ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቲክቶክ የሚታገድበት ቀን መቅረቡን ተከትሎ ትራምፕ ዋና ሥራ አስኪያጁን ሊያናግሩት ነው
ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከቲክቶክ ዋን ሥራ አስኪያጅ ጋር ንግግር ሊያደርጉ እንደሆነ ተሰምቷል።
ግዙፉ ማኅበራዊ ሚድያ ቲክቶክ በቅርቡ አሜሪካ ውስጥ መሥራት ያቆማ ተብሎ ይጠበቃል።
ሥራ አስኪያጁ ሹ ዚ ቺው ሰኞ ዕለት ትራምፕን በማራላጎ ያገኛቸዋል ተብሎ ተጠብቆ እንደነበር የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
እየተገባደደ ባለው የአውሮፓውያኑ መባቻ የወጣው ሕግ ቲክቶክ ካልተሸጠ በሚመጣው ጥር አሜሪካ ውስጥ ጥቅም እንዳይውል ይታገዳል ይላል።
የቲክቶክ ባለቤት ቻይናዊው ባይትዳንስ የተባለ ኩባንያ ነው።
ኩባንያው ለአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባስገባው ይግባኝ ዕገዳው እንዲዘገይ ጠይቋል።
አሜሪካ ቲክቶክን ለማገድ የወሰነችው ባይትዳንስ ከቻይና መንግሥት ጋር ግንኙነት አለው በሚል ምክንያት ነው። ቲክቶክም ሆነ ባይትዳንስ ግን ይህንን ውንጀላ ያስተባብሉታል።
በአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የፀደቀው ሕግ "የዩናይትድ ስቴትስን ብሔራዊ ደኅንነት በውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ካሉ መተግበሪያዎች ለመጠበቅ" የወጣ ነው ይላል።
ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ቲክቶክ መታገድ አለበት ሲሉ ነበር። ነገር ግን አሁን እገዳውን እየተቃወሙት ይገኛሉ።
ቲክቶክ ከታገደ ፌስቡክ ይበለፅጋል ይላሉ። ፌስቡክ በ2020 ምርጫ ለመሸነፋቸው አንዱ ምክንያት እንደሆነ ነው ትራምፕ የሚያምኑት።
ቲክቶክ የሚታገደው በአውሮፓውያኑ ጥር 19 ነው። ትራምፕ ደግሞ ሥልጣናቸው የሚጀምረው በበዓለ ሲመታቸው ቀን ጥር 20 ነው።
ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያስገባው ቲክቶክ ዕገዳው "የተወሰነ እንዲዘገይ" እና አዲሱ አስተዳደር "ጉዳዩን እንዲመረምረው" ጠይቋል።
ኩባንያው ቲክቶክን አሜሪካ ውስጥ ካሉ "እጅግ አስፈላጊ የንግግር መድረኮች" አንዱ ነው ያለው ሲሆን ይህንን ማገድ ለኩባንያውም ሆነ ለተጠቃሚዎቹ "ትልቅ ጉዳት" መሆኑን ተናግሯል።
ትራምፕ ሰኞ ዕለት በነበራቸው አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ አስተዳደራቸው "ቲክቶክ እንደሚያጤነው" ተናግረዋል።
"እኔ ለቲክቶክ የተሻለ ቦታ አለኝ። ምክንያቱ 34 በመቶ ወጣቶች ድምፃቸውን ለኔ ሰጥተዋል" ብለዋል።
"አንዳንድ ሰዎች [ለማሸነፌ] ቲክቶክ ትልቅ አስተዋፅፆ ነበረው ይላሉ። ቲክቶክ ትልቅ ተፅዕኖ አለው።"
ዕድሜያቸው ከ18-29 ያሉ አብዛኛዎቹ አሜሪካዊያን ባለፈው ኅዳር ለዲሞክራቷ ዕጩ ካማላ ሀሪስ ያላቸውን ድጋፍ ቢያሳዩም ከ2020 ምርጫ ጋር ሲነፃፀር በርካታ ወጣቶች ለትራምፕ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
ትራምፕ ባለፈው ሰኔ ነው የቲክቶክ አካውንት የከፈቱት። በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት በርካታ ሚሊዮን የቲክቶክ ተከታዮች ማፍራት ችለዋል።