መንግሥት እና ህወሓት በሦስተኛው ዙር ንግግር የደረሱበት ስምምነት ይዘት ምንድነው?

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት ተወካዮች መካከል በተደረገው ሦስተኛ ዙር ንግግር የሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ ጦር መሪዎች ከአንድ ወር በፊት በፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተገዢ በመሆን አፈጻጸሙን ለመቆጣጠር እና የአፈጻጸም መከታተያ ነጥቦች ላይ ከስምምነት ደርሰዋል።

በሁለቱ ወገን በኩል ያሉት የጦር አዛዦች ናይሮቢ ኬንያ ላይ ሲገናኙ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። የጦር መኮንኖቹ ናይሮቢ ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር ንግግር የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም ላይ ከስምምነት ደርሰው ነበረ።

ረቡዕ እና ሐሙስ ታኅሣሥ 12 እና 13/2015 ዓ.ም. ባደረጉት ንግግር ደግሞ የሰላም ስምምነት ተገዢ በመሆን የስምምነቱን አፈጻጸም በጋራ ለመቆጣጠር እና ለማረጋገጥ በሚያስችሉ የመከታተያ ነጥቦች ላይ ተስማምተዋል።

መንግሥት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ድርድር ካደረጉ በኋላ ግጭት በዘላቂነት ለማቆም፣ ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች ለማስጀመር፣ የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ ለማስፈታት እና የውጭ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።

ሐሙስ 13/2015 ዓ.ም. የጦር አዛዦቹ ዳግም ናይሮቢ ላይ ተገናኝተው የፕሮቶሪያ ስምምነት በጋራ ለመቆጣጠር እና ለማረጋገጥ የመከታተያ ነጥቦች ላይ ከስምምነት መድረሳቸውን ይፋ ያደረገው የእርሰ በርስ ጦርነቱ በንግግር እንዲፈታ ድርድሩን በበላይነት ሲመራ የቆየው የአፍሪካ ኅብረት ነው።

የስምምነቱ ይዘት ምንድነው?

ከፌደራል መንግሥቱ እና ከህወሓት የተወጣጡ አባላት ያሉበት ኮሚቴ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት የባለሙያዎች ቡድንን ያካተት የቁጥጥር፣ የማረጋገጫ እና ስምምነቱ መከበሩን የሚያረጋግጥ ሥርዓት እንዲኖር ከስምምነት ደርሰዋል።

ይህ የቁጥጥር፣ ማረጋገጥ እና ስምምነቱን የሚያረጋግጠው አካል ዋነኛ ዓላማ ፕሪቶሪያ ላይ የተደረሰው የሰላም ስምምነት በሁለቱም ወገኖች ስምምነቱ እየተፈጸመ መሆኑን ማረጋገጥ እና በየትኛውም ወገን ያልተተገበረ የስምምነት አካል ካለ ለእርማት ሪፖርት ማድረግ ነው።

በዚህ ቡድን ውስጥ መንግሥት እና ህወሓት፣ ድርድሩን ሲመራ የቆየው የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ቡድን እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ተቋም (ኢጋድ) እያንዳንዳቸው አንዳንድ ተወካዮች የሚኖራቸው ሲሆን የአፍሪካ ኅብረት ተወካዩ የቡድኑ ሊቀ መንበር ይሆናል።

የዚህ ቡድን ዋነኛ ዓላማ በደቡብ አፍሪካ እና በናይሮቢ የተፈረሙት ስምምነቶች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ድጋፍ ማድረግ ቀዳሚው ነው። በስምምነቱ ውስጥ የተመላከተው የፖለቲካ ንግግር በሁለቱ አካላት መካከል እንዲደረግ መሰረት መጣል የሚል ዓላማም አንግቧል።

የመንግሥት፣ የህወሓት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ ተወካዮችን እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት የባለሙያዎች ቡድን ያጣመረው ቡድን መንግሥት እና ህወሓት የደረሱትን የሰላም ስምምነት እንዲሁም የጦር መኮንኖቹ የተፈራረሙትን የአፈጻጸም ስምምነት የሚጥስ ተግባር በየአፍሪካ የባለሙያዎች ቡድን አማካይነት ሪፖርት ሲደረግ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ መፍትሄ ይሰጣል።

በሰላም ስምምነቱ መሠረት የህወሓት ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት ሂደት መጠናቀቁን እና የህወሓት ተዋጊዎች ዳግም የጦር መሳሪያ እና ተተኳሽ እንዳይዙ እና ያልተፈቀ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዳያደርጉ ማረጋገጥ፤ የህወሓት ተዋጊዎች የሚፈቱት ትጥቅ የሚቀመጠው የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በለያቸው ቦታዎች መሆኑን ማረጋገጥ የሚሉት ኃላፊነቶች ለዚህ ጥምር ቡድን ተሰጥተዋል።

የአፍሪካ የባለሙያዎች ቡድን

የመንግሥት፣ የህወሓት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ ተወካዮችን ያካተተው ጥምር ኮሚቴን የሚደግፍ ከ10 ያላነሱ አባላት ያሉት የአፍሪካ ባለሙያዎች ቡድን ይመደባሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከየአፍሪካ ባለሙያዎች ቡድን ጋር አብሮ የሚሰራ ባለሙያዎች ሊመድብ ይችላል።

በአፍሪካ ባለሙያዎች ቡድን ውስጥ የሚከተቱት ባለሙያዎች የጦር እውቀት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የኮሙኒኬሽን እና የግጭት አፈታት ክህሎት ያላቸው መሆን አለባቸው።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የአፍሪካ የባለሙያዎች ቡድን ዕጩ አባላት ዙሪያ ከመንግሥት እና ከህወሓት ጋር ይመክራል። ሁለቱ አካላት በ24 ሰዓታት ውስጥ በቀረቡት ዕጩ አባላት ዙሪያ ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል።

ይህ የባለሙያዎች ቡድን ወደ ሥራ ሲገባ ቀዳሚው ኃላፊነቱ በሰላም ስምምነቱ መሠረት ሁለቱ አካላት ተግባራዊ አፈጻጸማቸውን በተመለከተ መረጃ ማሰባሰብ፣ የመስክ ጉብኝቶችን በማድረግ የስምምነት ጥሰቶችን መመዝገብ፣ የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ አፈታትን በበላይን መከታተል ይገኙበታል።

የአፍሪካ የባለሙያዎች ቡድን የውጭ ኃይሎች እና ከአገር መከላከያ ኃይል አባላት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከትግራይ ክልል መውጣታቸውን ማረጋገጥ ሌላኛው የተሰጠው ኃላፊነት ነው።

መሠረታዊ አግልግሎቶች መጀመራቸውን እና የሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው መደረሱን ማረጋገጥ የሚለው ተጨማሪ ኃላፊነቱ ነው።

የአፍሪካ የባለሙያዎች ቡድን ለስድስት ወራት የሚቆይ ሲሆን ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት የሰው ኃይል፣ የሎጂስቲክስ እና የፋይናንስ ድጋፍ በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በኩል ይሰባሰባል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መቀለ

በሦስተኛው ዙር የናይሮቢው የጦር ሠራዊት አዛዦች ስብሰባ ላይ ዘላቂውን ግጭት የማስወገድ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ በዝርዝር ተነጋግረው ከስምምነት መድረሳቸው ተገልጿል።

እስካሁን ተግባራዊ የሆኑትን እና ወደፊት መደረግ ያላባቸውን ጉዳዮች ለመመልከትና አቅጣጫ ለማስቀመጥ የአፍሪካ ኅብረት አሸማጋዮች በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ መቀለ ያመራሉ።

የኅብረቱ አደራዳሪዎች ወደ ትግራይ የሚያቀኑት ከሳምንታት በፊት በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረሰውን ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት አፈጻጸምን ለመታዘብ መሆኑን የቡድኑ አባል የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተናግረዋል።

በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ሁለቱን ወገኖችን ሲያደራድሩ የነበሩት ፕሬዝዳንቱ እያበቃ ያለው የፈረንጆቹ ወር ከመጠናቀቁ በፊት ባሉት ቀናት ውስጥ ወደ ትግራይ ሊያምሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ኡሁሩ በየትኛው ቀን ወደ መቀለ እንደሚጓዙ ሲጠየቁ፤ “ቁርጥ ያለ ቀን መናገር አልፈልግም፣ ነገር ግን በዚህ ወር መጨረሻ እንበል። ለዚያ ነው በጥቂት ቀናት ውስጥ ያልኩት” ሲሉ መልሰዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና የህወሓት ወታደራዊ አዛዦች ለሁለተኛ ጊዜ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ላይ ከረቡዕ ታኅሣሥ 12/2015 ዓ.ም. ጀምሮ እያደረጉት ያለው ውይይት ስኬታማ መሆኑን ኬንያታ ተናግረዋል።

በዝግ የተደረገውን የሁለቱን ወገኖች ውይይት ተከትሎ ኬንያታ “ከፍ ያለ ውጤት” መታየቱን እና በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ለማስፈን “በትክክለኛው አቅጣጫ እየተጓዝን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በደቡብ አፍሪካ ተጀምሮ ወደ ኬንያ የቀረበው በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የተካሄደው የሰላም ጥረት በቀጣይ ወደ መቀለ በማምራት የተደረሰበት ደረጃ ይፋ ይሆናል።

ከዚህ በፊት ኡሁሩ ኬንያታ ከመቀለ በመቀጠል የሰላም ስምምነቱ ስኬት መቋጫ በአዲስ አበባ ላይ በሚደረግ ሥነ ሥርዓት እንደሚሆን መናገራቸው ይታወሳል።