ፕሬዚዳንት ካጋሜ ጄነራሎችን ጨምሮ ከ200 በላይ ወታደሮችን አሰናበቱ

የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ የመከላከያ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን ጨምሮ ከ200 በላይ ወታደሮችን አሰናበቱ።

ለሁለት ዓመት ያህል በአውሮፓውያኑ 2018ና 2019 የተጠባባቂ ኃይል አዛዥ በመሆን ያገለገሉት ሜጀር ጄነራል አሎይስ ሙጋንጋ እንዲሁም በብሔራዊ መረጃ አገልግሎት የውጭ ደህንነትን ሲመሩ የነበሩት ፍራንሲስ ሙቲጋንዳ በፕሬዚዳንቱ ከተባረሩት 14 ከፍተኛ መኮንኖች መካከል ተካትተዋል።

በተጨማሪም በመከላከያ ኃይሉ ውስጥ የተለያየ ማዕረግ ያላቸውን 116 መኮንኖች እንዲሁም የ116 ወታደሮች የአገልግሎት ውል እንዲቋረጥ ማጽደቃቸውን የአገሪቱ መከላከያ ኃይል መግለጫ አስታውቋል።

መግለጫው ረቡዕ ረፋድ ላይ ስለተገለጸው 244 ያህል ወታደሮች ከኃላፊነታቸው ስለተነሱበት ምክንያት የጠቀሰው ነገር የለም።

እርምጃው ፕሬዚዳንት ካጋሜ በሩዋንዳ ያልተለመደ የተባለውን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን እንደገና በማዋቀር የመከላከያ ሚኒስትሩን እና የጦር ሰራዊት አዛዡን በተመሳሳይ ጊዜ በማባረር እና ተተኪዎቻቸውን ይፋ ካደረጉ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

አሁን መባረራቸው እስከተሰማበት ጊዜ ድረስ የሜካናይዝድ ዲቪዥን አዛዥ የነበሩት ሜጀር ጄነራል ሙጋንጋ ከአሜሪካ የጦርነት ኮሌጅ የተመረቁ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2018ና 2019 የተጠባባቂ ኃይል አዛዥ በመሆን አገልግለዋል።

ሌላኛው አሁን የተባረሩት ብርጋዲየር ጄነራል ሙቲጋንዳ በዋና መዲናዋ ኪጋሊ ወደሚገኘው የመከላከያ ኃይል ዋና መስሪያ ቤት እስኪዛወሩ ድረስ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የውጭ ደኅንነት ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።

በሩዋንዳ እና በጎረቤቷ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መካከል ከፍተኛ ውጥረት በነገሰበት ወቅትም ነው ይህ የስልጣን መሸጋሸግ እና ለውጥ እየተካሄደ ያለው። ሁለቱ አገራት ማዕከላዊውን መንግሥት ለመጣል ከአማጺ ቡድን ጋር እየሰራ ነው በማለት ሲወነጃጀሉም ይሰማል።