ፑቲን ምዕተ ዓመታት ያስቆጠረችውን የቅድስት ሥላሴን ምስል ለምን ለዕይታ አቀረቡ?

በሞስኮ በሚገኘው የመድኃኒያለም ካቴድራል ውጭ የሚገኙ ምዕመናን የቅድስት ስላሴን ስዕል ለማየት ተሰልፈው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሞስኮ በሚገኘው መድኃኒያለም ካቴድራል የኦርቶዶክስ ዝማሬዎች እና ጸሎቶች እየተሰሙ ነው።

ከኦርቶዶክስ ታላላቅ በዓላት አንዱ የሆነውን የእርገትን በዓልም ለመታደም ምዕመናኑ በካቴድራሏ ተገኝተዋል።

ነገር ግን በርካቶች ወደ ካቴድራሏ የመጡት የእርገትን በዓል መንፈሳዊ አገልግሎት ለመካፈል ብቻ አይደለም።

በቤተ ክርስቲያኗ ለዕይታ የበቃችውን ድንቅ የጥበብ ሥራን ለመመልከትም ነው።

ይህች ሥዕል በሩሲያ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣትና ስድስት ምዕተ ዓመታትን ያስቆጠረች ናት።

በመካከለኛው ዘመን ስመ ጥር በሚባለው አርቲስት አንድሬ ሩብልቭ እንደተሳለችም ይታመናል።

ሥዕሏ ቅድስት ሥላሴም በመባል ትታወቃለች።

ለመቶ ዓመት ያህል ይህች ሥዕል በመንግሥታዊው ትሬቲኮቭ ጋለሪ ውስጥ ተቀምጣ ነበር።

ሥዕሏን ባለችበት ሁኔታ ለመጠበቅ የሙቀት እና የእርጥበት መቆጣጠሪያዎች ተገጥመውላት በባለሙያዎች ክትትል እየተደረገላትም ቆይታለች።

ነገር ግን ክሬምሊን በቅርቡ ሥዕሏ ለሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንድትሰጥ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ይህም ውሳኔ የሩሲያ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ኪሪልን አስደስቷል።

“ይህች ሥዕል ወደ ቤተክርስቲያኗ የምትመለሰው አባት አገራችን ከፍተኛ የጠላት ኃይሎችን እየተጋፈጠ ባለበት ወቅት ነው” ሲሉም ፓትርያርኩ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ለምዕመናን ተናግረዋል።

አክለውም “ሥዕሏ የተመለሰችልን አገራችን እንድትረዳልን እንዲሁም ለማስመለሰ ለወሰኑት ለሩሲያ ፕሬዚዳንት ፑቲንም እንድንጸልይ ነው” ብለዋል።

የሥዕሏ መመለስ ፓትርያርኩን ቢያስደስትም የመወዛገቢያ ምንጭ መሆኗም አልቀረም።

በሩሲያ ውስጥ ታዋቂ ከሆኑት የጥበብ ታሪክ ፀሐፊዎች አንዱ የሆኑት ሌቭ ሊፍሺትስ ዝውውሩን ከተቃወሙት መካከል አንዱ ናቸው።

ሥዕሏ ከትሬትያኮቭ ጋለሪም እንዳትንቀሳቀስ ምክር ከሰጡት የባለሙያዎች ቡድን አንዱ ሲሆኑ፣ ዝውውሩ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትልም እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

“ይህ ውሳኔ የአንድ ሰው የግል ፍላጎት ነው” ሲሉም ሌቭ ያስረዳሉ።

የትሬትያኮቭ ጋለሪ የእደሳ ምክር ቤትም ይህንን ተቃውሞ ቆሟል።

የሩሲያ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ኪሪል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ሥዕሏ በሙዚየሙ ውስጥ በነበረችበት ወቅት የእደሳ ቡድኑ ልክ በጽኑ ህክምና ውስጥ እንዳለ ግለሰብም ነበር ክትትል እና ጥበቃ ሲያደርግላት የነበረው። በጣም ዘመናዊ በሆኑ መሳሪያዎችም ቁጥጥር ይደረግላት ነበር” ብለዋል።

“ሥዕሏ መዛወሩ የፖለቲካ ውሳኔ ነው። በአሁኑ ወቅት በሥልጣን ላይ ያሉት ወደ ሰማያት እያንጋጠጡ እርዳታ ለማግኘት ተስፋ እያደረጉም ይገኛሉ” ሲሉም አስረድተዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ እንዲሁም ለሩሲያው ፕሬዚዳንት ሕዝባዊ ድጋፍ ቤተ ክርስቲያኗ የምታደርገውን ድጋፍን ለማስቀጠልም ይረዳ ይሆናል።

ሩሲያ “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ብላ የምትጠራውን ጦርነት ፓትርያርኩ በይፋ ሲደግፉ ይሰማል።

ቀደም ሲልም የተገደሉ የሩሲያ ወታደሮች ከሃጢአታቸው ይነጻሉም ሲሉም ተናግረዋል።

ከዚህም በላይ የሩሲያ ፓትርያርክ የፕሬዚዳንት ፑቲን የግዛት ዘመን ከአምላክ የተሰጠ ሥልጣን ነው በማለት ጠቁመዋል።

“ለአገር እና ለሕዝብ ጠቀሜታ ያለው ሥራ እንድትሰሩ እና ትልቅ ኃላፊነት ያለው አገልግሎት እንድትፈጽሙ አምላክ በሥልጣን ላይ አስቀመጣችሁ” ሲሉም ፓትርያርኩ ከጥቂት ወራት በፊት ተናግረው ነበር።

ከዚህ አንጻር የቅድስት ሥላሴ ሥዕል ለቤተ ክርስቲያኗ መመለስ ቤተ ክርስቲኗ ለአገዛዙ ላሳየችው ታማኝነትም እንደ ሽልማት ሊተረጎም ይችላል። ነገር ግን ይህ የታሪኩ ቅንጭብ አካል ብቻ ሊሆን ይችላል።

ይህም “ፕሬዚዳንቱ ቤተ ክርስቲያኗ ለርዕዮተ ዓለማቸው መሠረት ናት ብለው ያምናሉ” ሲሉ የካርኒጌ ሩሲያ የዩሬዥያ ማዕከል ባልደረባ አንድሬ ኮሌስኒኮቭ ይናገራሉ።

“የፑቲን የቅርብ ሰዎችም ሆነ ፕሬዚዳንት ፑቲን የራሳቸው የሆነ ርዕዮተ ዓለም አላቸው። ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ፣ ፀረ ምዕራባዊ እና ፀረ ኢምፔሪያሊስት ናቸው። የዚህ ርዕዮተ ዓለም መሠረቱ ምንድን ነው? እንደ ቀድሞው የሩሲያ ታሪክ ማርክሲዝም፣ ሌኒኒዝምምን ሳይሆን ሃይማኖትን ማዕከል አድርጓል” ይላሉ።

“ፑቲን ሃይማኖተኛ ሰው ናቸው። ነገር ግን ክርስቲያን ናቸው ለማለት ይከብዳል፤ ተግባራቸው ከእውነተኛ ክርስቲያናዊ እሴቶች ጋር አይጣጣምም። ምክንያቱም ጭካኔ ክርስቲያናዊ እሴት አይደለም። ከዚህም በመነሳት ፑቲን ለየት ያለ ሃይማኖት ተከታይ ናቸው ማለት ነው” ሲሉም ይናገራሉ።

የሩሲያ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ኪሪል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሞስኮ በሚገኘው የመድኃኒያለም ካቴድራል ውጭ የሚገኙ ምዕመናን የቅድስት ሥላሴን ሥዕል ለማየት ተሰልፈው ይገኛሉ። ምዕመናኑ በሥዕሏ ተዓምራዊ ፈውስን ለማግኘትም በመሻት ላይ ናቸው።

“አገራችን በልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ውስጥ ስለምትገኝ ሁኔታዎች ፈታኝ ናቸው” በማለት በካቴድራሏ የተገኘችው ቫለንቲና ትናገራለች “አገራችን ድል እንድትቀዳጅ እየጸለይን ነው” ብላለች።

“ማንኛውም የሚያስተውል ሰው ጦርነቱ በቅርቡ እንደሚቆም ተስፋን ያደርጋል” ትላለች ሌላኛው ምዕመን አንቶኒና “አምላክ የሚረዳን ይመስለኛል።”

የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይህ ጦርነት ቅዱስ ጦርነት የሚል ትርክት ስትናገር ይደመጣል።

በዚህም ሩሲያውን አምላክ ከጎናቸው እንደሆነ እንዲያምኑ ለማድረግ እንዲሁም ዩክሬንን የወረረችው አገራቸው መሆኗን እንዲዘነጉ ለማድረግ ነው።