በጋዛ ህጻናት በረሃብ እየሞቱ እንደሆነ ዶ/ር ቴድሮስ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜናዊ ጋዛ ህጻናት በረሃብ እየሞቱ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም አስታወቁ።
እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ከጥቅምት በኋላ የመጀመሪያ ጉብኝቱን በአልአውዳ እና በከማል አድዋን ሆስፒታሎች ማድረጉንም ዶ/ር ቴድሮስ ገልጸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በሆስፒታሎቹ ቅዳሜና እሁድ ባደረገውም ጉብኝት ሁኔታው “አሳዛኝ እና አስከፊ” ሆነውም እንዳገኟቸው ዶ/ር ቴድሮስ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አጋርተዋል።
በምግብ እጦት ምክንያት አስር ህጻናት እንደሞቱ ገልጸው ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ የምግብ እጥረትም ተከስቷልም ብለዋል።
ህጻናቱም ሆነ ህመምተኞቹ ያሉበት የሆስፒታል ህንጻዎች መውደማቸውንም አክለዋል።
በካማል አድዋን ሆስፒታል ቢያንስ 15 ህጻናት በምግብ እና በውሃ እጥረት መሞታቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በደቡባዊ ራፋህ ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል አስራ ስድስተኛ ህጻን መሞቱን የፍልስጤም የዜና ወኪል ዋፋ ሰኞ እለት ዘግቧል።
በሰሜናዊ ጋዛ ያለውን አሳሳቢነት የገለጹት ዶ/ር ቴድሮስ “ አስከፊ የሆነ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት፣ ህጻናት በረሃብ ምክንያት ህይወታቸው እያለፈ ነው። የከፋ የነዳጅ እና የምግብ እና የህክምና አቅርቦቶች እጥረት ተከስቷል። እንዲሁም የሆስፒታል ህንጻዎች ወድመዋል” ብለዋል።
በሰሜናዊ ጋዛ የሚኖረው 300 ሺህ የሚገመተው ህዝብ የሚበላው እንዳጣም ተገልጿል።
“በምግብ እጦት ምክንያት 10 ህጻናት ሞተዋል” ሲሉም በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
ተቋሙ በሰሜናዊ ጋዛ ያለውን ሁኔታ ለመታዘብ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም እስካሁን ያልተፈቀደለት ሲሆን በወራትም ውስጥ ለመጀመሪያ ሲፈቀድለት ነው።
በተለይም ከህንጻዎቹ አንዱ ሙሉ በሙሉ የወደመበት አል አውዳ ሆስፒታል ሁኔታ አስከፊ ነው ሲሉም አክለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋዛ በረሃብ መመታቷ እንደማይቀር ባለፈው ሳምንት አስጠንቅቆ ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ ባለስልጣን ከህዝቡ አንድ አራተኛው ወይም 576 ሺህ ህዝብ አስከፊ የምግብ እጦት ላይ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ከሁለት ዓመት በታች ከሆኑ ስድስት ህጻናት መካከል አንዱ በአስከፊ የተመጣጠነ የምግብ እጦት እየተሰቃየ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት ኤጀንሲ (ዩኒሴፍ) የቀጣናው ዳይሬክተር በበኩላቸው “በጋዛ ሰርጥ ላይ ያለው የምግብ እጥረት ከፍቶ እንደፈራነው የህጻናት ሞትን እያስከተለ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“የህጻናቱ አሳዛኝ እና አሰቃቂ ሞት ሰው ሰራሽ ሊከሰት የሚችል እንደሆነ የሚታወቅ አንዲሁም ሙሉ በሙሉ መከላከል የምንችለው ነው” ሲሉም አዴሌ ኮድር እሁድ ዕለት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።












