በአዲሱ የትራምፕ የስደተኞች ፖሊሲ ከአገር እንዲባረሩ በአሰሳ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ሕገወጥ ከተባሉ ስደተኞች ጋር በተያያዘ እሑድ በተጀመረው የአሰሳ ዘመቻ እስካሁን 956 ሰዎች መታሰራቸው ተገለጸ።
ይህም ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከተመለሱ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር መሆኑን የአገሪቱ የስደተኞች እና የጉምሩክ ተቋም የሆነው ኢሚግሬሽን ኤንድ ከስተምስ ኢንፎርስምነት (አይሲኢ) አስታውቋል።
የፌደራል ተቋማት በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥልጣናቸው እንዲሰፋ መደረጉን ተከትሎ በቺካጎ፣ ኔዋርክ፣ ኒው ጀርዚ እና ማያሚ ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞችን የማደኑ ዘመቻ ተካሂዷል።
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወደንጀለኞች ያሏቸውን ያልተመዘገቡ ስደተኞችን በጅምላ ወደመጡባቸው አገራት እንደሚመልሱ ቃል ሲገቡ ነበር።
ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በየቀኑ በአማካይ 311 ስደተኞችን ከአሜሪካ ያባርሩ የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህ አብዛኞቹ ወንጀል የፈጸሙ ናቸው።
ትራምፕ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ 21 ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔዎች አሳልፈዋል።
ከስደተኞች ጋር በተያያዘው ተቋም ኃላፊነት የተሾሙት ቶም ሆማን ሰዎች ሲያዙ በቺካጎ ነበሩ። በውሳኔው ዴሞራቶች ደስተኛ እንዳልሆኑ ተገልጿል።
የቺካጎ ከንቲባ ብራንደን ጆንሰን ሰዎች የታሰሩት በስደተኞች ጉዳይ ተቋም እንጂ በቺካጎ ፖሊስ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ሰዎች መብታቸውን እንዲያውቁም አስታውሰዋል።
በማያሚም የስደተኞች ጉዳይ ተቋም ሠራተኞች "የስደተኞች ጉዳይ ትግበራዎችን" እንዳከናወኑ የማያሚ የደኅንነት ምርመራ ተቋም በማኅበራዊ ገጹ አስታውቋል።
በማያሚ ሰነድ አልባ ስደተኞች በተለያየ ክስ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
አንድ ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ቃሉን የሰጠ ግለሰብ ባለቤቱ በተቋሙ መወሰዷን ገልጿል።
"የሚሠሩት ነገር ያስጸይፋል። ያሳፍራል። ባለቤቴ ዜግነት ልታገኝ እየሞከረች ነው። መጥተው ወሰዷት" ብሏል።
ወታደራዊ አገልግሎት የሰጡ ሰዎችን ጨምሮ ሰነድ አልባ ነዋሪዎች እና ዜጎች በአሰሳው መያዛቸውን የኔዋርክ ከንቲባ ራስ ባራካ ተናግረዋል።
"ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ሲሸበሩ ኔዋርክ ዝም ብላ አታይም" ብለዋል።
የስደተኞች ተቋም በሒደቱ ዜጎችም ሊነኩ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።
የትራምፕ የስደተኞች ጉዳይ ኃላፊ ሰነድ አልባ ሰዎች በአሰሳ ወቅት ከተያዙ ወደመጡበት አገር ይመለሳሉ ብለዋል።
እስር እና ሰዎችን ወደ መጡበት አገር የመመለስ ሥራ "በቁጥር ይጨምራል" ሲሉ ለኤቢሲ ተናግረዋል።
"አሁን ትኩረታችን የሕዝብ ደኅንነት እና የብሔራዊ ደኅንነት ስጋትን ማስወገድ ነው" ብለዋል።
ያለፈው ሳምንት አርብ 538፣ ቅዳሜ 593 እና እሑድ 286 ሰዎች ተይዘዋል።
በጆ ባይደን የአራት ዓመታት አስተዳደር ዘመን ከአሜሪካ ተባረው ወደ አገራቸው የተመለሱ 1.5 ሚሊዮን ስደተኞች ናቸው።












