ብሊንከን ከሰላም ውይይቱ በፊት ፕሬዝዳንት ሩቶን እና የደቡብ አፍሪካ ባለስልጣንን አነጋገሩ

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች በደቡብ አፍሪካ ከሚያደርጉት የሰላም ንግግር በፊት የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ከኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናት ጋር ተነጋገሩ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ባወጣው መግለጫ መሠረት አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ጉዳይ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና ከደቡብ አፍሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ናሌዲ ፓንዶር ጋር ተነጋግረዋል።

ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 14/2015 ዓ. ም. ጀምሮ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የሰላም ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

የትግራይ ኃይሎች በውይይቱ የሚሳተፉ ልዑካን ደቡብ አፍሪካ መድረሳቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ቀደም ሲል ደግሞ የፌደራሉ መንግሥት ዛሬ በሚደረገው ውይይት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

ውይይቱ ከሚደረግበት አንድ ቀን ቀደም ብሎ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በንግግሩ ላይ ተሳትፎ ካላቸው የአፍሪካ መሪዎች ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።

ከኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኬንያ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ስላላት 'ቁልፍ' ተሳትፎ ተነጋግረዋል።

በተመሳሳይ አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ጉዳይ ከደቡብ አፍሪካው የውጪ ጉዳይ እና ትብብር ሚንስትር ናሌዲ ፓንዶር ጋር በስልክ አውርተዋል።

ብሊንክን ከሚንስትሩ ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር በደቡብ አፍሪካ ስለሚካሄደው የሰላም ውይይት መወያየታቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ መግለጫ አመላክቷል።

ደቡብ አፍሪካ ይህን ውይይት በማስተናገዷ ከዚህ ቀደም ከአሜሪካ የምስጋና መልዕክት ደርሷት ነበር።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ጥቅምት 11፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “ደቡብ አፍሪካ ይህንን ውይይት ለማስተናገድ በመፍቀዷ እናመሰግናለን። የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆን እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ፓናል አባል የሆኑትን ፑምዚሌ ማልምቦ ንግቹካ እና ኡሁሩ ኬንያታ የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደረስ የሚያደርጉትን ጥረት እንደግፋለን” ብሎ ነበር።

ሁለቱን ተዋጊ ኃይሎች የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ፣ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፉምዚሌ ምላምቦ-ናግኩካ እና የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በአሸማጋይነት በንግግሩ ይሳተፋሉ ተብሎ ነበር።

ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከዚህ ቀደም በሎጂስቲክስ ምክንያት በተላለፈው ንግግር ላይ እንደማይሳተፉ ገልጸው ነበር።