በፈረንሳይ ሚስቱን እንዲደፍሩ ከ70 በላይ ወንዶችን ቀጥሯል የተባለው ግለሰብ ተከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማሳሰቢያ፡ ይህ ዘገባ አንባቢያን የሚረብሽ ይዘት አካቷል
በፈረንሳይ አንድ ግለሰብ ለሚስቱ አደንዛዥ ዕጽ በመስጠት እና በመድፈር እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት ከ70 በላይ ወንዶች እንዲደፍሯት በማመቻቸት ተጠርጥሮ ተከሷል።
ዶሚኒክ ፒ በሚል ስም የተከሰሰው የ71 ዓመቱ ግለሰብ ከ10 ዓመታት በላይ ሰዎችን ‘በኦንላይን’ እያፈላለገ በመቅጠር ቤቱ ድረስ መጥተው ሚስቱ ላይ ወሲባዊ ጥቃት እንዲያደርሱ ሲያደርግ ነበር ተብሏል።
ደርጊቱ ሲፈጸም ባለቤቱን በከፍተኛ ሁኔታ “በማደንዘዝ” እነደሆነ እና ስለሁኔታው ምንም በማታውቅበት ሁኔታ እንደሆነ የተጠርጣሪው ሚስት ጠበቃ ገልጿል።
ይህ ወንጀል ፈረንሳውያንን እጅግ ያስደነገጠ ሲሆን ከፍተኛ ቁጣንም ቀስቅሷል።
የተጠርጣሪው ባለቤት ቢያንስ 92 ጊዜ በ72 ወንዶች እንደተደፈረች ፖሊስ ገልጿል። ከነዚህ ውስጥ 50 የሚሆኑት የተለዩ ሲሆን ከዋናው ተከሳሽ ጋር ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
አሁን 72 ዓመት የሞላት ተጠቂ በአውሮፓውያኑ 2020 ፖሊስ ስለጉዳዩ እስኪያሳውቃት ድረስ ምንም ፍንጭ እንዳልነበራት ተዘግቧል።
ጠበቃዋ አንቶኒ ካሙስ ደንበኛው ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመባትን ድርጊት በቪዲዮ ማስረጃ ስትመለከት ከፍተኛ የስሜት ጉዳት ይደርስባታል ሲል ገልጿል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ከ10 ዓመታት በላይ ሲፈጽምባት የነበረውን ድርጊት ተረድታ ከዚያ ስሜት ጋር አብራ ትኖራለች ሲል ጠበቃው ጨምሮ ገልጿል።
ተጠርጣሪው ዶሚኒክ በፈረንጆቹ 2020 በመገበያያ ማዕከል ውስጥ ሶስት ሴቶችን ተገቢ ባልሆነ መንገድ በድብቅ ሊቀርጽ ሲሞክር በጸጥታ ሰራተኛ ከተያዘ በኋላ በተደረገበት ምርመራ ሚስቱ ላይ ፈጽሟል ለተባለው ወንጀል ፍንጭ ሰጥቷል።
ፖሊስ ባደረገው ተጨማሪ ምርመራ በኮምፒውተሩ ውስጥ የባለቤቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፎቶ እና ቪዲዮዎች ተገኝተዋል። በእነዚህ ፎቶዎች ላይ ባለቤቱ ራሷን የምታውቅ በማይመስል ሁኔታ ትታያለች።
ፎቶዎቹ በጥንዶቹ ቤት ሚስትየው ላይ ሲፈጸሙ የነበሩ ጥቃቶችን የሚያሳዩ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ተገምቷል።
ይህ ጥቃት ከአውሮፓውያኑ 2011 ጀምሮ ሲደረግ የቆየ እንደሆነ ተጥርጥሯል።
ፖሊስ እያደረገ ባለው ምርመራ ዶሚኒክ ሚስቱን ቤት ድረስ መጥተው የሚደፍሩ ወንዶችን ለመቅጠር በድረ ገጾች አማካኝነት የተጻጻፋቸው መልዕክቶችም ተገኝተዋል።
ተጠርጣሪው ለባለቤቱ ጭንቀትን የሚቀንስ እንክብልን ጨምሮ የተለያዩ መድሃኒቶች እንደሳጣት አምኗል።
ሰውዬው በመድፈር ተሳታፊ ከመሆን በተጨማሪ፣ ስትደፈር በመቅረጽ እና ደፋሪዎቹ ጸያፍ ቃላትን እንዲጠቀሙ ሲያበረታታ እንደነበር አቃቤ ህግ ገልጿል።
ሰውዬው ለቀጣሪዎቹ ገንዘብ እንደከፈላቸው የሚገልጽ ማስረጃ አልተገኘም።
የ72 ዓመቷን ሴት የደፈሩት ሰዎች ከ26 እስከ 74 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ እንደሆነ ተገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ አንድ ጊዜ ብቻ ወደ ጥንዶቹ ቤት የመጡ እንደሆኑ እና አንዳንዶቹ ደግሞ እስከ 6 ጊዜ ቤታቸው መጥተው እንደደፈሯት አቃቤ ህግ አመልከቷል።
ተከሳሾቹ በጥንዶቹ እውቅና እና ፍላጎት የተፈጸመ እንደሆነ ቢገልጹም ዶሚኒክ ግን ሚስቱ ራሷን እንደማታውቅ ያውቁ ነበር ሲል ተከራክሯል።
ባለሙያዎች ባለቤቱ በምትደፈርበት ወቅት “ከአንቅልፍ ይልቅ ለኮማ የቀረበ ነው” ብለዋል።
በ9 ዓመቱ እንደተደፈረ የሚገልጸው ዶሚኒክ ከቤተሰቡ እና ባለቤቱ የሚመጣበትን ሁሉ ለመቀበል እንደተዘጋጀ ገልጿል።
ሰውዬው በአውሮፓውያኑ 1991 በግድያ እና መድፈር ተከሶ የነበረ ሲሆን ይህንን ድርጊት አልፈጸምኩም ብሏል። በ1999 በመድፈር ወንጀል ተከሶ የዘረ መል ምርመራ ካደረገ በኋላ ወንጀሉን መፈጸሙን አምኗል።
ይህ ችሎት እስከመጪው ዓመት ህዳር እንደሚቆይ ይጠበቃል።
ባለፈው ሰኞ በተጀመረው ችሎት የዶሚኒክ ባለቤት ከሶስት ልጇቿ ጋር በፍርድ ቤት እንደታየች ኤኤፍፒ ዘግቧል።












