“በፕላስቲክ የሚሠራ ቤት ሕገ ወጥ መሆን አለበት” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ “በሚታይ ሁኔታ” መንገዶች ላይ የሚሠሩ የፕላስቲክ ቤቶች እና የፕላስቲክ በረንዳዎች መከልከል እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ክፍለ ከተማ እና ወረዳዎች “ነገ፣ ከነገ ወዲያ የኮሪደር ልማት እንደሚመጣ አውቀው” ዝግጅት እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ሌሎች ከፍተኛ ዑከተማዋ አመራሮች እነዚህን ትዕዛዞች የሰጡት ከትናንት በስቲያ ረቡዕ፣ ኅዳር 4/2017 ዓ.ም. በመዲናዋ እየተገነባ ያለውን ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በገመገሙበት ወቅት ነው።

ትናንት ምሽት፣ ኅዳር 5/2017 ዓ.ም. በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተላለፈው ይህ ግምገማ ከንቲባ አዳነችን እና የኮሪደር ልማቱን የሚያስፈፅሙ የከተማዋ አመራሮች የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡበት ነው።

በስምንት መስመሮች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት በድምሩ 2,879 ሄክታር ቦታን የሚሸፍን እና 135 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው እንደሆነ ከንቲባ አዳነች አስረድተዋል።

በግምገማው ላይ ሪፖርት ያቀረቡት የከተማዋ አመራሮች በሚከታተሏቸው የኮሪደር መስመሮች ላይ የጠቀሷቸው የተነሺዎች ብዛት በድምሩ ቢያንስ ከ6,500 በላይ ባለይዞታዎች እንደሚሆኑ ያመለክታል።

በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ለሚነሱ ባለይዞታዎች የተገመተው አጠቃላይ የካሳ መጠን 11.9 ቢሊዮን ብር እንደሆነ በሪፖርታቸው ላይ የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ እስካሁን ድረስ የአምስት ቢሊዮን ብር ካሳ እንደተፈጸመ አስታውቀዋል።

እንደ አዳነች ገለጻ ለተነሺዎች የተዘጋጀው የመኖሪያ እና መሥሪያ ምትክ መሬት 100 ሄክታር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ለተነሺዎች ተላልፏል።

ከአራት ሺህ በላይ ቤቶችም ለተነሺዎች እንደተሰጡ ተጠቅሷል። ይሁንና በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የቤቶች እጥረት በማጋጠሙ ነዋሪዎች በተፈለገው ፍጥነት እንዳልተነሱ ሪፖርት ባቀረቡ ሌሎች የከተማዋ አመራሮች ተጠቅሷል።

አንድ ሰዓት ገደማ ከፈጀው የከተማዋ አመራሮች ሪፖርት በኋላ ማጠቃለያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ናቸው። ዐቢይ፤ 40 ደቂቃ ገደማ የወሰደውን ንግግራቸውን የጀመሩት በከተማዋ እየተከናወነ ስላለው የኮሪደር ልማት የሚሰጡ አስተያየቶችን በማንሳት ነው።

“የሀገር ግንባታ” በሂደቱ ወቅት የሚኖሩ ሰዎች “በቀላሉ ተቀብለው፣ ተስማምተው የሚሄዱበት ጉዳይ” እንዳልሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን የሚሠራውን ሥራ የሚያደንቁ ሰዎች የሚመጡት ከተማው የተገነባለት “ትውልድ ሲነሳ” መሆኑን አስረድተዋል።

“ሀገራቸውን የሚወዱ፣ ስለ ሀገራቸው ጥሩ የሚናገሩ፣ ሀገራቸውን በከፍተኛ ደረጃ የሚያስተዋውቁ ትውልዶች የሚፈጠሩት የገነባንለት ትውልድ ሲነሳ ነው። የምንገነባው ለትውልድ ከሆነ፤ ያ የገነባንለት ትውልድ ሲነሳ ተመሳሳይ ቋንቋ እንሰማለን” ሲሉ በግምገማው ላይ ለተገኙት የከተማዋ አመራሮች አብራርተዋል።

አክለውም የከተማ መሠረተ ልማትን ከማከናወን ባሻገር “ለከተማ የሚመጥን ትውልድ መሥራት” እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በከተማዋ የተገነቡ መሠረት ልማቶች አጠቃቀም እና አጠባበቅ ላይ “በከፍተኛ ደረጃ ክፍተት” መታየቱን ጠቅሰዋል።

“ሳር እየረገጠ የሚሄድ፣ በሳይክል መስመር ላይ በእግሩ የሚጓዝ፣ የእግረኛ መንገድ እያለ አስፓልት ላይ የሚጓዝ በጣም በርካታ ሰው አለ። ይህንን አስተሳሰብ እየቀየርን ለከተማው የሚመጥን ትውልድ ማድረግ ሁለተኛ ሥራችን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ያለው እንደ ሌሎች ሀገራት “ነዳጅ ሳይወጣ እና ከፍተኛ የውጭ ሀብት ሳይፈስ” መሆኑን ያስረዱት ዐቢይ፤ ግንባታ የሚከናወነው “ወደ ውጭ ይሸሽ የነበረን ሀብት በማስቀረት” እና የሀገር ውስጥ አቅምን በመጠቀም መሆኑን ገልጸዋል።

“ከፍተኛ የሀብት ውስንነት አለብን። አድቫንቴጁ [ጥቅሙ] በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት፤ የእኛ ሀብት መንግሥታዊ ሙስና ስለሌለ ገንዘብ አይሸሽም። አዲስ ገንዘብ የለንም ፤ ይሄ ሁሉ ሥራ የሚሠራው ወደ ውጭ ይሸሽ የነበረውን ገንዘብ ማስቀረት ስለቻልን ነው። 100 ፐርሰንት ግን አይደለም አሁንም በግራ በቀኝ የሚሾልኩ ይኖራሉ” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኮሪደር ልማቱ ጋር በተያያዘ ከተማ ውስጥ “መስተካከል አለባቸው” ያሏቸው ጉዳዮች አንስተው ግምገማው ላይ ለተገኙት የከተማ አመራሮች መመሪያ ሰጥተዋል። ከእነዚህም ውስጥ አንደኛው የፕላስቲክ አጠቃቀምን የሚመለከት ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነዋሪዎች በፕላስቲክ ቤት እና በረንዳ እንደሚሠሩ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገር ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮች “ውሃ፣ ከተማ፣ የአኗኗር ዘዬ እያበላሸ” እና “በሽታ እያመጣ” መሆኑን ገልጸዋል።

“ማንም ሰው በቤቱ በረንዳ ላይም ይሁን ቡና ለመሸጥ በፕላስቲክ የሚሠራ ቤት ሕገ ወጥ መሆን አለበት። መጀመሪያ ላስቲክ ነው፣ ቀጥሎ ነው ህጋዊ ቤት የሚመስለው። ግን ፕላስቲክ የሚባል መፈቀድ የለበትም” ሲሉ ለከተማዋ አመራሮች አሳስበዋል።

የፌደራል መንግሥት ፕላስቲክን በተመለከተ ሕግ እያዘጋጀ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፕላስቲኮች “ወደ ሀገር ውስጥ የማይገቡበትን መንገድ [ለመፍጠር] እንሞክራለን” ብለዋል።

“ሰው እያመጣ ላስቲኩን እዚህ ዳምፕ [እንዲጥል] እንዲያደርግ መፍቀድ የለብንም። በሀገር ደረጃ የሚወጣው ሕግ እንዳለ ሆኖ በአዲስ አበባ ግን ቢያንስ በሚታይ መንገድ ላስቲክ የሚሠሩ በረንዳዎች መከልከል አለበት። ከፈለገ በሳር ይሥራ” ሲሉ ለከተማዋ አመራሮች ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

በከተማዋ ውስጥ የሚታየው የሳተላይት “ዲሽ” ሳህን አጠቃቀምም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነሳ ሌላኛው ጉዳይ ነው።

አዲስ አበባ ውስጥ “በየቦታው ዲሽ መከመሩን” ያነሱት ጠ/ሚ ዐቢይ፤ ብዙ የ“ዲሽ” ሳህን መኖሩ “ተጨማሪ ኢነርጂ፣ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ እና ኪሳራ” መሆኑን እና “ከፍተኛ የሀብት ውድመት” እንደሚያስከትል አስረድተዋል።

በአንድ የ“ዲሽ” ሳህን “20፣ 30” ቤቶች የሚጠቀሙበት አሠራር በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የተለመደ መሆኑን ጠቅሰውም ይህ ተግባር “ስታንዳርድ ሆኖ” ተግባራዊ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

“ኮንዶሚኒየም አካባቢ አንድ ዲሽ አድርጎ ለሁሉም መጠቀምን ስታንዳርድ ማድረግ ነው። ‘[የዲሽ ሳህን] መለጠፍ አይቻልም፣ ሽቦ መቀጠል አይቻልም’ ተብሎ እሱን ስታንዳርድ ማድረግ ነው” ሲሉ የከተማ አስተዳደሩ ይህንን ማስፈጸም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ሆስፒታል፣ የጋራ መኖሪያ አካባቢዎች እና ዩኒቨርስቲዎች የሚኖራቸው የመፀዳጃ ቤት እና የሌሎች ፍሳሾች አወጋገድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነሳ ሌላኛው ጉዳይ ነው።

ከእነዚህ ተቋማት እና የመኖሪያ መንደሮች የሚወጣው ፍሳሽ በባዮ ጋዝ ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል መቀየር እንዳለበት ተናግረዋል።

“በሆስፒታል፣ ኮንዶሚኒየም አካባቢ፣ ዩኒቨርስቲዎች እነዚህ ሰብሰብ፣ ሰብሰብ ያለ ሰው ያለበት አካባቢ ባዮ ጋዝ መገንባት ግዴታ ይሁን” ያሉት ዐቢይ፤ የከተማ አስተዳደር አመራሮች ይህንን እና የፕላስቲክ ጉዳይን “በሕግ እንዲሄዱበት” አዝዘዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለከተማዋ አመራሮች ያስተላለፉት ሌላኛው መመሪያ በከተማዋ “ወጣ” ያሉ አካባቢዎች እየተገነቡ ነው ያሏቸው “ሕገ ወጥ ቤቶችን” የተመለከተ ነው።

ግንባታ እየተከናወነ ባለባቸው የኮሪደር መስመሮች ላይ የነበሩ “ሕገ ወጥ” ቤት የገነቡ ሰዎች እንዲነሱ ሲደረጉ “አዲስ ስፍራ የሚሰፍሩ ከሆነ ሌላ ጣጣ ነው” ብለዋል።

“ሁሉም ክፍለ ከተማ፣ ሁሉም ወረዳ ኮሪደር ነገ ከነገ ወዲያ እንደሚመጣ አውቆ ከአሁኑ የቤት ልየታ፣ ከአሁኑ የሕገ ወጥ ልየታ ማድረግ አለበት” ሲሉ ወረዳዎች “አሁኑኑ” የሕጋዊ እና የሕገወጥ ቤቶችን ቁጥር መለየት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

“ተጨማሪ ሕገ ወጥ ቤቶች እንዳይቀጣጠል ከአሁኑ ካልተሠራ ይህንን ጨርሳችሁ ስትሄዱ ሌላ ጣጣ ነው የሚሆነው። ወረዳዎች እና ክፍለ ከተሞች የልየታ ሥራ አሁኑኑ እንዲሠሩ ቢደረግ ጥሩ ነው” ሲሉ በግምገማው ላይ ለተሳተፉት የከተማዋ አመራሮች ትዕዛዝ ሰጥተዋል።