ትራምፕ በአገራት ላይ የጣሉትን ከፍተኛ ታሪፍ ተፈጻሚነት ለ90 ቀናት አዘገዩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ታሪፍ በተጣለባቸው አገራት ላይ የቀረጡ ተፈጻሚነት ለ90 ቀናት እንዲዘገይ ማድረጋቸውን አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ ከቻይና ጋር የገቡበት የንግድ ጦርነት ግን እየተባባሰ ቀጥሏል።
60 ገደማ በሆኑ የአሜሪካ አጋር አገራት ላይ ተጣለው ቀረጥ ተፈጻሚ መሆን በጀመረ በሰዓታት ውስጥ ትራምፕ አስገራሚ በሆነ የፖሊሲ ለውጥ የከፍተኛ ታሪፍ ተፈጻሚነትን አዘግይተዋል።
በዚህ መሰረት ከአገራቱ ጋር የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል እና ሁሉም አገራት የሚከፍሉት "ዝቅተኛ የሆነውን 10 በመቶ ቀረጥ" እንዲሆን ተደርጓል።
ትራምፕ ይህንን ውሳኔ ባስተላለፉ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ "አክብሮት ይጎድላታል" ባሏት ቻይና ላይ ተጣለውን ቀረጥ ወደ 125 በመቶ አሳድገዋል።
ፕሬዝዳንቱ በቻይና ላይ ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት ቤጂንግ ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የ84 በመቶ ቀረጥ እንደምትጥል ማስታወቋን ተከትሎ ነው።
ሁለቱ አገራት በዚህ የንግድ ጦርነት ውስጥ የገቡት ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገኑ ሁሉም ምርቶች ላይ ታክስ እንዲጣል በማድረግ በዓለም የንግድ ስርዓት ላይ ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ያልታየ ለውጥ ካደረጉ ከሳምንት በኋላ ነው።
በትራምፕ በባለፈው ሳምንት ውሳኔያቸው ከሁሉም አገራት በሚገቡ መርቶች ላይ ዝቅተኛ መነሻ የሆነው የ10 በመቶ ታክስ እንደሚጣል አስታውቀዋል።
ኋይት ሀውስ፤ "የለየላቸው አጥፊዎች" ብሎ በፈረጃቸው እና ፕሬዝዳንቱ ፍትሐዊ ባልሆነ የንግድ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል ብለው በለይዋቸው አገራት ላይ የተጣለው ቀረጥ ከፍተኛ ነው።
በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት መካከል 27 የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት፣ ቪየትናም እና ደቡብ አፍሪካ የሚገኙበት ሲሆን እነዚህ አገራት ከ11 በመቶ እስከ 100 በመቶ የሚደረስ ቀረጥ ተጥሎባቸዋል።
ይህንን የትራምፕ ውሳኔ ተከትሎ ባለፈው ሳምንት የገበያ ቀውስ ተከስቷል።
በዓለም ዙሪያ በትሪሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ኪሳራ ባስከተለ ሁኔታ ብዙ ሰዎች የነበራቸውን አክስዮኖች ሸጠዋል።
በርካታ አሜሪካውያን የሸቀጦች ዋጋ ይንራል የሚል ፍራቻ ውስጥ ሲገቡ፤ ተንታኞች ደግሞ የኢኮኖሚ ውድቀት ሊያገጥም የሚችልበት እድል እየጨመረ መሆኑን እየተናገሩ ነው።
ትራምፕ፤ ትናንት ረዕቡ ከቻይና ውጪ ባሉ አገራት ላይ የተጣለውን ከፍተኛ ቀረጥ እንዳገዱ ይፋ ከማድረጋቸው አስቀድሞ፤ ከየካቲት ወዲህ ከፍተኛ በሆነ ደረጃ በአሜሪካ መንግሥት የእዳ ወለድ ላይ ጭማሪ ታይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሰዓታት በኋላ አዲሱ ለውጥ ይፋ ሲደረግ ግን በገበያው ላይ አዎንታዊ ለውጥ ታይቷል።
ትራምፕ፤ በ"ትሩዝ" ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ አሜሪካ ለጣለችው ቀረጥ አጸፋዊ ምላሽ ባልሰጡ አገራት ላይ ተፈጻሚነቱ ለ90 ቀናት እንዲዘገይ ማዘዛቸውን አስታውቀዋል።
በቻይና ላይ የተጣለውን ተጨማሪ ቀረጥ ግን ወዲያውኑ ተፈጻሚ መሆን እንደሚጀምር ገልጸዋል።
"አንዱ ወቅት ላይ፤ ምናልባትም በቅርብ ጊዜ ቻይና አሜሪካን እና ሌሎች ሀአራትን የምትገፍፍባቸው ቀናት ከአሁን ወዲህ ዘላቂ እና ተቀባይነት ያላቸው አለመሆናቸውን ታስተውላለች" ብለዋል።
የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት ትናንት የተደረገው ለውጥ በዓለም አቀፉ የፋይንስ ውድቀት ተጽዕኖ ምክንያት የተወሰነ እንዳልሆነ ተከራክረዋል። አንጋፋው ዲሞክራት ቸክ ሹመር ግን ይህ ውሳኔ ትራምፕ "እየተንገዳገዱ እና እያፈገፈጉ" መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
ትራምፕ በኋይት ሃውስ ባደረጉት ንግግር ሰዎች "እየተንቦቀቦቁ ስለሆነ" የታሪፍ ፖሊሲ ለውጡን "መደረግ እንደነበረበት" ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ፤ "አጸፋዊ ምላሽ ባልሰጡት ላይ [የቀረጡ ተፈጻሚነት] ለ90 ቀናት እንዲዘገይ ያደረግኩት 'አጸፋዊ ምላሽ ከሰጣችሁ እጥፍ እናደርገዋለን' ስለነገርኳቸው ነው።
ቻይና ላይ ያደረግነውም ይህንኑ ነው" ብለዋል። "ሁሉም ነገር በሚያስደንቅ መንገድ ይከናወናል" ብለው እንደሚያስቡም አክለዋል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ሺፒንግ "ስምምነት ላይ መድረስ የሚፈልጉበት ሁኔታ ላይ ይደርሳሉ" ብለው እንደሚያስቡም ተናግረዋል።
በቻይና እና አሜሪካ መካከል አዲሱ መካረር የተጀመረው ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ያስተዋወቁትን አዲስ ቀረጥ ተከትሎ ነው።
ትራምፕ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ቻይና ላይ ጥለው በነበረው የ20 በመቶ ቀረጥ ላይ ተጨማሪ 34 በመቶ ታክስ አስተዋውቀዋል።
ቤጂንግ በበኩሏ ከአሜሪካ በሚመጡ ምርቶች ላይ 34 በመቶ ቀረጥ በመጣል ፈጣን ምላሽ ሰጥታለች።
ትራምፕ፤ቻይና ይህንን የአጸፋ ምላሿን የማትቀለብስ ከሆነ ተጨማሪ 50 በመቶ ቀረጥ በመጣል አጠቃላይ የታክስ መጠኑን 104 በመቶ እንደሚያደርሱት ማክሰኞ ዕለት ዝተው ነበር።
ከውሳኔዋ ያላፈገፈገችው ቻይና ግን፤ አሜሪካ "የቀረጥ ወይም የንግድ ጦርነት መቆስቆስ ከቀጠለች"፤ "እስከ መጨረሻው እንደምትዋጋ" ተናግራለች።
ትራምፕ በቻይና 104 በመቶ ቀረጥ ከጣሉ ከሰዓታት በኋላ ቤጂንግ ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተጣለውን ቀረጥ ከ34 በመቶ ወደ 84 በመቶ ከፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊን ጂያን፤ አሜሪካ "ተንኳሽ በሆነ ሁኔታ ቻይና ላይ ቀረጥ መጣል ቀጥላለች" ብለዋል።
ቻይና ይህን አይነቱን "አጉራ ዘለል ተግባራት" እንደምትቃወም የተናቀሩት ቃል አቀባዩ አሜሪካ ጉዳዩን በድርድር የመፍታት ተስፋ ካልት "የእኩልነት፣ የመከባበር እና የመደጋፍ አመለካከት" ልታሳይ እንደሚገባ ተናግረዋል።












