በሱዳን የፈጸመው ግድያ በቢቢሲ የተጋለጠው ወታደራዊ መሪ በዩኬ ማዕቀብ ተጣለበት

'አቡ ሉሉ' በሚል ስም የሚታወቀው ብርጋዴር ጀነራል አል-ፋታሕ አብዱላህ ኢድሪስ
የምስሉ መግለጫ, 'አቡ ሉሉ' በሚል ስም የሚታወቀው ብርጋዴር ጀነራል አል-ፋታሕ አብዱላህ ኢድሪስ

'አቡ ሉሉ' በሚል ስም የሚታወቀው ብርጋዴር ጀነራል አል-ፋታሕ አብዱላህ ኢድሪስ ቢያንስ 10 የሚሆኑ ያልታጠቁ ምርኮኞችን ሲገድል የሚያሳይ ቪድዮ ተገኝቷል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ኤል-ፋሸር ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸም ተከስሷል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ያደረገውን ምርመራ ተከትሎ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አቡ ሉሉ ላይ ማዕቀብ ጥሏል።

አርኤስኤፍ በኤል-ፋሸር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደገደለ ይታመናል። የዩኬ የውጭ ጉዳይ ጸሐፊ የቬት ኩፐር እንዳሉት በሱዳን የተፈጸመው ግድያ "በዓለም ሕዝብ ሕሊና ታትሞ የሚቀር ጠባሳ" በመሆኑ "ያጠፉት ሳይቀጡ መታለፍ የለባቸውም"።

የአርኤስኤፍ ምክትል መሪ አብዱል ራሒም ሐምዳን ዳጋሎን ጨምሮ ሦስት ወታደራዊ መሪዎች ላይ ማዕቀብ ተጥሏል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ መሐመድ ደጋሎ (ሔሜቲ) ወንድም የሆነው ደጋሎ በአውሮፓ ኅብረትም ማዕቀብ ተጥሎበታል። ኤል-ፋሸር በአርኤስኤፍ እጅ ስትወድቅ የወጡ ቪድዮዎች ላይ ታይቷል።

በሁለት ዓመቱ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል።

ኤል-ፋሸር በሱዳን ጦር ሥር የነበረች የዳርፉር ግዛት ናት። በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እጅ ከወደቀች በኋላ የጦርነቱ አቅጣጫ ተለውጧል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ ቬሪፋይ ባደረገው ምርመራ ወታደሮች ከተማዋን ከበባ ውስጥ ከትተው ሰዎችን ሲያንገላቱ የሚያሳዩ ቪድዮዎች ወጥተዋል።

ወደ ከተማዋ የዕለት ከዕለት አቅርቦት ለማስገባት የሞከሩ ሰዎች ስቅይት ተፈጽሞባቸዋል። ከተማዋን በአሸዋ በመክበብ ንጹኃን እንዳይወጡ ታግደዋል።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ባወጣው መገለጫ "አቡ ሉሉ ንጹኃን ላይ ባነጣጠረ ዘር እና ሃይማኖት በለየ ጥቃት ጥፋተኛ ነው" ብሏል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ያረጋገጠው ቪድዮ፤ ያለፈው ጥቅምት ላይ አቡ ሉሉ በሰሜን ምዕራብ የከተማዋ ክፍል ያልታጠቁ ሰዎችን ሲገድል ያሳያል። የአርኤስኤፍ ወታደሮች በተሰጣቸው ትዕዛዝ ደስታቸውን ሲገልጹም ይታያል።

ይፋ በሆነው ቪድዩ ተዋጊዎች በፒክአፕ መኪና ላይ ሆነው በዘጠኝ አስከሬኖች አጠገብ ሲያልፉ እየሳቁ ነበር።

"ይህንን ሥራ ተመልከቱ። ይህንን የዘር ማጥፋት ተመልከቱ" ሲል አንዱ በደስታ ሲናገር ይደመጣል።

ካሜራውን ወደራሱ አዙሮ ፈገግ ካለ በኋላ ባልደረቦቹን ይቀርጻል። ሁሉም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አርማ ያለበትን ወታደራዊ ልብስ ለብሰዋል። ወታደሩ "ሁሉም በዚህ መንገድ ይሞታሉ" ሲልም ይሰማል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በኤል-ፋሸር ከተማ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎችን ሳይገደሉ አልቀሩም ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) "የጦር ወንጀሎች እና በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች" ተፈጽመዋል የሚለውን መርምሯል።

ዩኬ ማዕቀብ የጣለችባቸው ወታደራዊ አመራሮች "ዘግናኝ የጅምላ ግድያ፣ ስልታዊ ወሲባዊ ጥቃት እና ንጹኃንን ዒላማ ያደረገ ግድያ" መፈጸማቸው ተገልጿል።

ወታደራዊ መሪዎቹ የጉዞ ክልከላ ተጥሎባቸዋል። ሃብት ንብረታቸውን እንዳያንቀሳቅሱም ታግደዋል።

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ጸሐፊ የቬት ኩፐር "ማዕቀቡ እጃቸው በደም የተነከረው ኮማንደሮች ላይ ያነጣጠረ ነው። ወደ ከተማው እርዳታ ለማስገባት የሚደረገውን ጥረትም አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል።

ዩኬ ምግብ፣ መጠለያ እና የጤና አገልግሎት ለማቅረብ ተጨማሪ 21 ሚሊዮን ፓውንድ ቃል ገብታለች።

የዬል ዩኒቨርስቲ የሰብአዊ ምርምር ክፍል ይፋ ያደረገው የሳተላይት ምሥል የጅምላ መቃብሮችን አሳይቷል።

የአርኤስኤፍ መሪ ሔሜቲ ወታደሮቻቸው በኤል-ፋሸር "ጥሰት" መፈጸማቸውን አምነው ምርመራ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በኤል-ፋሽር መስከረም 19 በአንድ መስጊድ ላይ አርኤስኤፍ ባደረሰው ጥቃት 78 ሰዎች ተገድለዋል። የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው በጥቅምት ወር በተፈናቃዮች ካምፕ ላይ በተደረጉ የድሮን እና የመድፍ ጥቃቶች 53 ተጨማሪ ሰዎች ተገድለዋል።

ለቢቢሲ ቬሪፋይ የደረሱ ቪዲዮዎች አርኤስኤፍ የምግብ እና አስፈላጊ አቅርቦቶችን እንዳይገቡ እገዳ እንደጣለ ጠቁመዋል።

በሱዳን ጦርነት እንዲሳተፉ የኮሎምቢያ ወታደሮች መልምለዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ አሜሪካ ከሰሞኑ ማዕቀብ ጥላለች።