የተካረረ ምልልስ እና ክርክር ካካሄዱ በኋላ እንዲዘገይ ተደርጓል።

ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን የሚሰጠው ወታደራዊ እርዳታ ለጊዜው እንዲቆም ካደረጉ በኋላ በሁለቱ መሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት ከቀናት በኋላ የመሻሻል ምልክት አሳይቷል።

ይህ የዶናልድ ትራምፕ እርምጃ ይፋ በሆነ በሰዓታት ውስጥ ዜለንስኪ አሜሪካ ለአገራቸው ላደረገችው ድጋፍ ያላቸውን አድናቆት የሚገልጽ ረዥም መልዕክት በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ለጥፈው ነበር።

በዚሁ ጽሑፋቸው ላይ አገራቸው የማዕድን ስምምነቱን በማንኛውም አመቺ በሆነ ጊዜ ለመፈረም ዝግጁ መሆኗን አሳውቀዋል።

ትራምፕ ለኮንግረስ ባደረጉት ንግግር ላይ የዜሌንስኪን መልዕክትን ቢያደንቁም፣ስምምነቱ መቼ እንደሚፈረም ግን ግልጽ አላደረጉም።

ስምምነቱ ምን ይዟል?

በርካታ የመረጃ ምንጮች ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደተናገሩት፣ የስምምነቱ ውል እስካሁን እንዳልተጠናቀቀ እና ዜሌንስኪ የአሜሪካ አቻቸውን እና ምክትላቸውን ከማግኘታቸው በፊት በዩክሬን ሚድያዎች ላይ ይፋ ከሆነው የስምምነት ረቂቅ ሊቀየር እንደሚችል ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ሾልኮ በወጣው የስምምነቱ ረቂቅ ላይ ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት "የኢንቨስትመንት ፈንድ" እንደሚቋቋም የተገለፀ ሲሆን፣ የዩክሬኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴኒስ ሽሚሃል በኪየቭ እና በዋሽንግተን "በአቻነት" እንደሚተዳደር ተናግረው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በረቂቁ መሠረት የዩክሬን መንግሥት ከሚያስተዳድራቸው የማዕድን ኃብቶች የገቢውን 50 በመቶ ወደ ፈንዱ የሚያዋጣ ሲሆን፣ ፈንዱም "ለዩክሬንን ደህንነት፣ መረጋጋት እና ብልጽግናን ለማስፋት" ይውላል ይላል።

የአሜሪካ መንግሥት ተጠያቂነቱም በራሱ አገር ሕግ መሰረት ሲሆን "በኢኮኖሚ የበለጸገች እና የተረጋጋች ዩክሬንን ለመፍጠር የረዥም ጊዜ የገንዘብ ድጋፉን ይቀጥላል" ይላል።

ስምምነቱ በተጨማሪ በአሜሪካ ሕግ መሰረት የሚፈቀደውን ከፍተኛ የገንዘብ መጠን በዩኤስ ባለቤትነት እጅ ይሆናል ይላል።

ስምምነቱ መፈረም ከነበረበት ቀን በፊት በትራምፕ እና በዜለንስኪ መካከል ያሉ አለመግባባቶች ስር እየሰደዱ ሄደው ሳይፈረም ቀርቷል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት በመጀመርያ ከአሜሪካ 500 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ያቀረቡትን ጥያቄ የተዉት ሲሆን፣ ይህ ፍላጎት ሾልኮ በወጣው የስምምነቱ ረቂቅ ላይም አልሰፈረም።

"የአሜሪካ አስተዳደር የዩክሬንን ሉዓላዊነት በሚፈታተን መልኩ ነው ስምምነቱን የጀመረው፤ በኋላም ቢሆን አገሪቱን የሚያከስር፣ በዝባዥ ስምምነቱን ገፍቶበታል " ሲሉ የቀድሞ ሚኒስትር እና የኪዬቭ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት ኃላፊ ቲሞፊ ሚሎቫኖቭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"አሁን ከጋራ ባለቤትነት ጋር ወደ ምክንያታዊ ስምምነት ተመልሰዋል። በተጨማሪም ከዚህ በፊት የተሰጠ ዕርዳታ ላይ ቀጥተኛ ጥያቄ የለም። ይህ በእውነቱ ዩክሬንን ሊጠቅም ይችላል።"

ትራምፕ አሜሪካ ለዩክሬን ከ300 ቢሊዮን እስከ 350 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ እንደሰጠች እና በስምምነቱ "ያንን ገንዘብ ማስመለስ" እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

ነገር ግን የጀርመኑ ተመራማሪ የኪየል ኢንስቲትዩት አሜሪካ ለዩክሬን 119 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ብቻ እንደሰጠች ይፋ አድርጓል።

ስምምነቱ የደህንነት ዋስትናን ያካትታል?

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በስምነነቱ ውስጥ ከአሜሪካ ጥብቅ የደህንነት ዋስትናን ማግኘት የሚለው ሀሳብ አንዲካተት በብርቱ ይፈልጋሉ።

ምንም እንኳን በዩክሬን መገናኛ ብዙኃን ላይ የታተመው ሰነድ " ዩክሬን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የደህንነት ዋስትና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት" አሜሪካ ትደግፋለች ቢልም እስካሁን እንዲህ ዓይነት ዋስትና አልተሰጠም።

ትራምፕ የአሜሪካ ኮንትራክተሮች በዩክሬን መኖራቸው ለደህንነት ዋስትና ይሆናል ሲሉ ጠቁመ፤ ነገር ግን አሁን የዩክሬን ደህንነት ኃላፊነት በአውሮፓ ላይ ወድቋል።

የማዕድን ውሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ዓመት በዜሌንስኪ የቀረበው፣ አሜሪካ አገራቸውን መደገፏን ለመቀጠል የሚያስችል ተጨባጭ ምክንያት ለመስጠት በሚል ነበር።

ትራምፕ መጀመሪያ ላይ ዩክሬን የማዕድን ሀብቶቿን ለማግኘት በምላሹ "የመዋጋት መብት" ታገኛለች ብለው ነበር።

ነገር ግን በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል በዋሽንግተን የተጋጋለ ውይይት ከተካሄደ በኋላ አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠውን ወታደራዊ እርዳታ በሙሉ አቁማለች።

ስምምነቱ መቼ ይፈረማል?

ትራምፕ በዋይት ሐውስ በሚደረገው ውይይት ላይ ስምምነቱ እንደሚፈርም ተናግረው ነበር።

የዩክሬን ጠ/ሚ ሽሚሃል አሜሪካ እና ዩክሬን የስምምነቱ የመጨረሻ ረቂቅ እንዳዘጋጁ ቢገልፁም፣ የዜለንስኪ ረዳት ሚካሃይሎ ፖዶሊያክ ግን የስምምነቱ ማዕቀፍ ብቻ ይፈረማል ብለዋል።

ነገር ግን በጉብኝቱ ወቅት ምንም ነገር አልተፈረመም።

ይልቁንም በኦቫል ኦፊስ ውስጥ በፕሬዝዳንት ትራምፕ እና በዜሌንስኪ መካከል የጋለ የቃላት ምልልስ ተደርጓል።

በዚህ ምልልሳቸው በጣም የተናደዱት ትራምፕ ዜሌንስኪ በጦርነቱ ወቅት አሜሪካ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና ቢስ እንደሆኑ ገልጸው፣ "በሶስተኛው ዓለም ጦርነት ቁማር እየተጫወትክ" ነው ሲሉ ዜሌንስኪን ተናግረዋል።

አክለውም፣ ዜለንስኪ "ስምምነት ይፈርም፤ አለበለዚያ [ከስምምነቱ] እንወጣለን" በማለት አስፈራርተው፣ "ምንም ዓይነት የማሸነፍ እድል የለህም" ብለው ነበር።

ዜሌንስኪ በበኩላቸው ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር "ምንም ዓይነት ማመቻመች" ሊኖር አይገባም ብለዋል።

ብዙም ሳይቆይ እና ከተያዘው ፕሮግራም ቀደም ብሎ ፣ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ከዋይት ሐውስ ሲወጡ ታይተዋል።

ከዚያ በኋላ ዋይት ሐውስ ስምምነቱ እንዳልተፈረመ አስታውቆ ትራምፕ ፊርማው እንዲዘገይ መወሰናቸውን ገልጿል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በትሩዝ ሶሻል ሚዲያቸው ላይ ዜሌንስኪ "በተከበረው የኦቫል ኦፊስ ውስጥ አሜሪካን ንቋል" ሲሉ ጽፈዋል።

አክለውም "ለሰላም ዝግጁ ሲሆን ተመልሶ መምጣት ይችላል" ብለዋል።

ስምምነቱ መቼ ሊፈረም እንደሚችል ለጊዜው ግልጽ አይደለም።

የዩክሬን ብርቅዬ ማዕድናት

ከዓለማችን "ወሳኝ ጥሬ ማዕድናት" ውስጥ 5 በመቶ ያህሉ በዩክሬን ይገኛሉ ተብሎ ይገመታል።

ይህ 19 ሚሊዮን ቶን የተረጋገጠ የግራፋይት ክምችትን ያጠቃልላል።

የዩክሬን የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ግዛት ኤጀንሲ እንዳለው ከሆነ አገሪቱ በግራፋይት ክምችት "ከአምስት ዋና ዋና መሪ አገሮች መካከል አንዷ ነች።"

ግራፋይት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪዎችን ለመሥራት ያገለግላል።

በተጨማሪም ዩክሬን ለባትሪዎች ቁልፍ ግብዓት የሆነው ሊቲየም፣ ከጠቅላላው የአውሮፓ ክምችት መካከል አንድ ሦስተኛው ይገኝባታል።

ከሩሲያ ወረራ በፊት ደግሞ ከአውሮፕላን ጀምሮ እስከ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ግንባታ የሚውል ቀላል ክብደት ለማምረት የሚያገለግለው ቲታኒየም የምርት ድርሻዋ የዓለም 7 በመቶ ነበር።

በተጨማሪም ዩክሬን እጅግ በጣም ብዙ ብርቅዬ የማዕድናት ክምችት አላት።

እነዚህም የጦር መሳሪያዎች፣ የንፋስ ኃይል ተርባይኖች፣ ኤሌክትሮኒክስ እና ሌሎች በዘመናዊው ዓለም አስፈላጊ የሆኑ ቁሶችን ለማምረት የሚያገለግሉ የ17 ንጥረ ነገሮች ስብስብ ናቸው።

ሩሲያ ምን ምላሽ ሰጠች?

ስምምነቱ ይፈረማል ተብሎ ከሚጠበቅበት ቀን በፊት በአገራቸው ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣብያ ላይ የቀረቡት ቭላድሚር ፑቲን፣ ለአሜሪካ አጋሮች በጋራ በሚሰሩ ፕሮጀክቶች ውስጥ ማዕድናትን ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህም በሩሲያ "አዲስ ግዛቶች" ውስጥ፣ ሩሲያ በወረራ የያዘቻቸውን የምሥራቅ ዩክሬን ግዛቶች በማመልከት፣ የማዕድን ቁፋሮዎችን እንደሚጨምር ገልጸዋል።

ፑቲን እንዳሉት አሜሪካ ከዩክሬን ጋር ብርቅዬ ማዕድናትን በሚመለከት ልታደርግ የምትችለው ስምምነት አሳሳቢ እንዳልሆነ እና ሩሲያ ያለ ጥርጥር ከዩክሬን የበለጠ የዚህ ዓይነት ሀብት አላት ብለዋል።

"አዲሶቹን ግዛቶች በተመለከተም ተመሳሳይ ነው። ወደ ሩሲያ ፌዴሬሽን በተመለሱት ታሪካዊ ግዛቶቻችን የውጭ አጋሮችን ለመሳብ ዝግጁ ነን" ብለዋል።