በሊቢያ "ለባርነት ጨረታ" የቀረበችው ኢትዮጵያዊቷ ነሒማ

የፎቶው ባለመብት, Refugees In Libya
በሊቢያ ታጣቂዎች በርካታ ስደተኞችን አግተው የማሰቃየት ድርጊት ሲፈጽሙባቸው የሚያሳዩ ቪድዮዎች እና ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተሠራጭተው መነጋገሪያ ሆነዋል።
ከእነዚህ ታጋቾች መካከል ነሒማ ጀማል አንዷ ናት። ነሒማ ከኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ በመሰደድ ነው ወደ ሊቢያ ያቀናችው።
'ሬፊዩጂስ ኢን ሊቢያ' የተሰኘው ተቋም በኤክስ ገፁ እንዳስታወቀው ነሒማ እና ሌሎች ስደተኞች ኩፍራ በምትባለው የሊቢያ ግዛት በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ።
ነሒማ በፎቶዎቹ እና በቪዲዮዎች ላይ አፏ በጨርቅ ተለጉሞ ስቃይ ሲደርስባት ትታያለች።
የነሒማ ቤተሰቦች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች ተልኮላቸው የማስለቀቂያ ገንዘብ እንዲከፍሉ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል።
የነሒማ እህት ኢፍቱ ጀማል፤ ነሒማ ከስምንት ወራት በፊት ነበር ከሻሸመኔ ከተማ የ11ኛ ክፍል ትምህርቷን አቋርጣ ወደ ሊቢያ የተሰደደችው ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።
"ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ይልኩልናል። ስትሰቃይ ያሳዩናል። የድምፅ መልዕክትም ልከውልናል። እህታችን 'ገንዘብ ላኩላቸው ካልሆነ ይገድሉኛል' ስትል ይሰማል።"
ነገር ግን ኢፍቱ እንደምትለው ቤተሰቡ አጋቾቹ የጠየቁትን ገንዘብ የመላክ አቅም የለውም።
ሬፊዩጂስ ኢን ሊቢያ የተባለው በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞችን ጉዳይ የሚከታተለው ተቋም እንደሚለው የ20 ዓመቷ ነሒማ ጀማል ባለፈው ግንቦት ሊቢያ ከገባች ከቀናት በኋላ ነው በታጣቂዎቹ እጅ ውስጥ የገባችው።
በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ ስቃይ ሲደርስባት እና ስትደበደብ የሚያሳዩ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ለቤተሰቦቿ ተልከዋል።
ኢፍቱ እንደምትለው ቤተሰቡ የተጠየቀውን ገንዘብ ለማሰባሰብ እርዳታ ቢጠይቅም እስካሁን ድረስ ሊሞላላቸው አልቻለም።
ቤተሰቡ የነሒማን ድምፅ ከሰማ ሁለት ሳምንት እንዳለፈው እህቷ ኢፍቱ ለቢቢሲ ትናገራለች። "ገንዘቡን ካላገኘን በቀር እንዳንደውልላቸው አስጠንቅቀውናል። በጣም ተጨንቀናል።"
ሬፊዩጂስ ኢን ሊቢያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ስቃዩና ማስፈራራቱ እንደተጠናከረ እና ይህ ደግሞ ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ እንደሆነ ይገልጻል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
አጋቾቹ ለነሒማ ማስለቀቂያ የጠየቁት ገንዘብ 6 ሺህ ዶላር ነው። የነሒማ ቤተሰብ ይህን ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል።
ለነሒማ ቤተሰብ የተላኩ ቪዲዮዎች በርካታ ስደተኞች በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ያሳያሉ።
ነሒማ እጅና እግሯ ተጠፍሮ፤ አፏ በጨርቅ ታፍኖ ትታያለች። ስቃይ ሲደርስባት እና ደም በደም ሆና የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ፎቶዎችም አሉ።
ድርጅቱ በለቀቃቸው ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች ላይ ነሒማ ብቻ ሳትሆን 50 ገደማ ሌሎች የአጋቾቹ ሰለባዎች ከጀርባዋ ተደርድረው ይታያሉ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በሊቢያ እየተካሄደ ያለውን የባርነት ንግድ ዓለም ረስቶታል ሲሉ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ይወቅሳሉ።
"ሊቢያ ውስጥ ያለው እውነታ ይህ ነው። ይህን ድርጊት አሰቃቂ ብቻ ብሎ ማለፍ ተገቢ አይደለም" ይላሉ ከዚህ ቀደም ከእገታ የተረፉት እና አሁን የመብት ተሟጋች ሆነው የሚያገለግሉት ዴቪድ ያሚቢዮ።
ዲቨድ እንደሚሉት ነሒማ አሁን ያለችበት ሁኔታ በርካታ ስደተኞች የሚያልፉት አሳዛኝ ክስተት ነው።
የመብት ተሟጋች ቡድኖች ሊቢያ በተለይ ለጥቁር አፍሪካውያን ስደተኞች መካነ መቃብር ሆናለች ይላሉ። አክለውም መሰል የእገታ ድርጊቶችን የሚፈፅሙ 'ታጣቂዎች ለምንድነው የማይጠየቁት?' ሲሉ ይጠይቃሉ።
ዴቪድ "ቁጭ ብሎ በመመልከት ፍትሕ ማግኘት አይቻልም። ፍትሕ ሊመጣ የሚችለው ይህ የታጣቂዎች ኔትዎርክ ሲበጣጠስ እንጂ በንግግር አይደለም" ይላል።
የነሒማ እና የሌሎች በሊቢያ የባርነት አረንቋ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች መጨረሻ የዓለም መሪዎች በሊቢያ ያለውን ጭካኔ ካላስቆሙ የሚቆም አይደለም ሲሉ ዴቪድ አሳሳቢነቱን ይገልጻል።
ከዚህ ቀደም በሊቢያ የነበረውን የባርነት ጨረታን የሚያስታውሰው ዴቪድ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ለችግሩ ጀርባችንን ከሰጠን ሊቢያ ለአፍሪካውያን መካነ መቃብር መሆኗ ይቀጥላል ሲል ያስጠነቅቃል።
በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ወዳለችው ሊቢያ በስደት የተጓዙት ነሒማ እና ሌሎች ስደተኞች መጨረሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም።
በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ስደተኞች ሕይወታቸውን ለመቀየር በሚል ወደ አውሮፓ በሚያደርጉት ጉዞ የሜዲቴራኒያን ባሕርን ከማቋረጣቸው በፊት ሊቢያን ይረግጣሉ።












