በአሜሪካ ተማሪዎች 400 ‘ፑሽ አፕ’ እንዲሰሩ በመገደዳቸው ለህመም ተዳረጉ

የፎቶው ባለመብት, CBS News
በአሜሪካ ቴክሳስ ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት የስፖርት ቡድን አባላት የሆኑ ተማሪዎች ከባድ አካላዊ ስፖርት እንዲሰሩ በመገደዳቸው ምክንያት ህክምና እንዳስፈለጋቸው ወላጆች ተናገሩ።
በሮክዎል ሔዝ ትምህርት ቤት የአሜሪካ እግር ኳስ ቡድን አባላት የሆኑት ተማሪዎች ከባድ ስፖርት እንዲሰሩ በመደረጋቸው አካላዊ ጉዳት አጋጥሟቸው ለህክምና ድጋፍ ወደ ሐኪም ዘንድ በመወሰዳቸው ወላጆች የልጆቻቸው አያያዝ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ ምንም እረፍት ሳያደርጉ ወደ 400 ጊዜ የሚጠጋ ፑሽ አፕ እንዲሰሩ መገደዳቸውን፣ የአንደኛው ተማሪ ወላጅ የሆኑት ዶ/ር ኦሴሆቱ ኦኮጂ ተናግረዋል።
እናት ስለክስተቱ ሲናገሩ “ይህ ክስተት የሳምንቱ አስደንጋጭ ሁኔታ ነበር”ሲሉ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።
ይህንን ክስተት ተከትሎም የትምህርት ቤቱ እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ጆን ሃሬል የግዳጅ እረፍት እንዲወጣ ተደርጓል።
ቴክሳስ ግዛት ውስጥ በሚገኘው የሮክዎል ሔዝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ከባዱን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስፖርት እንዲሰሩ ከተገደዱት ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ ወደ ሆስፒታል ሄደዋል።
ተማሪዎቹ የሰሩት ከባድ ስፖርት በጡንቻቸው ላይ ከባድ ህመምን በማስከተል ለመንቀሳቀስ ተቸግረው እንደነበር ወላጆች ተናግረዋል።
በከባዱ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የተነሳ በልጃቸው የጡንቻ ህዋሳት ላይ ጉዳት መድረሱን ከሐኪሞች የተረዱት የአንደኛው ተማሪ እናት፣ ልጃቸው ለአንድ ሳምንት ሆስፒታል ለመቆየት መገደዱን ተናግረዋል።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ቶድ ብራድፎርድ ጉዳዩን በሚመለከት በትዊተር ላይ ለወላጆች ባስተላለፉት መልዕክት፣ በርካታ ወላጆች ልጆቻቸው “በርካታ ፑሽ አፕ እንዲሰሩ በመደረጋቸው” የህክምና ድጋፍ እንዳስፈለጋቸው ሪፖርት ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል።
ትምህርት ቤቱ ጉዳዩን በሚመለከት ገለልተኛ ሦስተኛ ወገን ቀጥሮ ምርመራ እንደሚያስደርግና ውጤቱም እስኪታወቅ ድረስም የእግር ኳስ ቡድኑ አሰልጣኝ የግዳጅ እረፍት እንዲወጣ መደረጉ ተገልጿል።
በርካታ የተማሪዎቹ ወላጆች ልጆቻቸው እንዲሰሩ በተደረጉት ከባድ ስፖርት የተነሳ ከባድ የጡንቻ ህመም እንዳጋጠማቸው እና እጆቻቸውን ማንቀሳቀስ እንኳን እንደተሳናቸው ገልጸው፣ ይህ ሁኔታ ከአካላዊ ጉዳቱ ባሻገር በልጆቹ አእምሯዊ ጤና ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።












