ሲሳደቡ እና ዕፅ ሲጠቀሙ ታይተዋል የተባሉት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዳኛ ከሥራቸው ተባረሩ

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዳኛ የነበሩት ዴቪድ ኩት "ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ" ከሥራቸው መሰናበታቸውን የዳኞች ማኅበር አስታወቀ።

የ42 ዓመቱ ኩት ከሁለት ወር ገደማ በፊት የቀድሞው የሊቨርፑል አሠልጣኝ የነበሩት ዩርገን ክሎፕን ሲዘልፉ የሚያሳይ ቪድዮ በማኅበራዊ ሚድያ መለቀቁን ተከትሎ ፒጂኤምኦኤል የተባለው የዳኞች ማኅበር ከሥራቸው በጊዜያዊነት አሰናብቷቸው ነበር።

ይህ ክስ ከቀረበባቸው ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ ባለፈው ዓመት በተደረገው የአውሮፓ ዋንጫ ሰሞን ነጭ ዱቄት በአፍንጫቸው ሲስቡ የሚያሳይ ቪድዮ 'ዘ ሰን' የተባለው ጋዜጣ ማውጣቱ ይታወሳል።

እነዚህን ቪድዮዎች ተከትሎ የእግር ኳስ ዳኞች ማኅበር ዳኛውን ከሥራ አግዶ ምርመራ ሲያደርግባቸው ቆይቷል።

የዳኞች ማኅበር የዴቪድ ኩት ተግባር "ልንከራከርለት" የምንችለው አይደለም ብሏል።

የፕሪሚዬር ሊጉ ዳኛ ፈጽመውታል የተባሉ ነገሮችን የሚያሳዩትን ይፋ የተደረጉ ቪድዮዎች እና ፎቶዎችን ቢቢሲ በግሉ ማጣራት አልቻለም።

"የደቪድ ኩት ተግባር የሥራ ኮንትራቱን የሚጥስ ነው" ሲል ማኅበሩ በመግለጫው አስታውቆ፣ ዳኛውን ለመርዳት የተቻለውን እንደሚያደርግ ይፋ አድርጓል።

ኩት ከሥራቸው እንዲታገዱ የተወሰነባቸውን ውሳኔ ይግባኝ ማለት ይችላሉ።

ምርመራ በከፈተበት ቪድዮ ላይ ዳኛው ከአንድ ግለሰብ ጋር ተቀምጠው ክሎፕን "ግልፍተኛ ናቸው" ያሏቸው ሲሆን፣ በተደጋጋሚ በጸያፍ ቃላት ሲሰድቧቸውም ይሰማል።

በአውሮፓውያኑ 2020 ሊቨርፑል ከበርንሊ ጋር በነበረው ጨዋታ 1 አቻ ተለያይቷል። አንዲ ሮበርትሰን ለሊቨርፑል ቀድሞ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑ መሪነቱን እንዲቆጣጠር ቢያስችልም በርንሊ በጄይ ሮድሪጉዌዝ ጎል አቻ ማድረግ ችሏል። ሊቨርፑል ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር 3 ነጥብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት አልተሳካም።

ከተጠናቀቀ በኋላ የመሐል ዳኛው ዴቪድ ኩት እና በወቅቱ የሊቨርፑል አሠልጣኝ የነበሩት ክሎፕ የቃላት ምልልስ ሲያደርጉ ታይተዋል።

የ42 ዓመቱ ኩት ለመጨረሻ ጊዜ የዳኙት ከሳምንታት በፊት ሊቨርፑል አስተን ቪላን 2-0 ሲረታ ነው። በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አሉ ከሚባሉ እና ልምድ ካላቸው ዳኞች መካከል ሲሆኑ፣ ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ የፕሪሚዬር ሊጉ ዳኛ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዳኞች የትኛውን ክለብ እንደሚደግፉ ለዳኛው አስተዳዳሪው ማኅበር የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው።

ኖቲንግሀም ከተባለው ሥፍራ የመጡት ዴቪድ ኩት ኖትስ ካውንቲ የተባለው ቡድን ደጋፊ ሲሆኑ፣ የኖትስ እንዲሁም በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወተው ኖቲንግሀም ፎረስት ጨዋታዎችን መዳኘት አይችሉም።