ገቢዎች ሚኒስቴር ካለፈው ዓመት በ279 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ግብር ቢሰበሰብም በቂ አለመሆኑን ገለጸ

የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ279 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው አስታውቀ። ይሁን እንጂ ሚኒስቴሩ አሁንም እየተሰበሰበ ያለው ገቢ "ከመንግሥት የወጪ ፍላጎት" አንጻር በቂ እንዳልሆነ ገልጿል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህን ያለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የዘጠኝ ወራት የአጻጸም ሪፖርት ላይ ነው።
በ17 ገጾች የተዘጋጀው ሪፖርቱ በሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ የሚመራው ተቋም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት በዝርዝር ያስቀመጠ ነው።
ተቋሙ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 646.72 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን ያመለከተው ሪፖርቱ ከዕቅዱ በላይ 653.2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ጠቁሟል።
ከዚህ ውስጥ የአገር ውስጥ የታክስ ድርሻ 345.93 ቢሊዮን ብር የውጭ ንግድ ቀረጥ እና ታክስ ድርሻ ደግሞ 307.27 ቢሊዮን ብር ነው።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተሰበሰበው 646.72 ቢሊዮን ብር ውስጥ 61.13 ቢሊዮን ብር "በተሻሻለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር መሠረት" ለክልሎች መተላለፉን ሚኒስቴሩ በሪፖርቱ ላይ ገልጿል።
ይህ የገቢ መጠን ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ279 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
"የገቢ አሰባሰቡን በየዓመቱ እያሻሻለ" መምጣቱን የገለጸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፤ ይሁንና "አፈጻጸሙ ከመንግሥት የወጪ ፍላጎት [እና] የታክስ ገቢ ከጠቅላላ አገራዊ ምርት ጥምርታ አንጻር ሲመዘን ገና ብዙ መሥራት እንዳለብን ያሳይል" ብሏል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የፌደራል መንግሥቱ የተለያዩ አዳዲስ የታክስ ዓይነቶችን ሲያስተዋውቅ ነባሮቹም ላይ ማሻሻያዎችን አድርጓል።
በዚህ የ2017 ዓ.ም. ብቻ የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ማሻሻያ፣ ኤክሳይዝ ታክስ፣ አረንጓዴ (የተሽከርካሪ ዝውውር ዓመታዊ) ታክስ እና የንብረት ታክስን ሥራ ላይ ለማዋል ዕቅድ አለው።
የመንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ከኢኮኖሚው ሊሰበሰብ የሚገባው ታክስ እንደማይሰበሰብ እና የታክስ መሠረትን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
አነዚህ ተደራራቢ የታክስ ዓይነቶች በሕዘብ ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶ/ር አብዱልመናን መሐመድ የመንግሥት ወጪ መብዛት "ከፍተኛ የገንዘብ ፍላጎት አስከትሏል" ሲሉ ባለፈው ጥር ወር ላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከመንግሥት ወጪ መብዛት በተጨማሪ ከዚህ በፊት ለመንግሥት የገቢ ምንጭ የነበሩት ብድር እና የገንዘብ ህትመት መቀነሳቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን መንግስት ትኩረት ወደ ታክስ እንዲሆን አስገድዶታል።
በመንግሥት በኩል የተስተዋለውን ይህን የገቢ እና ወጪ መዛባት ለማስተካከት "አንደኛ ወጪ መቀነስ ወይም ገቢ መጨመር አለበት" የሚሉት ዶ/ር አብዱልመናን፤ "ወጪ ለመቀነስ ግን ፍላጎት አላሳየም" ብለው ነበር።
"ስለዚህ ገቢውን መጨመር አለበት፤ ገቢ ለመጨመር ደግሞ አለ የሚለውን ሕብረተሰቡን ታክስ የማድረጊያ ዘዴ መፈለግ አለበት። ክስን እንደ ዋና የመንግሥትን ወጪ መሸፈኛ ዘዴ መጠቀም ካለበት ሕብረተሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ ታክስ ማድረግ መቻል ይኖርበታል" ብለዋል ዶ/ር አብዱልመናን።
"ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት መንግሥት ታክስን እንደ ገቢ ምንጭ እንዲጠቀም ከፍተኛ ጫና አሳድረውበታል" ሲሉ መንግሥት የገቢ ምንጩን እንዲቀይር የተገደደበትን ምክንያት ያብራራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከስድስት ወራት በፊት ባለፈው ኅዳር ለምክር ቤት አባላት ባደረጉት ማብራሪያ መንግሥታቸው በ2017 በጀት ዓመት 1.5 ትሪሊዮን ብር ከታክስ ለመሰብሰብ ማቅዱን አስታውቀው ነበር።
የገቢዎች ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በላከው ሪፖርት ላይ ያነሳው ሌላኛው ጉዳይ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያጋጠሙ "ተግዳሮቶች"ን ነው።
ተቋሙ ገቢን መደበቅ፣ ግብይትን ያለደረሰኝ ወይም በሕገ ወጥ ደረሰኝ ማከናወን፣ ኮንትሮባንድ፣ የግብር ስወራ እና የታክስ ማጭበርብር "አሁንም ያልተቀረፉ የታክስ አስተዳደሩ ተግዳሮቶች" መሆናቸውን ጠቁሟል።
በዘጠኝ ወራት ውስጥ 15.6 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ "የገቢ እና የወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃዎችን" እና "ሕገ ወጥ ገንዘብ" መያዙን ሚኒስቴሩ በሪፖርቱ ላይ ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም በኮንትሮባንድ ወንጀል የተሳተፉ 1 ሺህ 105 ተጠርጣሪዎች በጉምሩክ፣ በክልል ፖሊስ፣ በፌደራል ፖሊስ እና በመከላከያ ሠራዊት አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አክሏል።












