ተከታዮቹን 1 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ያጭበረበረው ናይጄሪያዊ ፓስተር በቁጥጥር ስር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, EFCC NIGERIA
ተከታዮቹን እና ሌሎች ግለሰቦችን 1 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አጭበርብሯል የተባለው ናይጄሪያዊ ፓስተር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ።
ቲዮ ኦ ኢቦኚ የተባለው የሃይማኖት መሪ ከተከታዮቹን እና ከሌሎችም ሰዎች 1.3 ቢሊዮን ናይራ (የናይጄሪያ ገንዘብ) ወይም 930 ሺህ ዶላር አጭበርብሯል የሚል ክስ ቀርቦበታል።
ይህ ታዋቂ ፓስተር በቁጥጥር ስር የዋለው ከጥቂት ወራት በፊት ሲሆን ከሳምንታት በፊት በዋስ ተለቆ ነበር። ነገር ግን በፖሊስ መያዙ ለሕዝብ ይፋ የሆነው ይፋ የሆነው አሁን ነው።
የናይጄሪያ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ቃል አቀባይ ግለሰቡ በማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር መዋሉን ይፋ ማድረግ ለምርመራ ሥራው አስፈላጊ ስላልነበረ የሃይማኖት መሪው መታሰር ሳይገለጽ መቆየቱን ተናግረዋል።
እራሱን ፓስተር ብሎ የሚጠረው ኢቦኚ ግን በቁጥጥር ስር ውሏል የተባለው በብሎገሮች በሚነዛ “ሐሰተኛ ዜና ነው” ብሏል።
የናይጄሪያ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ወንጀል ኮሚሽን ኤቦኚ መቀመጫውን በአሜሪካ ካደረገው ፎርድ ፋውንዴሽን ካገኘው 20 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች 1300 ዶላር እንዲከፍሉ ሲያደርግ ነበር ብሏል።
ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ እራሱን ፓስተር ብሎ የሚጠራው ግለሰብ ከፎርድ ፋውንዴሽን ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ አላገኘም ብሏል።
የናይጄሪያ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ወንጀል ኮሚሽን “የወንጀል ምርመራው ኢቦኚ ከፎርድ ፋውንዴሽን ጋር ምንም አይነት ግንኙነትም ሆነ ትውውቅ እንደሌላው አሳይቷል።”
ፎርድ ፋውንዴሽንም እንዲሁ ስለግለሰቡም ሆነ በግለሰቡ ስም ስለተከፈተ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ምንም እውቅና እንደሌላው መግለጹን የናይጄሪያ መንግሥት ኮሚሽን አስታውቋል።
የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ወንጀል ኮሚሽን ኢቦኚ ተከታዮቹን እና ሌሎች ሰዎችን አጭበርብሮ በሰበሰበው ገንዘብ በሚያስተዳድረው ሮክ ሚኒስትሪ ኢንተርናሽናል ቸርች ስም አምስት ቤቶችን መግዛቱን አስታውቋል።
ግለሰቡ ግን በቁጥጥር ስር አልዋልኩም፤ ሰዎችንም አጭበርበሯል የተባለው ሐሰት ነው ሲል ፌስቡክ ገጹ ላይ ወጥቶ በቪዲዮ ለተከታዮቹ መልዕክቱን አስተላልፏል።
“እኔን ተጠቅመው ገንዘብ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች የሚያስራጩት ትልቅ የውሸት ዜና ነው። ይህ እውነት አይደለም” ሲል የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።
የናይጄሪያ መንግሥት ኮሚሽን በበኩሉ ምርመራውን ሳጠናቅቅ ክስ ለመመሥረት እየተዘጋጀሁ ነው ይላል።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ዴል ኦዬዋሌ ፐንች ለተባለ ጋዜጣ፣ ኢቦኚ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በቁጥጥር ስር ውሎ በዋስ መለቀቁን ተናግረዋል።
“ለረዥም ጊዜ ታስሮ ቆይቷል። እያካሄድን ባለነው ምርመራ ምክንያት በወቅቱ መግለጫ መስጠት አስፈላጊ አልነበረም” በማለት ቃል አቀባዩ ለጋዜጣው ተናግረዋል።












