አዲስ የተገኘው የአልዘሚር በሽታ መድኃኒት ተስፋ ሰጪ ውጤት አሳየ

አንዲት የህክምና ባለሙያ የአንጎል ስካን ስትመለከት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአብዛኛው ከእርጅና ጋር በተያያዘ የሚከሰተው አልዘሚር የተባለው የአእምሮ ጤና እክልን ለማከም የሚውል ሁለተኛው መድኃኒት ተስፋ ሰጪ ውጤት ማሳየቱ ተዘገበ።

የዚህ መድኃኒት ውጤታማነት እና እውን ለመሆን መቃረቡ አስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለበሽታው መድኃኒት ማግኘት አስቸጋሪ ነው የሚለውን ግምት ይለውጠዋል ብለዋል ባለሙያዎች።

የመድኃኒቱ አምራች የሆነው ኤሊ ሊሊ እንዳለው፣ ዶናኔምባስ የተባለው ይህ የአልዘሚር መድኃኒት የበሽታውን የመስፋፋት ፍጥነት በአንድ ሦስተኛ ያዘገየዋል።

መድኃኒቱ በሚሞከርበት ጊዜ ሁለት በጎ ፈቃደኞች እና አንድ ሦስተኛው ህሙማን በአንጎላቸው ውስጥ ባጋጠማቸው አደገኛ እብጠት ምክንያት ለሞት መዳረጋቸው ተነግሯል።

“ለአስርታት የዘለቀው የአልዘሚር በሽታን ለመቀየር የሚያስችል ህክምና ለማግኘት የተደረገው ጥረት ለውጥ እያሳየ ነው” የሚሉት በዩናይትድ ኪንግደም የአንጎል ጤና ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ኬት መመሪ፣ በዚህም ሳቢያ በሽታው ያላባቸው ሰዎችን አስከሞት ድረስ ከመንከባከብ ባሻገር፣ አሁን ለማከም እና ለመጠበቅ ዕድል ይፈጠራል ብለዋል።

የመድኃኒት አምራቹ ኤሊ ሊሊ ሙሉው የሙከራ ውጤቱ ያልታተመ ቢሆንም፣ ነገር ግን ይፋ የሆኑት ቁልፍ ግኝቶቹ እንዳመለከቱት፣ መድኃኒቱ በህሙማን ጤና ላይ እና ሕይወት ዙሪያ ከፍተኛ ለውጥን አስገኝቷል።

መድኃኒት አምራቹ ኩባንያ በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ መድኃኒቱ በሆስፒታሎች ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስችለውን ፈቃድ ለማግኘት አስፋላጊውን ሂደት ይጀምራል።

የብሪስቶል ዩኒቨርስቲዋ ዶክተር ሊዝ ኩልትሃርድ እንዳሉት ምንም እንኳን መድኃኒቱን በተመለከተ የረጅም ጊዜ መረጃ ባይኖርም እንዲሁም “ጉልህ የጎንዮሽ ጉዳት” ቢኖረውም “በሽታው ያለባቸው ሰዎች ለረጅም ጊዜ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ይረዳል።”

ይህ የአሁኑ የአልዘሚር መድኃኒት ሁለተኛው ግኝት ሲሆን የበሽታውን ሂደት ለማዘግየት መቻሉ ሳይንቲስቶች ለዘመናት ያደረጉት ጥረት ለበሽታው መፍትሄ ለማግኘት በትክክለኛው መስመር ላይ እንዳደረሳቸው ማሳያ ነው ተብሏል።

ነገር ግን አሁን ለአልዘሚር ህክምና የተገኙት መድኃኒቶች ውጤታማ የሚሆኑት በሽታው በአንጎል ላይ ጉዳት ከማድረሱ ቀደም ብሎ በመጀመሪያው ደረጃ ላይ በሚገኙ ህሙማን ላይ ነው።