ሰኞ ዕለት መቀለ ውስጥ በትግራይ ኃይሎች የተከሰተው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, SM
በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ የትግራይ ኃይል አባላት ለተቃውሞ አደባባይ በመውጣት ቅሬታቸውን ከማሰማት ባሻገር ለሰዓታት መንገድ ዘግተው እንደነበር ተዘግቧል።
በትግራይ ኃይሎች ውስጥ ያሉ የአርሚ 22 አባላት ሰኞ ጥቅምት 3/2018 ዓ.ም. ከጠዋት ጀምሮ በመቀለ ውስጥ በሚገኙ ዋነኛ መንገዶች ላይ ወጥተው ቅሬታቸውን እና ጥያቄያቸውን አሰምተዋል።
የሠራዊቱ አባላት ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎችን ያቀረቡት በሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ለሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሲሆን፣ ሰልፈኞቹ ጠዋት ላይ ወደ አስተዳደሩ ጽሕፈት ቤት በመሄድ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ዛሬ ጥቅምት 4/2018 ዓ. ም. በማዕከላዊ የትግራይ ዞን በሚገኘው ነበለት አካባቢ መናኸሪያ እና መንገድ መዘጋቱን ለማወቅ ተችሏል።
በምሥራቅ ትግራይ ሐውዜንም ዛሬ እስከረፋድ ድረስ ተመሳሳይ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ተጀምረው እንደተቋረጡ የቢቢሲ የመቀለ ዘጋቢ ታዝቧል።
መቀለ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ እንዳለው፤ትናንት አደባባይ የወጡት የትግራይ ኃይሎች አባላት በጋዜጠኞች ፎቶ ለመነሳት፣ በቪዲዮ ለመቀረጽ እንዲሁም ጥያቄዎችን ለመመለስ ፈቃደኞች አልነበሩም።
አርሚ 22 የተባለው የትግራይ ኃይሎች ክፍል፤ ካምፓቸው ከሚገኝበት አካባቢ ተነስተው ባለፉበት መንገድ ላይ ጎዳናዎች ተዘግተው ስለነበረ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎ እንደዋለ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በከተማዋ የሚገኙ መንገዶችን ሰልፈኞቹ በመዝጋታቸው እንቅስቃሴዎች ተገድበው እንደዋሉ የቢቢሲ የመቀለ ዘጋቢም ታዝቧል።
ሰላማዊ ሰልፉ ከጠዋት አንስቶ እስከ ከሰዓት ድረስ እንደቀጠለም ዘጋቢያችን አስተውሏል። ዋነኛ ጥያቄያቸው በተለይም ከደመወዝ ክፍያ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተገልጿል።
የሠራዊቱ አባላት አደባባይ በወጡበት ጊዜ ካኪ የደንብ ልብሳቸውን ለብሰው ጥያቄያቸውን የሚያንጸባርቁ መፈክሮችን ሲያሰሙ ነበር።
ከእነዚህም መካከል የሠራዊቱ እና የተሰው አባላት የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄን የሚመለከቱ፣ ሰላም እንደሚፈልጉ የሚገልጹ እንዲሁም አስተዳደሩ ጥያቄያቸውን እንዲሰማ የሚጠይቁ ይገኙበታል።
በተጨማሪም ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሠራዊቱን ጥያቄ መመለስ የማይችል ከሆነ የሌላውን ሕዝብ ጥያቄ "መመለስ አይችልም" በማለት ጥያቄያቸው ቅድሚያ እንዲሰጠው የሚጠይቁ መፈክሮች ተሰምተዋል።
ከሚኖሩበት ካምፕ በጠዋት በመውጣት ወደ ክልሉ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ያመሩት የአርሚ 22 አባላት ዓላማቸው በዋናነት የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት ማነጋገር ነበር።
ለተቃውሞ ሰልፉ አደባባይ የወጡት የትግራይ ኃይሎች አባላት ወደ አስተዳደሩ ጽሕፈት ቤት ዘልቀው በመግባት ቢሞክሩም ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ በሥፍራው ስላልነበሩ ሊያገኗቸው ሳይችሉ ቀርተዋል።
አስከ እኩለ ቀን ድረስ በመቀለ ማዕከላዊ ክፍል ውስጥ የቆዩት ሰልፈኞቹ ከሰዓት በኋላ ላይ ወደ አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ የሚወስደውን መንገድ ዘግተው ለሰዓታት ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት ቢያንስ አንድ በረራ መስተጓጎሉን አንድ የአየር ማረፊያው ሠራተኛ ተናግርዋል።

አዲ ሀውሲ፣ 70 ካሬ እና ዳያስፖራ በሚባሉ አካባቢዎች መንገዶች መዘጋታቸው እንቅስቃሴ ማስተጓጎሉን ዘጋቢያችን ታዝቧል። ወደ አውሮፕላን ማረፊያ የሚወስደው እንዲሁም ከባድ የጭነት መኪና የሚተላለፍበት መንገድ በሰልፉ ምክንያት መዘጋቱም ጫና ማሳደሩን ተመልክቷል።
ከሰዓት ከ11 ሰዓት በኋላ ለተቃውሞ ሰልፍ አደባባይ የወጡት የአርሚ 22 አባላት ተወካዮች የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።
በውይይቱ ላይ ከክልሉ ባለሥልጣናት እና ከሠራዊት አባላት ተወካዮች ውጪ ማንም አልታደመም።
የትግራይ ኃይሎች ጥያቄያቸውን ካቀረቡ በኋላ "ጥያቄዎቹ ደረጃ በደረጃ ታይተው ምላሽ ያገኛሉ" የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ለውይይት ዝግጁ መሆናቸውን ካሳወቁ በኋላ በሰልፈኞቹ ተዘግተው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎባቸው የነበሩ መንገዶች መከፈታቸውን ቢቢሲ ለመረዳት ችሏል።

በትግራይ ኃይሎች ውስጥ ከአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከቀድሞ የክልሉ ልዩ ኃይል እንዲሁም ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ የገቡ ወጣቶችም የሚገኙበት ሲሆን፤ በደመወዝ አከፋፈል ዙርያ ያላቸውን ጥያቄ ይዘው ወደ አደባባይ መውጣታቸውን የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩ እንዲሁም ከፌደራል ፖሊስ እና ከቀድሞው የክልሉ ልዩ ኃይል የትግራይ ኃይልን የተቀላቀሉ ወታደሮች፤ ቀድሞ የደመወዝ ክፍያ ዝርዝር ውስጥ ስለነበሩ ደመወዛቸው ከ2013 ዓ. ም. ጀምሮ መቀጠሉን የመቀለው ዘጋቢያችን አስተውሏል።
ሆኖም ግን ጦርነቱን በ2013 ዓ. ም. እና በ2014 ዓ. ም. የተቀላቀሉ ወጣቶች ደመወዛቸው ይከፈላቸው የጀመረው ከ2015 ዓ. ም. በኋላ እንደሆነ በመጥቀስ፤ "ልክ እንደሌሎቹ ድጎማ ይሰጠን፤ አድልዎ አይፈጠር፤ ለ2013 ዓ. ም. እና 2014 ዓ. ም. ክፍያ ይሰጠን" ብለው መጠየቃቸውን ይናገራል።
ሰልፈኞቹ ከደመወዝ ጥያቄ በተጨማሪ ቤት መሥሪያ መሬት እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል። በቅርቡ በጦርነቱ ለተገደሉ ሰዎች ቤተሰቦች ቤት መሥሪያ መሬት መስጠት ተጀምሯል።
በቀጣይ በጦርነቱ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎችም ቦታ እንደሚሰጥም ተገልጿል።
ትናንት የክልሉ ባለሥልጣናት ከከሠራዊቱ አባላት ጋር ከተወያዩ በኋላ የመሬት ጥያቄን በተመለከተ በጊዜያዊው አስተዳደር ሥር ያለ ካቢኔ "ጉዳዩን አጥንቶ ውሳኔ እንደሚሰጥ" ተገልጿል።
ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ በተደረሰው የፕሪቶሪያ ስምምነት በትግራይ ክልል ውስጥ ጦርነት የቆመ ቢሆንም፣ በፌደራል መንግሥቱ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲሁም በህወሓት መካከል በዘለቀው አለመግባባት ክልሉ አሁንም ድረስ በፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ትጥቅ ፈትተው በመሰናበት ወደ ሰላማዊ ሕይወት ይመለሳሉ የተባሉት የትግራይ ኃይል አባላት አሁንም ድረስ በካምፖች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት ጥያቄዎችን ሲያነሱ ቆይተዋል።
ህወሓት ከሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ሲሰረዝ፤ የፌደራል መንግሥቱ ህወሓት ከኤርትራ ጋር በመሆን ጦርነት ለመቀስቀስ እየሠራ ነው በማለት እየከሰሰው ነው።
ህወሓትና የኤርትራ መንግሥት የቀረበባቸውን ክስ ቢያስተባብሉም፤ ይህ ሁኔታ ዳግም በትግራይ ውስጥ ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።















