ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አፍሪካዊቷ ደሴት ቻይናን ለመሰለል የተመረጠች “ወታደራዊ ጣቢያ” ትሆን?
አርናውድ ፖሌይ ትንሿን የሕንድ ውቅያኖስ ደሴትን ለቆ መሄድ አይሻም ነበረ። ነገር ግን ዘንድሮ ሻንጣውን ጠቅልሎ ለመኮብለል ተገዷል። ቤቴ የሚላት አጋሌጋ ደሴት ወታደራዊ ጣቢያ እየሆነች ነው በሚል ነው ጥሎ የወጣው።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአጋሌጋ ደሴት ይኖሩ የነበሩት 350 ሰዎች ብቻ ነበሩ። ዓሳ እያሰገሩ የኮኮናት ፍሬ እየሰበሰቡ ነው የኖሩት።
ሌላ ዓይነት ምግብ የሚያገኙት 1100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው የሞሪሺየስ ዋና ከተማ ነው። አንድ መርከብ በዓመት አራት ጊዜ ምግብ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ይዞ ወደ ደሴቷ ይመጣል። አነስተኛ አየር ማረፊያ ቢኖርም ለድንገተኛ ሕክምና ካልሆነ በቀር ጥቅም ላይ አይውልም።
በአውሮፓውያኑ 2015 ሞሪሺየስ እና ሕንድ ወታደራዊ ስምምነት ላይ ደረሱ። በስምምነቱ መሠረት ሕንድ በአጋሌጋ ደሴት ላይ 3 ሺህ ሜትር የሚረዝም ወታደራዊ አየር ማረፊያ ገነባች።
ነገር ግን የደሴቷ ነዋሪዎች ይህ ስምምነት አጋሌጋ ወታደራዊ ጣቢያ እንድትሆን እያደረጋት ነው የሚል ስጋት ገብቷቸዋል።
የሬጌ ሙዚቀኛው የ44 ዓመቱ ፖሌይ ይህ ፕሮጀክት እንዳይስፋፋ ዘመቻ ጀምሯል።
“ደሴቷን እወዳታለሁ፤ ደሴቷም ትወደኛለች” ይላል። “ነገር ግን ወታደራዊው ጣቢያ ሲከፈት ለቅቄ መሄድ እንዳለብኝ ገባኝ” ሲል ቁጭቱን ይገልፃል።
አጋሌጋ የሁለት ትናንሽ ደሴቶች ጥምረት ናት። ስፋቷ 25 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው። በደቡብ ምዕራባዊ የሕንድ ውቅያኖስ ላይ የምትገኘው ደሴት ለሕንድ የባሕር ኃይል እንቅስቃሴ ቁጥጥር አመቺ ናት።
ከታች ያለው የሳተላይት ምሥል ደሴቷ በአውሮፓውያኑ 2019 እና በሐምሌ 2024 መካከል ያሳየችውን ለውጥ ነው። የደሴቷ የፓልም ዛፍ ተቆርጦ አየር ማረፊያ ተሠርቶበታል። አየር ማረፊያ በደሴቷ ባሉ ሁለት መንደሮች መካከል የተገነባ ነው።
ሁለት 60 ሜትር ርዝመት ያላቸው ሕንፃዎች ተገንብተዋል። አንደኛው ሕንፃ የሕንድ አየር ኃይል ንብረት የሆነው ፒ-8አይ አውሮፕላንን ለማስጠለል የተገነባ ነው ይላሉ የአውስትራሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ሳሙኤል ባሽፊልድ።
ቦይንግ 737 ሞዴል የሆነው ፒ-8አይ አውሮፕላን የጠላትን የባሕር ኃይል አሳዶ የሚመታ እና የባሕር ኃይል ግንኙነትን የሚቆጣጠር ነው። የደሴቷ ነዋሪዎች አውሮፕላኑ ቆመው አይተውት ፎቶ አንስተውታል።
ከአውሮፕላን ማረፊያው በተጨማሪ ወደ ውቅያኖሱ ዘለቅ ብሎ የሚገባ ድልድይም ተሠርቷል። ምሑሩ እንደሚሉት ይህ ድልድይ የሕንድ አየር ኃይል ቁጥጥር ለማድረግ እና ቁሳቁስ የሚመጣበትን መርከብ ለመቀበል የተዘጋጀ ነው ይላሉ።
ዓለም አቀፉ የስትራቴጂክ ጥናት ተቋም ደሴቷ “የስለላ ጣቢያ” ሆናለች ይላል። አክሎም ሕንድ ዘመናዊ የሆነ የራዳር ቴክኖሎጂ ተክላበታለች ሲል ይገልፃል።
የሕንድ መንግሥት ስለ አጋሌጋ ከቢቢሲ የቀረበሉትን ጥያቄዎች ከመመለስ ተቆጥቦ ድረ-ገፃችን ላይ ያለውን መግለጫ ተመልከቱ ብሏል።
በመግለጫው የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ሞሪሺየስ “ተፈጥሯ አጋራችን” ናት ያሉ ሲሆን፣ ሀገራቱ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ግንኙነት እንዳላቸው ተገልጿል።
የሞሪሺየስ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ፣ የባሕር ጠረፍ ዘብ ኃላፊ እና የፖሊስ ሄሊኮፕተር ክፍል መሪ የሕንድ ዜግነት አላቸው። ሕንድ እና የምዕራብ ሀገራት በሕንድ ውቅያኖስ ላይ ቻይና ያላት ተፅዕኖ ያሰጋቸው ይመስላል።
አብዛኞቹ የአጋሌጋ ነዋሪዎች ከቻጎስ ደሴቶች የመጡ ናቸው። ቻጎስ 2 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቃት የሚገኙ ደሴቶች ሲሆኑ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ሥፍራውን ለዩናይትድ ስቴትስ አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ነው ነዋሪዎች ወደዚህ የመጡት።
የሞሪሺየስ መንግሥት ቃል-አቀባይ ለቢቢሲ እንደሚናገሩት ማንኛውም ነዋሪ ደሴቷን ለቆ እንዲወጣ አይገደድም።
ነገር ግን ነዋሪዎች ወደ አየር ማረፊያው መግባት አይችሉም። ቃል -አቀባዩ አክለው ጣቢያው የተቋቋመው የባሕር ላይ ዘረፋን ለመቆጣጠር፣ ሕገ-ወጥ የዕፅ ዝውውር ለመግታት እና ሕገ-ወጥ የዓሳ ማጥመድን ለመከላከል ነው።
ደሴቷ ወታደራዊ ጣቢያ ሆናለች የሚለውን ሐሳብ የሞሪሺስ መንግሥት አይደግፈውም። ብሔራዊው ፖሊስ በደሴቷ ላይ ነው የሚገኘው የሚል ምላሽ ይሰጣል። ነገር ግን የሕንድ ባሕር ኃይል እርዳታ እንደሚያደርግ አይክድም።
የሞሪሺየስ እና የሕንድ መንግሥታት በደሴቷ የተቋቋመው አዲሱ ጣቢያ ነዋሪዎችን ለመጥቀም የተገነባ ነው ይላሉ። ነገር ግን የደሴቷ ነዋሪዎች በሕንድ የተገነባው ሆስፒታል ውስጥ መግባት አይፈቀድላቸውም።
በቅርቡ በሞሪሺየስ ፓርላማ ቀርበው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ፕራቪንድ ጁግናውት የአጋሌጋ ደሴት ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ከፍ ብሏል ሲሉ ተደምጠዋል።
በደሴቷ የጤና እና የትምህርት እንዲሁም የትራንስፖርት መሠረተ ልማት እንዲስፋፋ አዲስ ‘ማስተር ፕላን’ ተነድፏል። የዓሳ እና የኮኮናት ምርት እንዲበለፅግም ዕቅድ ተይዟል።
ሕንድም ሆነች ሞሪሺየስ በ2015 የገቡትን የመግባቢያ ሰነድ ዝርዝር መረጃ ግልፅ አላደረጉም። ይህ ማለት ሁለቱ ሀገራት ምን ለመገንባት እንደስተማሙ ግልፅ አይደለም ማለት ነው።