የሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ተጠርጣሪው ፍርድ ቤት ለመቆም ብቁ አይደለም ተባለ

ፊሊሺዬን ካቡጋ ችሎት ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, UN-IRMCT

የምስሉ መግለጫ, ፊሊሺዬን ካቡጋ ችሎት ውስጥ

ከአስርታት በፊት ሩዋንዳ ውስጥ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት በገንዘብ ደግፏል ተብሎ የተከሰሰው የ88 ዓመቱ አዛውንት በጤና ችግር ምክንያት ፍርድ ቤት ለመቆም ብቁ አይደለም ሲል የተባበሩት መንግሥታት ፍርድ ቤት ወሰነ።

የተከሳሹ ግለሰብ ፊሊሺዬን ካቡጋ ጠበቃ ከዕድሜ መግፋት ጋር በሚያጋጥም የአእምሮ ችግር እንዳለበት በመግለጽ ፍርድ ቤት አቤቱታውን አቅርቦ ነበር።

ግለሰቡ የዘር ማጥፋቱ ከተፈጸመ በኋላ ለ26 ዓመታት ተሰውሮ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ከሦስት ዓመት በፊት ነበር ፓሪስ ውስጥ የቴኣዘው።

ካቡጋ 800 ሺህ የሚሆኑ ቱትሲዎችን እና ለዘብተኛ ሁቱዎችን ጨፍጭፈዋል የሚባሉትን የሁቱ ጎሳ ሚሊሻዎችን በገንዘብ ደግፏል ተብሎ ቢከሰስም፣ እሱ ግን ክሱን አስተብብሏል።

በሩዋንዳ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ተጠያቂዎችን ለፍርድ ለማቅረብ ለአስርት ዓመታት በተደረገው ጥረት ውስጥ ፍርድ ቤቱ እንዲህ ያለውን ውሳኔ ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ዘ ሄግ ኔዘርላንድስ ውስጥ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጦር ወንጀሎች ችሎት ዳኛ ካቡጋ “ትርጉም ባለው ሁኔታ በፍርድ ሂደቱ ወስጥ ለመሳተፍ ብቁ አይደለም፤ ወደፊትም በፍርድ ቤቱ ለመቆም የሚያስችል የጤና ብቃት ሊኖረው አይችልም” ብለዋል።

በተጨማሪም ዳኛው ሌላ አይነት የሕግ ሂደት አማራጭን አቅርበዋል። ይህም ከመደበኛው የችሎት ሂደት ጋር የተቀራረበ፣ ነገር ግን የጥፋተኝነት ውሳኔ የማይተላለፍበት ሊሆን ይችላል ተብሏል።

ችሎቱ የፊሊሺዬን ካቡጋ የጤና ሁኔታ እንዲመረመር ዕድል ለመስጠት ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ሂደቱ እንዲቆም ማዘዙ ይታወሳል።

የፍርድ ቤቱ ሰነዶች እንደሚያሳዩት የተከሳሹ 88 ዓመት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን በትክክለኛው ዕድሜው ላይ አንዳንድ አለመግባባቶች አሉ።

ፊሊሺዬን ካቡጋ በአውሮፓውያኑ በ1970ዎቹ በሻይ እርሻ ልማት ላይ ተሰማርቶ ከፍተኛ ሃብትን ያገኘ ሲሆን፣ በዘር ማጥፋቱ ወቅት ለሁቱ ገዳይ ቡድኖች አባላት ገጀራ ለመግዛት የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል ተብሎ ተከሷል።

በተጨማሪም ይህ ሃብታም ነጋዴ በነበረው የሬዲዮ ጣቢያ አማካይነት ሁቱዎች ቱትሲዎችን እንዲገድሉ የሚያነሳሱ ጥቃት አባባሽ የጥላቻ ንግግሮችን በማሰራጨት የዘር ማጥፋቱን አበረታቷል ተብሎ ተከሷል።

ከሦስት ዓመት በፊት የፈረንሳይ መርማሪዎች ፓሪስ ውስጥ በሚገኝ አንድ አፓርትመንት ውስጥ ሐሰተኛ ስም ተጠቅሞ ሲኖር ነበር በቁጥጥር ስር ያዋሉት።

ሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ተሰውሮ የቆየው ፊሊሺዬን ካቡጋ ያለበትን ጠቁሞ ላስያዘ ሰው አሜሪካ 5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ለመስጠት ቃል ገብታ ነበር።