በሱዳኗ ኤል ፋሽር በሦስት ቀናት ውስጥ 6 ሺህ ሰዎች እንደተገደሉ የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ባለፈው ዓመት በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ቁጥጥር ሥር በነበረችው ኤል ፋሽር ከተማ በሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተጎጂዎች እና የዐይን ምስክሮችን የጠቀሰው የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት አመለከተ።
አንድ ግለሰብ በሦስቱ ቀናት ውስጥ የተፈፀመውን ጥቃት ሲገልጽ " የሆነ አስፈሪ ፊልም ክፍል ይመስል ነበር" ብሏል።
የዐይን እማኙ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ( አርኤስኤፍ) ተዋጊዎች ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በአንድ ዩኒቨርሲቲ ሕንፃ ውስጥ ተጠልለው በነበሩ 1000 ሰዎች ላይ ተኩስ በከፈቱበት ወቅት አስክሬኖች ሲወረወሩ ተመልክቷል።
የተባበሩት መንግሥታት በዚህ ሪፖርቱ በከተማዋ በሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የጅምላ ግድያ፣ የሞት ቅጣት፣ ስቅይት፣ ጠለፋ እና ወሲባዊ ጥቃት መፈፀማዎችን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ጠቅሷል።
እነዚህ ድርጊቶች እንደ "የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች" እንደሚቆጠሩም ገልጿል።
አርኤስኤፍ በዚህ ሪፖርት ላይ ያለው ነገር ባይኖርም ከዚህ ቀደም የቀረቡበትን ተመሳሳይ ክሶች አስተባብሏል።
ሱዳን በአገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል በተፈጠረ የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ዝግ ከሆነች ሦስት ዓመት ሊሞላት ተቃርቧል።
እየተካሄደ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለ ሲሆን ከ13 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ደግሞ ከቀያቸው አፈናቅሏል።
በሴቶች፣ በወንዶች እና በሕፃናት ላይ በስፋት የሚፈፀሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን እንደ ጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ ውለዋል።
ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች፤ አርኤስኤፍም እና የሱዳን ጦር በእነዚህ ወንጀሎች ይከሰሳሉ።
አሜሪካ እና ሂውማን ራይትስ ዎችም አርኤስ ኤፍ እና አጋሮቹ በምዕራባዊ ዳርፉር ግዛት በሚኖሩ ማሳሊት ሕዝቦች እንዲሁም አረብ ያልሆኑ ማኅበረሰቦች ላይ የዘር ማጥፋት እንደፈፀሙ ያምናሉ።
ሆኖም በቅርቡ የወጡ የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርቶች ይህንን በዝርዝር ይህንን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።
ኤል ፋሽር በዳርፉር የምትገኝ ቁልፍ ከተማ ስትሆን ለ18 ወራት ያህል በከበባ ውስጥ ትገኛለች። በጦርነቱ አሰቃቂ ታሪኮች ከተሰሙባት ከተሞችም አንዷ ነች።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ ከሆነ በአውሮፓውያኑ 2025 መጨረሻ ከ140 በላይ ሰለባዎች እና የዐይን ምስክሮች እማኝነታቸውን ሰጥተውታል።
በዚህም በኤል ፋሽር ጥቃት በመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት ውስጥ ቢያንስ 4 ሺህ 400 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ1 ሺህ 600 በላይ የሚሆኑት ቀያቸውን ለቀው መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።
"ለሳምንት በቆየው ጥቃት በትክክል የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ያለምንም ጥርጥር በጣም ከፍተኛ ነው" ብሏል ሪፖርቱ።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኃላፊ ቮልከር ተርክ በሱዳን ያሉ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በቁጥጥራቸው ሥር ባሉ ኃይሎች የሚፈፀሙ ከባድ ሰብዓዊ ጥሰቶችን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የዚህ ግጭት ደጋፊዎችም እጃቸውን እንዲያወጡ ዓለም አቀፍ ግፊት ጨምሯል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለአርኤስኤፍ ተዋጊዎች ዋነኛ የጦር መሣሪያ አቅራቢ እንደሆነች በስፋት የሚነገር ሲሆን የሚቀርብባትን ክስ በተደጋጋሚ አስተባብላለች።
ባለፈው ሳምንትም ዩናይትድ ኪንግደም የሱዳን ጦር እና አርኤስኤፍ ከፍተኛ የጦር አዛዦች እንዲሁም ለአርኤስኤፍ እንዲዋጉ ኮሎምቢያውያን ተዋጊዎች መልመለዋል ያለቻቸውን ሦስት የውጭ ዜጎች ጨምሮ የሱዳንን ጦርነት እያቀጣጠሉ ነው ባለቻቸው ስድስት አካላት ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
በቅርቡም የብሪታንያ ሕግ አውጪዎች የተባበሩት መንግሥታት ዩናይትድ ኪንግደም በሕጋዊ መንገድ ለዩኤኢ የሸጠችውን የጦር መሣሪያ ዩኤኢ እንደገና ለአርኤስኤፍ ሸጣለች ማለቱን ተከትሎ ጉዳዩን አንስተውት ነበር።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይቬት ኩፐር " ዩኬ በእጅ አዙር ወደ ሌሎች እጅ እንዳይገቡ ለመከላከል የጦር መሣሪያ ሽያጯን በተመለከተ በጣም ጠንካራ ቁጥጥር አላት። ይህንን በትኩረት መከታተላችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።
ይህ በእንድህ እንዳለ በሱዳን ምዕራባዊ ክፍል የሚገኘው የሱዳን መንግሥት ተቀናቃኝ ኃይል ከአርኤስኤፍ ጋር 'ሱዳን ፋውንዲንግ አሊያንስ' የተባለ ጥምረት ለመመስረት እቅድ መያዙን አስታውቋል።
የአፍሪካ ኅብረት እነዚህን እቅዶች ውድቅ ያደረገ ሲሆን እንዲህ ዓይነት እርምጃዎች አንድነትን አደጋ ላይ እንደሚጥሉ አስጠንቅቋል።















