ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቀጣዩ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድ እንሁን ሲሉ ጥሪ አቀረቡ
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትርነት ውድድርን ያሸነፉት ሪሺ ሱናክ “ይህንን ከባድ የኢኮኖሚ” ፈተና በአንድነት ቆመን እና በመረጋጋት እንለፈው የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል።
ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር በከባድ ፉክክር በተደረገው ውድድር ተቀናቃኛቸውን አሸንፈዋል።
ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ከተረጋገጠ በኃላ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር ፓርቲያቸውን እና ዩኬን ወደ አንደነት ማምጣት ከምንም በላይ ቅደሚያ የሚሰጡት እንደሆነ ተናግረዋል።
ሱናክ የእስያ የዘር ሀረግ ያላቸው የመጀመሪያው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስተር ሲሆኑ ከ200 ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ ዕድሜ ከሳቸው ያነሰ ወይም እኩል የሆነ ጠቅላይ ሚኒስተር አልነበረም።
የሂንዱ እምነትን የሚከተሉት የ42 ዓመቱ ሱናክ ንጉስ ቻርለስ በይፋ በሚሰጧቸው ሹመት ዛሬ ስልጣናቸውን ይረከባሉ።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከ45 ቀናት የስልጣን ቆይታ በኃላ ባለፈው ሳምንት ሃላፊነት በቃኝ ያሉትን ሊዝ ትረስ የሚተኩ ይሆናል። .
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር በስልክ “እንኳን ደስ አለዎት” የማለት እቅድ እንዳለቸው ኋይት ሃውስ አሳውቋል።
ሱናክ እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 በዩኬ በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ያሸነፈውን ወግ አጥባቂ ፓርቲ የወከሉ ሶስተኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው።
ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር በዝግ በተደረገ ስብሰባ ላይ ለፓርቲያቸው አባላት ባደረጉት ንግግር ጊዜው አስቸጋሪ ነው ያሉ ሲሆን በቀጣዩ ምርጫ ልናሸንፍ እንችላለን ማለታቸው ተሰምቷል።
በምርጫው ብርቱ ፉክክር ይገጥመናል ያሉ ሲሆን አንድ ከሆንን ግን ልነሸንፍ እንችላለን ብለዋል።
ከዚህ ስብሰባበኋላ በቴሌቪዢን ቀርበው ባደረጉት ከሁለት ደቂቃ ያነሰ ንግግር “በቅንጅት” እንደሚሰሩቃል የገቡ ሲሆን ተሰናባቿን ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስን “እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ” ስለሰጡት አመራር አመስግነዋቸዋል።
“ዩናይትድ ኪንግደም ታላቅ ሀገር ናት ሆነም ምንም በማያጠራጥር ሁኔታ ከባድ የምጣኔ ሃብት ፈተና ላይ ነን” ያሉት ሱናክ “አሁን መረጋጋት እና አንድነት ያስፈልገናል። ፓርቲያችንን እና ሀገራችንን በጋራ ለማቆም ከምንም በላይ ቅደሚያ ሰጥቼ እሰራለሁ” ሲሉ አክለዋል።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሳምንታት በፊት በተቀናቃኛቸው ሊዝ ትሩስ ተረተው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታን ቢያጡም ባልተጠበቀ መንገድ እና ፍጥነት ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ተሰናባቿ ጠቅላይ ሚኒስትር በስልጣን ላይ እያሉ ይፋ ያደረጓቸው የኢኮሚ እቅዶች “የተረት ተረት ኢኮኖሚከስ” ሲሉ ያጣጣሉባቸውን ሪሺ ሱናክን እንኳን ደስ አለዎት ያሉ ሲሆን “ሙሉ ድጋፍ” እንደሚሰጧቸው ቃል ገብተዋል።
ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀገራቸው በኢኮኖሚ ፈተና ላይ ባለችበት ወቅት ስልጣን ይረከባሉ።