ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውድቅ ያደረጉት የደብረጽዮን ጥያቄ

የፎቶው ባለመብት, Abraham Belay/fb
ለወራት በዘለቀ ውዝግብ ውስጥ የሚገኙት የህወሓት አመራሮች አዲስ አበባ ውስጥ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎች የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በትግራይ ውስጥ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ ውይይት ማድረጋቸው ተዘግቧል።
በህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ መካከል ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ የተከሰተው አለመግባባት አሁንም ቀጥሎ ሁለቱም ወገኖች እየተካሰሱ ይገኛሉ።
ሐሙስ ኅዳር 26/2017 ዓ.ም. አዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ውስጥ በተካሄደው ውይይት በክልሉ የፀጥታ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን መንግሥታዊ የመገናኛ ብዙኃን የዘገቡ ቢሆንም፣ የሁለቱ ወገኖች መካሰስ በዚህ ስብሰባ ላይ መከሰቱን ስማቸውን መጥቀስ ያለፈለጉ ውይይቱን በቅርበት የተከታተሉ ታማኝ ምንጭ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
በፌዴራል መንግሥት እና በትግራይ ክልል አመራሮች መካከል የተካሄደው ውይይት ዋነኛ ትኩረቱ በክልሉ የፀጥታ እና የፖለቲካ ችግሮችን በጋራ መፍታት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሲሆን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ከሥልጣን እንዲነሱ ጥያቄ መነሳቱ ተነግሯል።
በደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን በትግራይ እየተከሰተ ላለው ችግር የጊዜያዊ አስተዳደሩን ደካማነት በመግለጽ ለዚህም ፕሬዝዳንቱ ጌታቸው ረዳ ምክንያት መሆናቸውን በመግለጽ "ጌታቸው ተነስቶ ምክትሉ ጄኔራል ታደሰ ወረደ" ቦታውን እንዲይዙ ሃሳብ ማቅረባቸውን ጉዳዩን በቅርብት የተከታተሉት ተሳታፊ ተናግረዋል።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የህወሓት ቡድን "ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን በተገቢው መንገድ እንዳያከናውን" በማድረግ ደብረጽዮንን እና ቡድናቸውን ከሷል።
"ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራዎች እንቅፋት የሆናችሁት እናንተ [በደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን] ናችሁ" በማለት ምላሽ የሰጡት ጌታቸው ረዳ፣ በጦርነቱ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ አድርገዋል ሲሉም ከሰዋቸዋል።
በድርጅቱ አባላት እና አመራሮች እንዲሁም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅናን ያላገኘው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ አቶ ጌታቸው እና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች ከፓርቲው ከተባረሩ በኋላ ደብረጽዮን የሚመሩት ቡድን የጊዜያዊ አስተዳደሩ መሪዎች ሥልጣን ላይ ጥያቄ ሲያነሳ ቆይቷል።
አቶ ጌታቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንትነትን ቦታ የያዙት በህወሓት ውክልናቸው ነው በሚልም ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የፌደራል መንግሥቱን ሲጠይቁ ነበር። አሁን ውዝግቡ እየተባባሰ ባለበት ጊዜም ችግሮችን ለመፍታት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ስብሰባ ደብረጽዮን ይህንኑ ጥያቄ አንስተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Abraham Belay/fb
ደብረጽዮን (ዶ/ር) አቶ ጌታቸው ከጊዜያዊ አስተዳደር መሪነታቸው ተነስተው በቦታው ጄኔራል ታደሰ እንዲተኩ ያቀረቡት ሃሳብን ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀበሉት መቅረታቸውን ምንጩ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
"ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን እንዳያከናውን 'የትግራይ ሠራዊት' ከጎናችን ነው' በማለት ሕዝቡን ግራ እያጋባችሁት ነው" በማለት የደብረጽዮን ቡድንን የወቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "በስመ ምክር ቤት በሚል ሕዝቡን እየረበሻችሁት ነው" በማለት ወቅሰዋቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም መንግሥታቸው የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ሙሉ ለሙሉ ድጋፍ አድርጌለታለሁ እንደማይል በማንሳት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ክልላዊ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ የሚጠበቅበትን እያከናወነ እንሚቆይ ማሳወቃቸውን ስለውይይቱ ለቢቢሲ የተናገሩት ምንጭ ገልጸዋል።
በዚህ ሀሳብ ያልተደሰተው በደብረጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው የህወሓት ቡድን፣ አቶ ጌታቸው ከጊዜያዊ መንግሥቱ መሪነት እንዲወርዱ በያዘው አቋም የጸና መሆኑን ስማቸውን መጥቀስ ያልፈቀዱት ምንጭ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
ለወራት በዘለቀ አለመግባባት ውስጥ ያሉት የህወሓት አመራሮች ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት ጋር ቢነጋገሩም፣ የፌደራል መንግሥቱ ግን ቡድኖቹ ችግራቸውን በጋራ እንዲፈቱ በመምከር መመለሱን ምንጩ ተናግረዋል።
በዚህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ውስጥ ቀን ሙሉ በተካሄደው ስብሰባ ላይ በክልሉ እየተካሄደ ነው በሚል በስፋት ስለሚነገረው ሕገወጥ ማዕድን ማውጣት የተነሳ ሲሆን፣ ሕዝብ እና አገርን በሚጠቅም ሁኔታ በሕጋዊ መንገድ መካሄድ አለበት ተብሏል።
ሁለቱ ወገኖች የክልሉን ሕዝብ የፀጥታ፣ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ፍላጎት ለማሟላት በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በጦርነቱ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደቀያቸው የሚመለሱበት እንዲሁም ታጣቂዎችን ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስ በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲካሄድ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነግሯል።
በተጨማሪም የክልሉ የተፈጥሮ ሃብት በሕጋዊ መንገድ ብቻ ጥቅም ላይ እንዲውሉ፣ እንዲሁም ሕዝባዊ የመንግሥት አገልግሎቶች ተሻሽለው የሕዝቡን ፍላጎት በሚያሟላ ደረጃ እንዲቀርቡ አስፈላጊው ሥራ እንዲከናወን ከስምምነት መደረሱን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በውይይቱ ላይ ከፌደራል መንግሥቱ በኩል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጤሞቲዮስ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሬድዋን ሁሴንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተሳትፈዋል።
ከትግራይ ክልል በኩል ደግሞ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ፣ ጄኔራል ታደሰ ወረደ እንዲሁም ከህወሓት በኩል ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ ምክትላቸው አማኑኤል አሰፋ እና ሌሎችም ተገኝተዋል።












