ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ የሰላም ተደራዳሪዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናታቸው ተገለጸ
በሰሜን ኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት እየተፋለሙ ያሉት የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ወኪሎች ዛሬ ጥቅምት 14፣ 2015 ዓ.ም ለሚጀመረው የሰላም ንግግር ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናታቸው ተገለጸ።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሕይወት፣ በአፍሪካ ኅብረት በሚመራው የሰላም ንግግር ላይ የሚሳተፈው የትግራይ ልዑክ ቡድን ደቡብ አፍሪካ ደርሷል ሲሉ ትናንት እሁድ ጥቅምት 13 ምሽት ላይ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ረፋድ ጥቅምት 14/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በሰላም ንግግሩ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ዛሬ ጠዋት ወደ ደቡብ አፍሪካ አምርቷል ብሏል።
ሁለቱ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር ለመፍታት በጠረጴዛ ዙሪያ የሚቀመጡት በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት ነው።
ባለፉት ቀናት የፌደራሉ መንግሥት ጥምር ኃይሎች በርካታ ከተማዎችን እና የትግራይ አካባቢዎችን ከትግራይ ኃይሎች አስለቅቋል የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ ነው።
ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 14/2015 ዓ. ም. ጀምሮ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በፌደራል መንግሥቱ እና በሕወሓት አመራሮች መካከል የሰላም ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የንግግር አጀንዳዎች
የአፍሪካ ኅብረት ተፋላሚ ኃይሎች ግጭት አቁመው ልዩነቶቻቸው በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ሊደራደሩባቸው የሚችሏቸውን ጉዳዮች በይፋ ባይገልጹም፤ የአፍሪካ ኅብረት እና ምዕራባውያን ግን ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ፕሮፌሰር ክንደያ፣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በሚደረገው ውይይት የትግራይ ኃይሎች የሚያነሷቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች ግጭት በአስቸኳይ ማስቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ እና የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ማስወጣት የሚሉት መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የፌደራል መንግሥት ግን ከዚህ ቀደም "ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ" ለንግግር ዝግጁ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።
ድርድሩ “. . . ለዜጎች መረጋጋትንም ይመልሳል”
ዛሬ በደቡብ አፍሪካ የሚጀመረው የሰላም ንግግር ለሁሉም ዜጎች መረጋጋትን የሚመልስ ነው ስትል አሜሪካ ያላትን ተስፋ ገልጻለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ጥቅምት 11፣ 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሰላም ውይይቱን አሜሪካ እንደምትደግፍ ገልጾ፤ ድርድሩ በኢትዮጵያ ያለውን ውጊያ ይገታል ሲል ያለውን ተስፋ ጨምሮ ገልጿል።
“ደቡብ አፍሪካ ይህንን ውይይት ለማስተናገድ በመፍቀዷ እናመሰግናለን። የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆን እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ፓናል አባል የሆኑትን ፑምዚሌ ማልምቦ ንግቹካ እና ኡሁሩ ኬንያታ የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደረስ የሚያደርጉትን ጥረት እንደግፋለን” ይላል መግለጫው።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ድረ ገጽ ላይ የወጣው መግለጫ “ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መስከረም ላይ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዳሉት፣ በአፍሪካ ኅብረት ፓናል አባላቱ አማካይነት የሚደረሰው የሰላም ስምምነት፣ በኢትዮጵያ ያለውን ውጊያ ይገታል። ለሁሉም ዜጎች መረጋጋትንም ይመልሳል” ሲልም አክሏል።
ተደራዳሪዎቹ እነማን ናቸው?
የፌደራሉ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚነጋገሩ አባላት ከዚህ ቀደም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ይህ ተደራዳሪ ቡድን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የሚመራ ሲሆን ሰባት አባላትን ያካተተ ነው።
ከአቶ ደመቀ በተጨማሪ የፌደራል መንግሥቱን የሚወክሉት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፣ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጥሩነህ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንት ጉዳዮች አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የመከላከያ ሠራዊት የመረጃ ደኅንነት ኃላፊ ሌ/ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ጌታቸው ጀምበር (ዶ/ር) እና በብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ማዕከል ዘርፍ ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት እየሰሩ የሚገኙት አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር ናቸው።
የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው ሁለት ተወካዮቻቸውን ለድርድር እንደሚልኩ ከዚህ ቀደም ገልጸው ነበር። የመጀመሪያው የህወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የፓርቲው ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ የትግራይ ኃይሎችን ከሚመሩት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች መካከል አንዱ የሆኑት ጀኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ ናቸው።