ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አዲስ አበባ ከአፍሪካ ለኑሮ እጅግ ውድ ከተሞች መካከል ስንተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች?
የዓለም ሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መምጣት በአገራት ውስጥ ከተሞች እንዲስፋፉ እያደረገ ነው። በዚህም ሳቢያ በከተሞች ያለው መሠረተ ልማት እና አቅርቦት ጫና እየበረታበት ነው።
ይህ ደግሞ ከገጠር አካባቢዎች ይልቅ በከተሞች ውስጥ ኑሮ እየተወደደ ደህነት እየተስፋፋ በመሄድ ላይ ነው። ወትሮውንም በከተሞች የሚቀርቡ ምርት እና አገልግሎቶች እየተወደዱ የሚሄዱ ቢሆንም፣ በተለይ ባለፉት ዓመታት ዓለምን ያጋጠሙት ወረርሽኝ እና ጦርነቶች የከተማ ኖሮን ፈታኝ አድርገውታል።
የአንድ ከተማ ኑሮ ውድ መሆን የሚለካው በተለያዩ መመዘኛዎች ነው። የዋጋ ግሽበት፣ የቤት ዋጋ፣ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም ምጣኔ ሀብታዊ ፖሊሲዎች ከግምት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።
ለምሳሌ እንደ ሆንግ ኮንግ፣ ሲንጋፖር እና ዙሪክ (ስዊትዘርላንድ) ያሉ ከተማዎች የዓለማችን እጅግ ውድ የሚባሉት የመኖሪያ ቤት እና የትራንስፖርት ዋጋ ከፍ ያለ በመሆኑ ነው።
ኢስላማባድ (ፓኪስታን)፣ ሌጎስ (ናይጄሪያ) እና አቡጃ (ናይጄሪያ) ደግሞ የአገራቱ የመገበያያ ገንዘብ ከመግዛት አቅም ጋር በተያያዘ ለኑሮ ርካሽ ከሚባሉ ከተማዎች ተርታ ተመድበዋል።
ሜርሴር የተባለው የከተሞችን ደረጃ በዋጋ መዝኖ የሚያወጣ ድረ-ገፅ የአውሮፓውያኑ 2024 መገባደድን ተከትሎ የ226 ከተሞችን ሰንጠረዥ ይፋ አድርጓል።
ለመኖር እጅግ ውድ ከሚባሉት የማይቀመሱ ከተሞች ጀምሮ ኑሮ በጣም ርካሽ የሆነባቸው ከተማዎች በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል።
አዲስ አበባ፣ ዳካር (ሴኔጋል)፣ ሜክሲኮ ሲቲ (ሜክሲኮ) እና ኤደንብራ (ስኮትላንድ) ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ደረጃቸው ትልቅ ለውጥ ካሳዩ ከተማዎች መካከል ሆነዋል።
ቀድሞ ለኑሮ አመቺ እና ብዙም ውድ ያልሆነች ትባል የነበረችው አዲስ አበባ ውድ ከሚባሉ የአህጉሪቱ ከተሞች መካከል ተደልድላለች። አዲስ አበባን ጨምሮ የዓለማችን እጅግ ውድ የሚባሉ ከተማዎችን እንመልከት።
10 የዓለማችን እጅግ ውድ ከተማዎች
በዓለማችን ኑሮ በጣም ውድ ከሆነባቸው 10 ከተማዎች መካከል ግማሽ ያክሉ የሚገኙት በምዕራብ አውሮፓ ነው። ከእነዚህ መካከል አራቱ የሚገኙት ስዊትዘርላንድ ውስጥ ነው። ነገር ግን አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሆንግ ኮንግ እና ሲንጋፖር ናቸው።
ከስዊትዘርላንድ ከተማዎች በተጨማሪ የዩናይትድ ኪንግድም መዲና ለንደን ከአስሩ መካከል ተካታለች። የአረብ ኤምሬቶች ዱባይ ደግሞ ከመካከለኛው ምሥራቅ ከተሞች ቁንጮዋ ናት።
ወደ ደቡብ አሜሪካ ስንመጣ የኡራጓይዋ ሞንቴቪድዮ በጣም ውድ ከተማ ስትባል፤ የአርጀንቲና መዲና ቡዌኖስ አይረስ ከደረጃዋ ዝቅ ብላለች።
ሰሜን አሜሪካ የሚገኙት ኒው ዮርክ፣ ባሐማስ እና ሎስ አንጀለስ እጅግ ውድ ከሚባሉ ከተሞች መካከል ሆነዋል።
በአህጉረ አፍሪካ አዲስ አበባ እና ጂቡቲን ጨምሮ ዳካር በዋጋ ግሽበት ምክንያት ኑሮ እጅግ ውድ እየሆነ ከመጣባቸው ከተሞች መካከል ተደልድለዋል።
አስሩ ውድ የዓለማችን ከተማዎች፡
1. ሆንግ ኮንግ - ሆንግ ኮንግ
2. ሲንጋፖር - ሲንጋፖር
3. ዙሪክ - ስዊትዘርላንድ
4. ጄኔቫ - ስዊትዘርላንድ
5. ባዜል - ስዊትዘርላንድ
6. በርን - ስዊትዘርላንድ
7. ኒው ዮርክ - ዩናይትድ ስቴትስ
8. ለንደን - ዩናይትድ ኪንግደም
9. ናሳው - ባሐማስ
10. ሎስ አንጀለስ - ዩናይትድ ስቴትስ
10 የአፍሪካ እጅግ ውድ ከተማዎች
በአፍሪካ ኑሮ በጣም ውድ የሆነባቸው 10 ከተሞችን በተለመከተ የሚወጡ ዘገባዎች ወጥነት የላቸውም።
ለምሳሌ ስታቲስታ የተባለው ድረ-ገፅ በአውሮፓውያኑ 2024 አዲስ አበባ ከአፍሪካ ከተማዎች እጅግ ውዷ ናት ይላል። ኑምቤዮ የተባለው የከተሞችን የኑሮ ውድነት ዋጋን የሚያሰላ የቀመር ቋት ደግሞ ኢትዮጵያ በ2024 በኑሮ ውድነት ከአፍሪካ ሦስተኛ ናት ይላል።
ሜርሴር በበኩሉ አዲስ አበባ ለኑሮ ውድ ከሆኑ 10 ከተሞች መካከል ባትካተትም በ2024 ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ካሳዩ አምስት የዓለማችን ከተማዎች መካከል አዲስ አበባ አንዷ እንደሆነች ይጠቅሳል።
ባለፈው 2023 የአውሮፓውያኑ ዓመት በኑሮ ውድነት 194ኛ ደረጃ ላይ የነበረችው አዲስ አበባ ዘንድሮ ወደ 138 ከፍ ብላለች። አክራ (ጋና)፣ ኢስታንቡል (ቱርክ)፣ ቲራና (አልቤኒያ) እና ካይሮ (ግብፅ) ሌሎች በአንድ ዓመት ውስጥ ትልቅ ለውጣ ያሳዩ አሊያም የዋጋ ግሽበታቸው ከፍ ያሉ ከተሞች ናቸው።
የስታቲስታ 10 የአፍሪካ እጅግ ውድ ከተሞች
1. አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
2. ሐራሬ - ዚምባቡዌ
3. ጆሀንስበርግ - ደቡብ አፍሪካ
4. ኬፕ ታውን - ደቡብ አፍሪካ
5. ፕሪቶሪያ - ደቡብ አፍሪካ
6. ደርባን - ደቡብ አፍሪካ
7. ካዛብላንካ - ሞሮኮ
8. አልጀርስ - አልጄሪያ
9. ማራካሽ - ሞሮኮ
10. ታንጂዬር - ሞሮኮ
የኑሮ ውድነት በአዲስ አበባ
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ የተካሄዱ እና እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶች፣ አለመረጋጋት፣ መፈናቀል፣ መንግሥት ለነዳጅ የሚያደርገው ድጎማ ቀስ በቀስ መቀነስ፣ የነዳጅ ዋጋ መናር፣ የብር የመግዛት አቅም መዳከም በመላው አገሪቱ የኑሮ ውድነት እንዲከሰት ምክንያት መሆናቸው ይነገራል።
በተለይ ደግሞ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚፈልሱ ዜጎች በከተማዋ መሠረተ ልማት እና አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል።
በዚህም የምግብ፣ የውሃ፣ የቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት ዋጋ. .. . በከፍተኛ ደረጃ ንሯል እነዚህ ሁሉ ሲደማመሩ አዲስ አበባን በአፍሪካ ለኑሮ ውድ ከሆኑ ከተሞች ተርታ እንድትሰለፍ ያደርጋታል።