በአሜሪካዋ ኒው ጀርዚ ሰማይ ላይ ሲበሩ የታዩት ሚስጢራዊ ድሮኖች የማን ናቸው? ስለድሮኖቹ ምን እናውቃለን?

በአሜሪካዋ ኒው ጀርዚ ግዛት ሲበሩ የታዩት ድሮኖች ጉዳይ አንድ ወር ቢሞላውም አሁንም መነጋገሪያነቱ ቀጥሏል።

ነዋሪዎች ፍርሀት ገብቷቸዋል። ሰማይ ላይ የታዩት ምንድን ናቸው? ድሮኖች ናቸው? የሚለው ጥያቄ አከራካሪ ሆኗል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት በራሪዎቹ ቁሶች ለሕዝቡም ሆነ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አስጊ አይደሉም ከማለት ውጭ ቁርጥ ያለ መልስ ሊሰጡ አልቻሉም።

ባለፈው ሐሙስ የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ድሮኖች ናቸው ተብለው ሰማይ ላይ ሲበሩ የታዩት አብዛኛዎቹ አውሮፕላኖች ናቸው ብለዋል።

ነገር ግን አንዳንድ ፖለቲከኞች መንግሥት ድሮኖቹን በተለመከተ በቂ መረጃ ለሕዝቡ አልሰጠም ሲሉ ይወቅሳሉ።

እነሆ ስለበራሪዎቹ ቁሶች እስካሁን የምናውቀው።

ድሮኖቹ የት የት ታዩ?

ከአውሮፓውያኑ ኅዳር 18 ጀምሮ ጅምላ የሚሆኑ ድሮኖች በኒው ጀርዚ ታይተዋል መባላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ገልፀዋል።

ድሮኖቹ መጀመሪያ የታዩት ራሪታን የተባለው ወንዝ አካባቢ መሆኑን አሶሲየትድ ፕረስ ዘግቧል። ይህ ወንዝ ወደ ራውንድ ቫሊ ውሀ ማቆሪያ የሚፈስ ነው።

ቀጥሎ የኒው ጀርዚ የባሕር ጠረፍን ጨምሮ በተለያዩ የግዛቲቱ ክፍሎች ታይተዋል መባላቸው ተሰማ።

በራሪዎቹ ቁሶች ፒካቲኒ አርሰናል የተባለው ካምፕ አካባቢም መታየታቸው ተዘግቧል። ይህ ሥፍራ ሚስጢራዊ ወታደራዊ ጥናት የሚደረግበት ነው።

ድሮኖቹ በኒው ጀርዚዋ ቤድሚኒስትር ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የጎልፍ መጫወቻ ክለብ አቅራቢያም ታይተዋል ተብሏል።

ታኅሣሥ 12 ደግሞ የኒው ጀርዚ አጎራባች በሆነችው ኒው ዮርክ ከተማ ብሮንክስ በተባለው ሥፍራ በርካታ ድሮኖች መታየታቸውን አንድ የፖሊስ ኃላፊ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ተናግረዋል።

ድሮኖች ታይተዋል በተባሉባቸው ሥፍራዎች የተገኙት የፖሊስ መኮንኖች እነሱም በራሪ ቁሶች ማየታቸውን ተናግረው ነገር ግን ከደቂቃዎች በኋላ ድሮኖቹ መሰወራቸውን አሳውቀዋል።

የኒው ዮርክ ግዛት ፖሊስ እንዳስታወቀው ድሮኖች ታዩ የተባሉት በኒው ዮርክ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የግዛቲቱ አካባቢዎችም ጭምር ነው።

የኮኔቲከት ግዛት ፖሊስ በተለያዩ አካባቢዎች "አጠራጣሪ ድሮኖች" መታየታቸውን አስታውቋል። በግሮተን እና ኒው ለንደን ከተማዎች የድሮኖችን እንቅስቃሴ የሚከታተል ቴክኖሎጂ ተገጥሟል።

በሜሪላንድ ደግሞ የቀድሞው ሪፐብሊካን ሀገረ ገዥ ላሪ ሆገን ከዋሺንግተን ዲሲ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ "ድሮኖች የሚመስሉ" በራሪዎች ማየታቸውን ተናግረዋል።

"እንደ አብዛኛዎቻችሁ ሰማይ የምናያቸው በራሪዎች ለሕዝቡም ሆነ ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ስለመሆናቸው የማውቀው ነገር የለም" ሲል በኤክስ ገፃቸው ፅፈዋል።

ባለፈው ኅዳር የዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል ዩናይትድ ኪንግደም በሚገኙ ሶስት ጣቢያዎቹ አካባቢ ምንነታቸው ያልታወቀ ድሮኖች መታየታቸውን አስታውቆ ነበር።

በጥቅምት ወር ደግሞ ምስጢራዊ ድሮኖች ቨርጂኒያ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎች አቅራቢያ ለ17 ቀናት መታየታቸውን ዎል ስትሪት ጆርናል አስነብቧል።

ምርመራዎች ስለድሮኖቹ ምን ይላሉ?

የአሜሪካ የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ድሮኖቹ የውጭ ኃይል ንብረት አይደሉም፤ ብሔራዊ ደኅንነታችንም ላይ ስጋት አይፈጥሩም ሲሉ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ጠይቀዋል።

አንድ የኤፍቢአይ ኃላፊ "ትንሽ የተጋነነ ነገር ያለ ይመስለኛል" ብለዋል።

ምንም እንኳ ኃላፊዎቹ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ቢጠይቁም የድሮኖቹን ምንነት ለማወቅ ምርመራ እያደረጉ እንደሆነ ግን አስታውቀዋል።

"ሰዎች ለምን ስጋት ውስጥ እንደገቡ እንረዳለን። ለዚህ ነው አቅማችንን አሟጠን ምርመራ እያደረግን ያለነው" ሲል ሆምላንድ ሴኪዩሪቲ የተባለው የደኅንነት መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

መሥሪያ ቤቱ አክሎ "ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ለሕዝቡ ስጋት የሚሆን ምንም ነገር የለም" ብሏል።

በራሪዎቹ ቁሶች ምንድን ናቸው?

የኒው ጀርዚዋ ፖለቲከኛ ዶውን ፋንቴዢያ ከሆምላንድ ሴኪዩሪቲ መግለጫ ከተሰጣቸው በኋላ ድሮኖቹ በሄሊኮፕተር እና በራዲዮ ምርመራ ሊደርግባቸው አልቻለም ሲሉ ተደምጠዋል።

ፋንቴዢያ አክለው ድሮኖቹ 1.8 ሜትር ስፋት ያላቸው፤ መብራታቸውን አጥፍተው የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም "በጣም በተቀናጀ መንገድ የሚበሩ" ናቸው ብለዋል።

ዋይት ሐውስ ግን በተቃራኒው ድሮን ናቸው ተብለው የተዘገቡት በራሪዎች "አነስተኛ በሰው የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖች" ናቸው ብሏል።

ኤፍቢአይ እና ሆምላንድ ሴኪዩሪቲም እንዲሁ አብዛኛዎቹ ድሮን ናቸው ተብሎ የታዩ በራሪዎች በሕጋዊ መንገድ የሚበሩ ሰው አልባ ያለሆኑ አውሮፕላኖች ናቸው ይላሉ።

ሁለቱ መሥሪያ ቤቶች ባወጡት መግለጫ እስካሁን በተከለከለ የአየር ክልል ላይ የበረሩ እንደሌሉ አስታውቀዋል።

የፌዴራል አቪዬሽን ባለሥልጣን አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ በርካታ ሰዎች ድሮን እየተጠቀሙ ስለሆነ ነው ሰዎች አየናቸው እያሉ ያሉት ብሏል።

ባለሥልጣኑ አክሎ ድሮኖች ከ400 ጫማ በታች (121 ሜትር) መብረር እንዲችሉ ቢፈቀድላቸውም ከመሥሪያ ቤቱ ፈቃድ ውጭ በተከለከሉ የአየር ክልሎች አሊያም በአየር ማረፊያዎች አቅራቢያ መብረር እንደማይችሉ አስታውቋል።

ድሮኖቹ ከየት መጡ?

በራሪዎቹ ቁሶች ድሮኖች መሆናቸው እስካሁን አልተረጋገጠም። እኒህን ሚስጢራዊ ድሮኖች እያበረረ ያለው ማን እንደሆነም እስካሁን አልታወቀም።

የአሜሪካ ኮንግረስ አባል የሆኑት ሪፐብሊካኑ ጄፍ ዳን ድሩ "ከፍተኛ አመኔታ ካላቸው" ምንጮቼ ሰማሁ ብለው ድሮኖቹ ከኢራን ጋር ግንኘነት እንዳላቸው ተናግረው ነበር።

የኒው ጀርዚው ሪፐብሊካን ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ድሮኖች አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ከሚገኝ የኢራን የጦር አውሮፕላን የተነሱ ናቸው ብለዋል።

"መርከቧ የምትገኘው በዩናይትድ ስቴትስ ምስራቃዊ ጠረፍ አካባቢ ነው። ወደ ምናየው እና የምንሰማው ነገር ሁሉ ድሮኖች ለቀዋል" ሲሉ የኮንግረስ አባሉ ረቡዕ ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።

"ከፍተኛ አመኔታ ካላቸው ምንጮቼ ያገኘሁት መረጃ ነው። በቀላሉ የምወስደው ጉዳይ አይደለም።"

አክለው አሜሪካ ድሮኖቹ ተኩሳ እንድትጥላቸው ምክረ ሐሳብ ሰጥተዋል።

የኢሊኖይ ተወካዩ ዲሞክራት ራጃ ክሪሽናሙርቲ በበኩላቸው ኒውስኔሽን ለተባለው ጣቢያ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ቻይና ሳትኖርበት አትቀርም የሚል ጥርጣሬ እንዳለቸው ተናግረዋል።

"እኒህን ድሮኖች ተጠቅመው መረጃ ሊሰበስቡ እንደሚችሉ ከፍተኛ ጥርጣሬ አለ" ብለዋል።

ፔንታገን እና ዋይት ሐውስ ግን የውጭ ሀገራት ከበራሪዎቹ ቁሶች ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ነገር የለም ይላሉ።

በተያያዘ ዜና አንድ የሰሜናዊ ካሊፎርኒያ ነዋሪ ታኅሣሥ 11 ቫንደርበርግ ስፔስ ፎርስ ቤዝ በተባለው ሳንታ ባርብራ በሚገኘው ጣቢያ አቅራቢያ ድሮን አብርሯል እንዲሁም ፎቶ አንስቷል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

ተጠርጣሪው ድሮን ያበረረው ኅዳር 30 መሆኑን አቃቤ ሕግ አስታውቋል።

ግለሰቡ የ39 ዓመት ቻይናዊ ይንፒያዎ ዡ ወደ ቻይና አውሮፕላን ሊሳፈር ሲል በቁጥጥር ሥር ውሏል። ባለፈው ሐሙስ ፍርድ ቤት መቅረቡም ተሰምቷል።

ግለሰቡ ያበረረው ድሮን በመላ ሀገሪቱ ታዩ ከተባሉት በራሪ ቁሶች ጋር ግንኙነት ያለው እንደሆነ የሚጠቁም ነገር አልተገኘም።

ድሮኖቹን ማስቆም ይቻላል?

በርካታ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ድሮኖች ተመትተው እንዲወድቁ እና ዓላማቸው ምን እንደሆነ ምርመራ እንዲደርግባቸው ጠይቀዋል።

ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያቸው ድሮኖቹ ያለ መንግሥት ዕውቅና ሊበሩ አይችሉም ብለዋል።

"ሕዝቡ አሁኑኑ እውነታው እንዲያውቅ ይደረግ" ያሉት ትራምፕ "ካልሆነ ደግሞ ተመትተው ይጣሉ" የሚል ሐሳብ አቅርበዋል።

የፌዴራል አቪዬሽን ባለሥልጣን በቤድሚኒስትር እና ፒካቲኒ አካባቢ ድሮኖች እንዳይበሩ ጊዜያዊ ዕገዳ ጥሏል።

ባለሥልኑ በመግለጫው ደኅንነቱ ባልተጠበቀ እና አደገኛ በሆነ መንገድ ድሮን የሚያበሩ ግለሰቦች እስከ 75 ሺህ ዶላር የሚደርስ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው እንዲሁም የድሮን ማብረር ፈቃዳቸው እንደሚሰረዝ ገልጿል።

አንዳንድ ነዋሪዎች ደግሞ ድሮኖቹን ለመጣል በራሳቸው መንገድ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል። ባለሥልጣናት ግን ይህ ሕጋዊ ያልሆነ ተግባር ስለሆነ ዜጎች ከዚህ ድርጊት እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።

"አንድ ደኅና ክላሽ ይህንን ችግር ይቀርፈው ነበር" ሲል አንድ ግለሰብ በማኅበራዊ ሚድያ ገፁ ፅፏል።