ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አቡነ ባሲሊዮስ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ሆነው ተመረጡ
አቡነ ባሲሊዮስ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ስድስተኛ ፓትርያክ ሆነው መሾማቸውን ቤተክርስትያኗ በመግለጫ አስታወቀች።
ሰኞ ዕለት በኤርትራ መዲና አስመራ በሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ በተደረገ ምርጫ አቡነ ባሲሊዮስ ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት ፓትርያርክ ሆነው መመረጣቸው ታውቋል።
ሶስት ጳጳሳት የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ለመሆን ዕጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን 85 የሲኖዶሱ አባላት ድምፅ ሰጥተዋል።
በአሌግዛንድሪያው ፓትርያርክ ቴዎድሮስ ሁለተኛ የተመራ የግብፅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካዮች ቡድን ምርጫውን በአካል ተገኝቶ መታዘቡ ተሰምቷል።
አቡነ ባሲሊዮስ በአውሮፓውያኑ ጥር 25፤ 2025 በይፋ ሥራቸውን ይጀምራሉ።
የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን በውስጣዊ መከፋፈል እና በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ምክንያት ፈተና ላይ እንደሆነች ይነገራል።
ከአውሮፓውያኑ 2006 ጀምሮ ፓትርያርክ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቡነ አንቶኒዮስ በ2019 በኤርትራ ጳጳሳት ከመንበራቸው መሰናበታቸው ይታወሳል።
አቡነ አንቶኒዮስ ለ15 ዓመታት ያክል በቤት ውስጥ እስር ከቆዩ በኋላ የካቲት 2022 ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው አይዘነጋም።
በርካታ የቤተክርስትያኗ አባላት አቡኑ ከመንበራቸው የተነሱት የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት በመተቸታቸው ነው ብለው ያምናሉ።
አቡነ አንቶኒዮስ ከመንበራቸው ከተነሱ በኋላ ቤተክርስትያኗ ለዓመታት ያለ ፓትርያርክ ቆይታ ነበር።
አምስተኛው ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስ በ2021 ተሹመው ታኅሣሥ 2022 በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ሀገር ውስጥ ባለው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ምክንያት የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በተለይ በዳያስፖራው ዘንድ ብዙ መከፋፈል ገጥሟታል።
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ከመንበራቸው የተነሱት ፓትርያርክ ተከታዮች የራሳቸውን ቤተክርስትያን አቋቁመዋል።
የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በኤርትራ በይፋ መሥራት ከሚፈቀድላቸው አራት የእምነት ተቋማት መካከል አንዷ ናት። ኢቫንጀሊካል ሉተራን ቤተክርስትያን፣ ሱኒ ኢስላም እና ካቶሊክ ቤተክርስትያን ሌሎቹ የእምነት ተቋማት ናቸው።
ሌሎቹ አነስተኛ ተከታይ ያላቸው የእምነት ተቋማት እና ተከታዮቻቸው እስር እና መንገላታት እንደሚደርስባቸው የሰብዓዊ መብት ተቋማት ይናገራሉ።
የኤርትራ መንግሥት ሌሎች የእምነት ተቋማት የውጭ ሀገራትን ሥራ ለማስፈፀም የተቋቋሙ ናቸው ብሎ ያምናል።
የአስመራ መንግሥት ተቺዎች የፕሬዝደንት ኢሳያስ አገዛዝ ጭቆና የተሞላበት ነው ሲሉ ቢተቹም ደጋፊዎች በበኩላቸው ይህ ከእውነት የራቀ ነው ይላሉ።