ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሁን ባለው የዋጋ ግሽበት ገንዘብ መቆጠብ ያዋጣል?
በአጠቃላይ ገንዘብ ቆጠብን ስንል ወደ ወጪ ያልተቀየረ ገንዘብ አለን ወይንም ወጪያችንን በመቀነስ የምናስቀምጠው ገንዘብ ማለታችን ነው።
በምጣኔ ኃብት ቋንቋ ደግሞ ገቢያችን የወጪያችን እና የቁጠባችን ድምር ነው።
የምጣኔ ኃብት ባለሙያው ተሾመ ተፈራ (ዶ/ር) በመርህ ደረጃ ከወጪ የሚተርፍ ገንዘብ መቆጠብ አለበት።
ይሁን እንጂ ቁጠባ ከሰዎች ባህሪ ጋር የሚገናኝ ጉዳይ ነው ይላሉ።
“አንዳንድ ሰዎች ከወጪያቸው ቆጥበው ለወደፊት ኑሯቸው፣ ለጡረታ ዘመናቸው ወይንም ለልጆቻቸው ይቆጥባሉ። ሌሎች ደግሞ ከወጪያቸው እንደፈለጉ አውጥተው የሚተርፋቸውን ያስቀምጣሉ፤ ሌሎች ዛሬን ብቻ መኖር የሚፈልጉ አይቆጥቡም። ስለዚህ ቁጠባ ሌሎች ነገሮች ላይ ከምናሳየው ከባህሪያችን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው” ይላሉ።
የደስተኝነት ጥያቄ እና ቁጠባ
የምጣኔ ኃብት ባለሙያው እንደሚሉት በግለሰብ ደረጃ የምናደርገው የሀብት አጠቃቀም ውሳኔ አንድ ሰው ደስታ ያመጣልኛል ብሎ በሚያምነው ነገር ላይ የተመሰረተ ነው።
“ለምሳሌ አንድ ሰው ዛሬ ደስ የሚለውን ልብስ መግዛት ያስደስተኛል ካለ፣ ሊቆጥብ የሚገባውን ገንዘብ እዚያ ላይ ያወጣዋል። ሌላው ሰው ደግሞ ለወደፊት መግዛት ለሚፈልገው ደስታ አሁን ብሩን ይቆጥባል ማለት ነው”
ተሾመ (ዶ/ር) እንደሚሉት ገንዘብ የሚቆጥበውም ሆነ አባካኝ የሆነው፣ ሌላ ሰው ከውጪ ስም ይሰጣል እንጂ ሁለቱም በገንዘባቸው ደስታን የመግዛት ስራ እየሰሩ ነው ያሉት።
የዋጋ ንረት እና ቁጠባ
በምንኖርባት አገር ውስጥ የምንቆጥበው ገንዘብ ጥቅም ሊያስገኝልን የሚችለው የገበያው የዋጋ ንረት እኛ በመቆጠብ ከምናገኘው ጥቅም በታች ከሆነ ብቻ ነው ይላሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው።
ይህንንም በምሳሌ ሲያስረዱ “አንድ ሰው ያለፈው ዓመት አንድ መቶ ብር ባንክ ቢያስቀምጥ ከአመት በኋላ ቢበዛ ስድስት በመቶ ብቻ ነው ሊወልድለት የሚችለው። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የዋጋ ግሽበቱ ከ34 በመቶ በላይ ሆኗል።”
የምጣኔ ኃብት ምሁሩ እንደሚሉት አምና የቆጠብነው አንድ መቶ ብር ዘንድሮ የመግዛት አቅሙ በ34 በመቶ ይወርዳል።
“ስለዚህ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት ባለበት አገር ገንዘብ ዝም ብሎ ማስቀመጥ አዋጭ አይደለም። ከዚህ የዋጋ ግሽበት የቆጠቡትን ገንዘብ ለማስመለጥ ሰዎች መሬት እና የመሳሰሉ ሀብቶችን በመግዛት ገንዘባቸውን የተሻለ ነገር ላይ ቢያውሉት ተመራጭ ነው” ይላሉ።
አክለውም “ግን በአጠቃላይ ቁጠባ ጥቅም ሊያስገኝ የሚችለው የአንድ አገር የዋጋ ንረት ከባንክ ወለድ በታች ከሆነ ብቻ ነው። በዚህ ሁኔታ ገንዘብ መቆጠብን እንደ መነሻ ተጠቅመን ገንዘባችንን ኢንቨስት ማድረግ የተሻለ አማራጭ ነው። ገንዘብ ኢንቨስት ማድረግ ማለት፣ ገንዘብ ማስቀመጥ ሳይሆን እንዲያድግ ማድረግ ነው፝
ይህንንም በምሳሌ ሲያስረዱ፣ የባንክ ሼር በመግዛት እና በተለያዩ ሌሎች አማራጮች ተግባር ላይ ማዋል እንደሚቻል በመጥቀስ ይመክራሉ።
ለምሳሌ ይላሉ ዶ/ር ተሾመ፣ “ የኢትዮጵያ ባንኮች ለአንድ አክስዮን ከ20 በመቶ በላይ ትርፍ ይከፍላሉ። ስለዚህ ከምንቆጥበው ገንዘብ በላይ እንጠቀማለን ማለት ነው።”
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ኢንቨስትመንት ስላልተስፋፋ ከኢንቨስትመንት ላይ የምናገኘው ጥቅም ትልቅ ሊሆን ይችላል። እንደ ጃፓን ያሉ አገራት ውስጥ ግን ያለው የዋጋ መውረድ (ዲፊሌሽን) በመሆኑ ገንዘብ መያዝ ኢንቨስት ከማድረግ የተሻለ አማራጭ የሚሆንብት አጋጣሚ መኖሩን አቶ ተሾመ ያስረዳሉ።
ገንዘብ በመቆጠብ ሀብት ማካበት ይቻላል?
የተረጋጋ ምጣኔ ሀብት ባለበት አገር ገንዘባቸንን ስራዬ ብለን ብንቆጥብ ሀብት ማካበት እንችላለን የሚል ጥያቄ ለምጣኔ ኃብት ምሁሩ አቅርበን ነበር።
ባለሙያውም የአንዳንድ አገራትን ልምድ በማንሳት ይህንን ጉዳይ ያብራራሉ።
እንደ ቤልጂየም ያሉ አገራት ቁጠባን አያበረታቱም። ስለዚህ የቁጠባ የባንክ አካውንት ለሚከፍቱ ሰዎች ዓመታዊ ክፍያ ያስከፍላሉ።
ይህንንም የሚያደርጉት ብሩ እንዳይቀመጥ እና ስራ ላይ እንዲውል ስለሚፈልጉ ነው።
በአገራችን ግን ባንኮች እነርሱ ጋር አንድንቆጥብ በዘመቻ የሚያበረታቱን ከተጠቃሚው የሚሰበስቡትን ገንዘብ ለኢንቬስተር አበድረው ጥቅም ማግኝት ስላለባቸው ነው ይላሉ።
ስለዚህ እንደ ምሁሩ ገለጻ፣ ገንዘብ መቆጠብ እድል የሚከፍት ቢሆን እንጂ ብቻውን ወደ ሀብት ማካበት አያደርሰንም።
ለምሳሌ አንድ ተቀጥሮ የሚሰራ ሰራተኛ ገንዘቡን ቢቆጥብ በግሽበት እየተበላበት ነው የሚሄደው።
በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ እና የሰራተኞች ማህበራት ጠንካራ ባልሆኑበት አገር፣ የዋጋ ግሽበት በመጣ ቁጥር የሰራተኛው ደመወዝ ስለማይስተካከል መቆጠብ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ።
ነገር ግን አንድ ሱቅ ያለ ሰው ከተቀጣሪ ራሱን በተሻለ ሁኔታ ማስተዳደር ይችላል። ምክንያቱም የሽያጭ እና ግዢ ሁኔታው ከዋጋ ግሽበቱ ጋር ማስተካከል ስለሚችል ነው።
እንዲሁ በአጠቃላይ የተረጋጋ ኢኮኖሚ ባለበት አገር ገንዘብ መቆጠብ ኢንቨስት ለማድረግ መንገድ ሊከፍት እና ሊያሳድግ ይችላል። ነገር ግን በራሱ መቆጠብ ወደ ሀብት ማካበት አያደርስም።
ቁጠባ እና ኢንቨሰትመንት
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት የቁጠባ እና የኢንቨስትመንት ዋና ልዩነት ገንዘብን ለአጭር እና ለረዥመ ጊዜ ማስቀመጥ ነው።
በተጨማሪም ሌሎች እነዚህ ሁለቱ ሀሳቦች የሚለያዩበት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።
- የምንቆጥበውን ገንዘብ በምንፈልግበት ጊዜ ማግኝት እንችላለን። ገንዘባችንን የማጣት እድልም በጣም ትንሽ ነው። ገንዘብ ስንቆጥብ ገንዘባችንን የማስቀመጥ ተግባር ነው።
- ኢንቨስት ስናደርግ ግን በረዥም ጊዜ ውስጥ ገንዘባችንን ለማሳደግ የሚረዳ ሲሆን፣ ለጊዜው የማንጠቀምበት ገንዘብ ነው ማለት ነው። ኢንቨስት ስናደርግ ግን እያሳደግን ነው። ሆኖም ውጤቱን የምናገኘው በረዥም ጊዜ መሆኑ ነው።
- በቁጠባ እና በኢንቨስትመንት መካከል ያለው ግንኙነት ኢንቨስት ስናደርግ ሪስክ እንወስዳለን። ኪሳራ ከመጣ ማለት ነው