ጣሊያናዊቷ ታዳጊ የደረሰባት ወሲባዊ ትንኮሳ ከ10 ሰከንድ በታች ነው መባሉ ቁጣ ቀሰቀሰ

ጣሊያናዊያን ወጣቶች መስታወት ፊት ቆመው ለ10 ሰከንድ ያክል በዝምታ ራሳቸውን እየነካኩ የሚያሳይ ምስል እየለጠፉ ነው

የፎቶው ባለመብት, INSTAGRAM

ወሲባዊ ትንኮሳ ከ10 ሰከንድ በታች ከሆነ እንደ ትንኮሳ ይቆጠራልን?

የጣሊያን ወጣቶች ቁጣቸውን በማሕበራዊ አምባዎች እየገለጡ ነው።

ምክንያታቸው ደግሞ አንድ የትምህርት ቤት አስተዳዳሪ፤ ታዳጊ ላይ ያደረሰው ወሲባዊ ትንኮሳ (ጉንተላ) ከ10 ሰከንድ በታች ነው ሲሉ ዳኛው ክሱን መሻራቸው ነው።

የ17 ዓመቷ ታዳጊ የሮም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ናት።

ወደ ክፍል ለመሄድ ከጓደኛዋ ጋር ደረጃ እየወጣች ሳለ ያደረገችው ሱሪ ይወድቃል፤ አንድ እጅ መቀመጫዋን እየነካ የውስጥ ሱሪዋን ይጎትታል።

“የኔ ፍቅር፤ እየቀለድኩ አንደሆነ መቼም ይገባሻል” ይላል ዞር ብላ የተመለከተችው ግለሰብ።

ይህ የሆነው በፈረንጆቹ ሚያዝያ 2022 ነው። ተማሪዋ አንቶኒዮ አቮላ የተባለውን የ66 ዓመት ግለሰብ ለፖሊስ ሪፖርት ታደርጋለች።

ተማሪዋን ያለፈቃዷ መንካቱን ቢያምኑም እንደቀልድ ያደረግኩት ነው ሲል አስተባበለ።

የሮም አቃቤ ሕግ ግለሰቡ የሶስት ዓመት ተኩል እሥር ይገባዋል ሲል ቢከራከርም ተከሳሹ በያዝነው ሳምንት በነፃ ተለቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዳኛዎቹ፤ ጉንተላው ከ10 ሰከንድ በታች በሆነ ጊዜ ውስጥ ስለሆነ “ወንጀል አይደለም” ሲሉ በየኑ።

ከብይኑ በኋላ ፓልፓታ ብሬቬ አሊያም ቁንፅል ጥቃት የተሰኘው ቃል በማሕበራዊ ሚድያ ናኝቷል።

#10secondi በሚል በርካታ ጣሊያናዊያን በቲክቶክና ኢንስታግራም ቁጣቸውን እየገለጡ ይገኛሉ።

ጣሊያናዊያን ወጣቶች መስታወት ፊት ቆመው ለ10 ሰከንድ ያክል በዝምታ ራሳቸውን እየነካኩ የሚያሳይ ምስል እየለጠፉ ነው።

እርግጥ ነው እኒህን ምስሎች መመልከት ትንሽ ይጎረብጣል። ዓላማቸውም እሱ ነው። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ 10 ሰከንድ ምን ያክል ረዥም እንደሆነ ማሳየት።

ዋይታ ሎተስ የተሰኘው ተከታታይ ድራማ ተዋናይ ፓውሎ ካሚሊ ነው ይህን ያስጀመረው። ከዚያ በሺህ የሚቆጠሩ ተከተሉት።

በኢንስታግራም ገጿ 29.4 ሚሊዮን ሰዎች የሚከተሏት የጣሊያን እጅግ ታዋቂዋ ተፅዕኖ ፈጣሪ ቺያራ ፌራኚ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ቪድዮ ለጠፈች።

ሌላኛው የማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ ፍራንቼስኮ ቺኮኔቲ “ማነው 10 ሰከንድ ብዙ አይደለም ብሎ የሚወስነው? ጉንተላው ሲደርስስ ማነው ሰዓት የሚቆጥረው?” እያለ ሲጠይቅ ቲክቶክ ላይ ይታያል።

“ወንዶች የሴቶችን ገላ የመንካት መብት የላቸውም። ይቅርና ለ10 እና 5 ሰከንድ ለአንድ ሰከንድም ቢሆን።”

እሱ እንደሚለው የዳኞቹ ውሳኔ፤ ጉንተላ ጣሊያን ውስጥ ምን ያክል የተለመደ እንደሆነ ማሳያ ነው።

ዳኞቹ እንደሚሉት ግለሰቡ ታዳጊዋን ለጥቂት ሰከንድ ያክል ጎነተለ እንጂ “ወሲባዊ ስሜት አላሳየም።”

“ዳኞቹ እንደ ቀልድ የሆነ ነገር ነው ሲሉ በየኑ? ለኔ ግን ይህ በፍፁም ቀልድ አይደለም” ስትል ታዳጊዋ ለኮሪየሬ ዴላ ሴራ ጋዜጣ ተናግራለች።

“ግለሰቡ ምንም ድምፅ ሳያሰማ ከኋላየ መጣ። ሱሪየን ዝቅ አድርጎ የውስጥ ሱሪየን አልፎ ነካካኝ።”

ታዳጊዋ እንደምትለው በትምህርት ቤቱም ሆነ በፍትሕ ሥርዓቱ ተክዳለች።

“ተቋማቱን ማመኔ ትክክል እንዳልሆነ እየተሰማኝ መጥቷል። ይህ ፍትሕ አይደለም።”

ተማሪዋ፤ የዳኞቹ ውሳኔ ሌሎች ሴት ተማሪዎች መሰል ጥቃት ሲደርስባቸው ወጥተው የደረሰባቸውን እንዳይናገሩ የሚያደርግ ነው የሚል ስጋት አላት።

የአውሮፓ መሠረታዊ መብት ኤጀንሲ በቅርቡ የለቀቀው ጥናት እንደሚያሳየው 70 በመቶ የሚሆኑ ጣሊያኒዊያን ሴቶች ከ2016-2021 ባለው ጊዜ ትንኮሳ ደርሶባቸው ሳያሳውቁ ቀርተዋል።

“ማሳወቁ ጥቅም የለውም ብለው ያስባሉ። ነገር ግን ጥቅም አለው። ዝምታ የሚጠቅመው ጥቃት አድራሹን ነው።”