የሮማው ሊቀ ጻጻስ ጸሎታችን ኢትዮጵያውያንን ይርዳቸው አሉ

የሮማው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተሳታፊዎች ውይይት ፍሬማ እንዲሆን እመኛለሁ አሉ።

“ጸሎታችን እና አጋርነታችን ለኢትዯጵያውያን ወንድም እና እህቶቻችን አስፈላጊው ሰብአዊ እርዳታ ያለእንከን እንዲደርስ ያድርግ” ብለዋል።

አቡነ ፍራንሲስ በኢትዮጵያ ያለውን “የማያቋርጥ ግጭት” በሃዘን ስሜት እየተከታተልኩት ነው ሲሉ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

የሮማው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ ይህን ያሉት በፌዴራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በደቡብ አፍሪካ ንግግር እንደሚጀመር ከሚጠበቅበት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።

ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 14/2015 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የሰላም ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ከፌደራሉ መንግሥት ጋር እየተፋለሙ ያሉት የትግራይ ኃይሎች ዛሬ ለሚጀመረው የሰላም ንግግር ደቡብ አፍሪካ መድረሳቸው ያስታወቁ ሲሆን፤ ቀደም ሲል የፌደራሉ መንግሥት ዛሬ በሚደረገው ውይይት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

ሊቀ ጳጳሱ የግጭቱ ተሳታፊዎች ንግግር ለመጀመር እያደረጉ ያለው ጥረት ፍሬ አፍርቶ እውነተኛ እርቅን የሚያመጣ እንዲሆን መርቀዋል።