ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ከረጢት መጠቀም እና ማምረትን በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ አዋጅ ፓርላማ ቀረበ
በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ከረጢት መጠቀም፣ ማመረት እና ወደ አገር ውስጥ ማስገባት በገንዘብ እና በእስራት የሚያስቀጣ ድንጋጌ የተካተተበት ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።
በረቂቅ አዋጁ መሠረት የፕላስቲክ ከረጢት የተጠቀመ ወይም ለመጠቀም ይዞ የተገኘ ማንኛውም ሰው ከአምስት እስከ አስር ሺህ ብር ገንዘብ ይቀጣል።
በተመሳሳይ የፕላስቲክ ከረጢት ማምረት፣ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፣ ለገበያ ማቅረብ፣ መሸጥ ወይም ለንግድ ዓላማ ማከማች ከሃምሳ እስከ መቶ ሺህ ብር ያስቀጣል። ከዚህ በተጨማሪም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።
አነዚህን "የወንጀል ድርጊቶች" የፈጸመው ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት በሚሆንበት ጊዜ ቅጣቱ ሦስት እጥፍ እንደሚሆን ረቂቁ ያትታል።
የፕላስቲክ ከረጢት መጠቀም እና ማመረት በወንጀል ተጠያቂ የሚያደረገው አዋጅ፤ "የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ" ነው። ስድስት ክፍሎች እና 28 አንቀጾች ያሉት ይህ ረቂቅ አዋጅ የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ እና አወጋገድን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን ይዟል።
ከረቂቅ አዋጁ ሦስት መርሆዎች መካከል አንደኛው "የበከለን ማስከፈል" አንዱ ነው። ቆሻሻን ከምንጩ መቀነስ፣ መልሶ መጠቀም፣ መልሶ ዑደት ማድረግ እና በአግባቡ ማስወገድ፤ እና የሕብረተሰብ ተሳትፎ ማሳደግ ቀሪዎቹ መርሆዎች ናቸው።
አዋጁ ከ18 ዓመታት በፊት የወጣውን የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጅ የሚሽር ነው። በአዲሱ ረቂቅ የተሻረው አዋጅ "በቀላሉ በስብሶ ወደ አፈር የሚደባለቅ መሆን አለመሆኑን የሚያሳይ ምልክት ያልተደረገበትን የፕላስቲክ ከረጢት ለገበያ ማቅረብ" ይከልክል ነበር።
በሌላ በኩል አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፤ "ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ ማምረት፣ ለገበያ ማቅረብ፣ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፣ መሸጥ፣ ማከማቸት ወይም መጠቀም የተከለከለ ነው" የሚል ድንጋጌ ተካትቶበታል።
ነገር ግን ይህ ድንጋጌ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በተመረተ፣ ወደ አገር ውስጥ በገባ፣ ለመግባት በሂደት ላይ ባለ ፕላስቲክ ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን አዋጁ ያትታል። በረቂቅ አዋጁ መሠረት "ይህ ልዩ ሁኔታ ተፈጻሚ የሚሆነው ይህ አዋጅ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ወር ብቻ ነው።"
የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክን የተመለከቱ አዋጁ ድንጋጌዎች አፈጻጸምን መቆጣጠር እና፣ ጥሰት ሲኖር "ተገቢ የእርምት እርምጃ" የመውሰድ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
ከዚህ በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ "ባለሥልጣኑ አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮች እንዲመረቱ፣ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ወይም ጥቅም ላይ እንዲውሉ በመመሪያ ሊወስን ይችላል" ይላል።
በረቂቅ አዋጁ ባለሥልጣኑ ይህን ውሳኔ ሊወስን የሚችለው "ፕላስቲክ ማሸጊያው በቀላሉ በሌላ ምርት የማይተካ መሆኑ እና ፕላስቲኩ ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል መሆኑ ሲረጋገጥ ነው" የሚል ድንጋጌ ተካትቷል።
አዋጁ ላይ የተካተተው ሌላኛው ጉዳይ የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ እና አወጋገድ ጉዳይ ነው።
በረቂቅ አዋጁ መሠረት "ማንኛውም ሰው ከመኖሪያ ቤት ይዞታው ድንበር አንስቶ ቢያንስ እስከ ሀያ ሜትር ባለው ርቀት ውስጥ ደረቅ ቆሻሻን የማጽዳት ኃላፊነት አለበት።"
የአገልግሎት መስጫ እና የንግድ ተቋማት ደግሞ እስከ ሃምሳ ሜትር ርቅት ውስጥ ደረቅ ቆሻሻን የማጽዳት ኃላፊነት በረቂቁ ተጥሎባቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአንድ ወር ገደማ በፊት በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለውን ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራን በገመገሙበት ወቅት የፕላስቲክ ጉዳይን አንስተው ነበር።
በዚህ ግምገማ የፌደራል መንግሥት ፕላስቲክን በተመለከተ ሕግ እያዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፕላስቲኮች "ወደ አገር ውስጥ የማይገቡበትን መንገድ ለመፍጠር እንሞክራለን" ብለው ነበር።
ጠ/ሚ ዐቢይ በአዲስ አበባ ከተማ በሚታይ ሁኔታ መንገዶች ላይ የሚሠሩ የፕላስቲክ ቤቶች እና የፕላስቲክ በረንዳዎች መከልከል እንዳለባቸው ገልጸውም ነበር።
"ማንም ሰው በቤቱ በረንዳ ላይም ይሁን ቡና ለመሸጥ በፕላስቲክ የሚሠራ ቤት ሕገ ወጥ መሆን አለበት። መጀመሪያ ላስቲክ ነው፣ ቀጥሎ ነው ሕጋዊ ቤት የሚመስለው። ግን ፕላስቲክ የሚባል መፈቀድ የለበትም" ሲሉ ተናግረዋል።