በአረብ አገራት የተከበበችው ኢትዮጵያ ከሐላል ሥጋ ለምን ቢሊዮን ዶላር ማግኘት አቃታት?

የዓለም የሐላል ምግብ ገበያ ግምት 1.6 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል።

ስድስት ሚሊዮን ሙስሊሞች ባሉባት ፈረንሳይ የሐላል ምግብ ገበያ በዓመት 6 ቢሊዮን ዩሮ ይደርሳል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሐላል ኢንዱስትሪ ሐሳቡም ያለ አይመስልም።

ጥቂት አረቢያን ሬስቶራንቶች እንጂ ኢንዱስትሪው አይታወቅም።

ሐላል ምግብ መቀማመስ የሚሻ የውጭ እንግዳን ደረት ነፍቶ መጋበዝ የሚያስችሉ አገር በቀል የሐላል ፒዛና የሐላል በርገር ቤቶችም የሉም።

የሐላል ምግብ ቤቶች አነስተኛ ሙስሊሞች በሚኖሩባቸው ምዕራቡ ዓለም ጭምር በስፋት አሉ።

ኢትዮጵያ ከአካባቢው አገራት ብቻ ሳይሆን ከአንዳንድ አረብ አገራት በላይ የሙስሊም ቁጥር አላት።

በርካታ የአረብ አገር ኤምባሲዎች መቀመጫም ናት። የሐላል አቅርቦቷ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

የአገር ውስጥ የሐላል ገበያን ሌላ ጊዜ እንመለስበት። ዛሬ ስለውጭ ንግድ እናውራ።

ሐላል ሥጋን እንደ ቡና ወደ ውጭ እየላክን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንዴት አቃተን?

ለመሆኑ ሐሳቡስ አለ?

ሐላል ሥጋ ምንድን ነው?

ለሙስሊሞች ሐላል የሥጋ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ‘የሕይወት ዘይቤ’ ነው።

ብዙዎች እንደሚገምቱት ሐሳቡ ምግብና መጠጥ ላይ አያበቃም።

የመድኃኒት ምርት፣ የውበት ዕቃዎች፣ ማረፊያ ሆቴሎች ሳይቀሩ ሐላል ናቸው ወይ ተብለው ይፈተሻሉ።

 ‘ሐላል ቱሪዝም’ የሚባል ትልቅ ሐሳብም አለ። መጠጥ ከማይሸጥበት ሐላል ሆቴል ከማረፍ ጀምሮ ሙሉ የቱሪዝም አገልግሎቱ በሐላል ሰንሰለት የተዘረጋ ነው።

ለዛሬ ሐላል ሥጋን ብቻ ነጥለን ብንወስድ ግን ትርጉሙ ይጠባል።

 ለእርድ የቀረበው እንሰሳ ሐላል እንዲሆን ከሚባረክበት ስም ጀምሮ እስከሚሰዋበት ዘዴ ድረስ፣ አበላለቱን ጨምሮ ጥብቅ አፈጻጸሞች አሉት።

ይህን ኢስላማዊ የእርድ ሥርዓትን የተከተሉ ቄራዎች፣ ሐላል ሥጋ አቅራቢዎች ተደርገው ይወሰዳሉ።

ያ ግን የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ስላልሆነ አንዘልቅበትም።

 ‘ሐላል’ በሥጋ ብቻ የሚያበቃ ነገር አይደለም የሚለው ለማስረዳት ያህል ነው ይህን ያነሳነው።

አንዳንድ ጊዜ ግን ከሥጋ ውጭ ያሉ ነገሮች ‘ሐላል ናቸው፣ ሐላል አይደሉም’ ሲባሉ እንሰማለን፤ ለምን?

አንድ ምርት በኢስላም ክልክል የተደረጉ (ሐራም ከሆኑ) ምግቦች ተረፈ ምርት ሲገኝ ክልክል ይሆናል።

ለምሳሌ የአሣማ ሥጋ በኢስላም ክልክል ነው። ለምሳሌ የዉሻ ሥጋ ክልክል ነው።

የሥጋው ተረፈ ምርት ለአንድ መድኃኒት መሥሪያ ቢውል ያ መድኃኒት ከሐላልነት ዝርዝር ይወጣል።

እንደ ጄላቶ (Jelato) አይስክሬሞች፣ ቼኮሌቶች፣ ክሬሚ ብስኩቶች በአንድም በሌላም የአሣማ ንክኪ ያለባቸው ከሆኑ ተመሳሳይ ክልከላ ይጣልባቸዋል።

አንዳንድ ሊፒስቲኮች አሣማን እንደ ጥሬ ዕቃ ይጠቀሙታል።

በፋርማሱትካል የተለያዩ በእርግዝና ወቅት የሚወሰዱ መድኃኒቶች፣ ለምሳሌ ካፕሱሎቻቸው፣ በዚህ ጥሬ ዕቃ የተሠሩ ከሆኑ በኢስላም ክልክል ይደረጋሉ።

ስለዚህ የሐላል ኢንዱስትሪ ስንል ከግዙፍ ፋይናንስ ተቋምና ቱሪዝም እስከ አንዲት ሊፒስቲክ ሊዘልቅ ይችላል።

ኢትዮጵያ ለምን ከዚህ ዘርፍ ዶላር ማፈስ አቃታት?

አሁን ኢትዮጵያ ቀልቧ ስንዴ ላይ ነው።

ባለሙያዎች ግን በኢትዮጵያ ያልተነካ ሌላ ዶላር ማለቢያ ዘርፍ የሐላል ኢንዱስትሪ እንደሆነ አበክረው ያስገነዝባሉ።

ቢንመሊክ አብዶ በዚህ የሐላል ዘርፍ በማስተዋወቅ የተሰማሩ ናቸው።

ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ቢንመሊክ፣ ‘እንደ ኢትዮጵያ ከሐላል ኢንዱስትሪው ብዙ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ ላይ ያለ ሌላ አገር አላውቅም' ብለው ነበር።

እርሳቸው ከወራት በፊት ይህን ሰፊ ዕድል ለአገር ውስጥ ባለሐብቶች ለማስተዋወቅ የሐላል ኤክስፖ አሰናድተው ብዙ ባለሀብቶች ታድመውታል።

ቢንመሊክ ‘ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ሳይሆን ዓለም አቀፍ የሐላል ኤክስፖ ነበር ማዘጋጀት የነበረባት።' ብለው ይቆጫሉ።

በዚሁ መድረክ ላይ ተገኝተው የነበሩት የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴንም ተመሳሳይ ስሜት አንጸባርቀው ነበር።

ኢትዮጵያ ከግብርናው ዘርፍ ለሐላል ገበያ የምታቀርበው በርካታ ምርቶች አሉ ያሉት ሚኒስትሩ፤ ተደራሽነታችን በማስፋት እንደ ተረካቢው አገር ፍላጎት ካቀረብን በዘርፉ ብዙ እንጠቀማለን’ ብለው ነበር።

ታዲያ ለምን በተባለው ደረጃ አናቀርብም?

 ለምንድን ነው ኢትዮጵያ ለሐላል ኢንዱስትሪ የተመቸች ተደርጋ የምትታሰበው ከሚለው ጥያቄ እንጀምር።

ቢንመሊክ የሚመልሱት ሁለት ቁልፍ ነጥቦችን በማንሳት ነው።

አንደኛ ኢትዮጵያ ለመካከለኛው ምሥራቅ ቅርብ ናት።

ሁለተኛ ደግሞ ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ሃብታም ናት።

የተረጋገጠ መረጃ በቅርብ ማግኘት ቢከብድም በቀንድ ከብት ሃብት ብዛት (ቁጥርን ብቻ ያማከለ) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት፤ ከዓለም ደግሞ 5ኛ እየተባለች ትወደሳለች።

ታዲያ ለምን ከዘርፉ ብዙ ማግኘት ተሳነን?

‘መጀመርያ አረቦቹ ለኛ ያላቸው አመለካከት መቀየር አለበት’

አንዱ ማነቆ አረቡ ዓለም ለኛ ያለው በጎ ያልሆነ አመለካከት ነው።

ይህ አሉታዊ ስሜት ቀደም ካለው የረሀብ ታሪካችን ጋር ተያይዞ የሚመዘዝ እንደሆነ ይገመታል።

አቅርቦታችን አስተማማኝና እነርሱ በሚፈልጉት ከፍ ያለ ጥራት ደረጃ አለመሆኑ ሌላው ችግር ነው።

‘በኛ የሥጋ ምርት ላይ ብዙም መተማመን የላቸውም’ ይላሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያ አቶ አብረሃ ነጋሽ።

አቶ አብረሃ በሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የሥጋ ኢንዱስትሪዎች ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው።

አረቦቹ በኛ ላይ እምነት ያሳጣቸው ብዙ ነገር ነው።

የቀንድ ከብቶቹን የምንከባከብበት መንገድ፣ የቄራዎቻችን ጥራትና አያያዝ፣ የንጽሕና አጠባበቅ፣ መኖ አቅርቦት ወዘተ በዚህ ይካተታሉ።

ለምሳሌ አንዳንድ አረብ አገራት የሥጋ ተረካቢዎች የከብቱን ሙሉ የሕይወት ታሪክ ማወቅ ይፈልጋሉ።

አቶ አብረሃ ይህን ሐሳብ ‘traceability’ በሚል ይጠቀልሉታል።

‘አንድ ፍየል የት ተወልዶ፣ ምን በልቶ፣ ምን ተከትቦ፣ የት ቄራ ገብቶ በስንት ዓመቱ ታረደ የሚለውን የፍየል የሕይወት ታሪክ በሙሉ ማወቅ ይፈልጋሉ።‘

ይህ እንግዳ ነገር ሊመስል ይችላል። ቅብጠት ነው የሚልም አይጠፋም።

 ነገር ግን በወጭ ንግዳችን ላይ አንድ ማነቆ የሆነው ይህን አለማሟላታችን ነው።

የከብቱን የሕይወት ታሪክ በወጉ ማቅረብ አለመቻላችን ።

ይኸው ጥያቄ አቶ አብረሃ ዱባይ ውስጥ በነበረ አንድ አውደ ርዕይ አጋጥሟቸዋል።

‘ለአውስትራሊያ ሥጋ በኪሎ 5 ዶላር እየከፈለ ለኛ ሥጋ ቅናሽ ዋጋ ትጠራለህ ምነው? ይሉታል’፤ አንድን የሥጋ ተረካቢ።

‘...በዚያ ላይ ደግሞ የኛ ኦርጋኒክ ሥጋ ነው’ ሲሉ ሞገቱት።

ይህ አረብ የመለሰላቸው ምላሽ እንዲህ የሚል ነበር፤-

‘ለመሆኑ ፍየሉ ኦርጋኒክ ስለመሆኑ የሰርተፍኬት መረጃ ልታቀርብልኝ ትችላለህ?’

ቢሊዮን ዶላር እንዳናገኝ ያደረጉ ሌሎች ማነቆዎች

ቢንመሊክ ዋናው ፈተና ዓለም አቀፍ የዕውቅና ሠርተፍኬት ማግኘት እንደሆነ ያምናሉ።

እኛ የሌለን፣ ሌሎች ያላቸው ይህ ሠርተፍኬት ነው ባይ ናቸው።

እንደ ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ አውስትራሊያና ኒውዚላንድ ያሉ አገራት ብዙ ሃብት የሚዝቁት ሐላል ሥጋን ወደ አረብ አገራት በመላክ ነው።

አረቦቹ የነርሱን ሥጋ የሚቀበሉት በሌላ ምክንያት ሳይሆን ደረጃውን ያሟላ የዕውቅና ሠርተፍኬት በአስተማማኝ ሁኔታ ስለሚያቀርቡላቸው ነው።

ቢንመሊክ፣ ‘ብራዚል ብቻ በዓመት 350ሺህ ቶን የሐላል ሥጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ትልካለች።’ ይላሉ በቁጭት።

ያስቆጫቸው ሌላ አይደለም። ብራዚል ከመካከለኛው ምሥራቅ በብዙ ሺህ ማይልስ ርቃ ነው የምትገኘው።

ኢትዮጵያ ለአረብ አገራት አፍንጫቸው ሥር ናት።

ይሁንና ኢትዮጵያ በ2014 ወደ መካከለኛ ምሥራቅ መላክ የቻለችው ሥጋ ግን 22ሺህ ቶን ብቻ ነው።

ይህ ኢትዮጵያ ካላት አቅም በጣም፣ እጅግ በጣም ትንሹ ነው።

ታዲያ አገሪቱ ያላትን አቅም አሟጣ የተሻለ ገቢ ማግኘት እንዴት አቃታት?

‘ሕዝባችን ምን ያህል ከብቶች አሉኝ እንጂ ምን ዓይነት ከብቶች አሉኝ አይልም’

ብዙ የቀንድ ከብት አለን ማለት ብዙ መላክ እንችላለን ማለት አይደለም።

አቶ አብረሃ ኢትዯጵያ በቀንድ ከብት ሃብት ክምችት ገናና አገር ብትሆንም የዚያን ያህል ግን ለገበያ መቅረብ ትቻለለች ማለት እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

አንዱ ምክንያት የተረካቢ አገሮች ፍላጎትና መመዘኛ ነው።

‘ወደ መካከለኛ ምሥራቅ ከሚላከው 80 ከመቶ የፍየል ሥጋ ነው። ይህም የፍየል ፍላጎታቸው ከፍተኛ ስለሆነ ነው። ‘

በዚያ ላይ የሚላከው ከብት ሥጋ የወንድ መሆን አለበት። እናት መላክ ጄኖሳይድ ተደርጎ ይወሰዳልና።

ከዚህ በተጨማሪ ሴት ከብት ለእርድ የማትላክበት ፊዚዮሎጂካል ምክንያትም አለው። ቶሎ ስጋቸው ስብ ስለሚሆን።

የሚላከው የፍየል ሥጋ ከስምንት ወር ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት የሆነው ብቻ ነው። በዚህ ዕድሜ ያለ በሙሉ ይላካል ማለት አይደለም።

የተመረጠ ብቻ ይላካል፤ ለምሳሌ የፍየሉ ሰውነቱ ደልዳላ መሆን አለበት።

ይህ ዝርዝር መለኪያ ሲቀመጥ ብዙ የቀንድ ከብት ሀብት ቢኖረንም መላክ የምንችለው ጥቂቱን ብቻ ያደርገዋል።

አቶ አብረሃም ሆነ ቢንመሊክ የሚስማሙበት ነጥብ በኛ አገር ከብት የሃብት መለኪያ እንጂ የሃብት መፍጠሪያ አለመሆኑን ነው።

‘በቀንድ የሚቆጥር ማኅበረሰብ ነው ያለን’ ይላሉ አቶ አብረሃ። ሲያብራሩ፣ ‘አርብቶ አደሩ ምን ያህል ከብቶች አሉኝ እንጂ ምን ዓይነት ከብቶች አሉኝ’ የሚለው ብዙ አያሳስበውም።’

‘አንዲት ዝንብ ቄራ ውስጥ ከተገኘች ጥለው ይሄዳሉ’

ሌላው ፈተና የቄራዎቻችን ጥራት ደረጃ ነው። ማረድ የሚችሉት 200ሺህ ቶን ነው፤ በዓመት።

18 የሐላል ቄራዎች ቢኖሩም በሙሉ ኃይል የሚሠሩት ግን 11 ብቻ ናቸው።

እነሱም ቢሆን ከአቅማቸው 20 ከመቶውን ብቻ ነው የሚሠሩት።

በዚህ ላይ የጥራት ደረጃቸው የተቀባዮችን አንጀት የሚያርስ አልሆነም።

‘ብዙውን ጊዜ አረቦቹ ለምርመራ (ሱፐርቪዥን) መጥተው ቄራ ሲሄዱ በሚያዩት ነገር ብዙም ደስተኞች አይሆኑም። ‘ ይላሉ ቢንመሊክ።

አቶ አብረሃም ተመሳሳይ ተሞክሮ አላቸው።

 ‘በየዓመቱ ከዱባይና ከሌሎች አገሮች ሁኔታዎችን ለማየት ይመጣሉ። ቄራ ውስጥ የዛገ ብረት ወይ ደግሞ ዝንብ ብትገኝ ወንጀል ነው። ሁለተኛ አይቀበሉም። ‘

አረቦቹ ካልተቀበሉን ደግሞ ሥጋችን ገዥ የለውም።

የምንልከው ለምን አነሰ?

አቅርቦቱ ለምን አነሰ ከተባለ ብዙ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ።

አንዱና ዋንኛው ደግሞ በአርብቶ አደሮች አካባቢ የሚታየው ተደጋጋሚ የሰላም እጦት ነው።

‘ግጭት ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ በድርቅ ይጠቃሉ’ ይላሉ አቶ አብረሃ።

በዚያ ላይ ከብቶች ወደ ቄራ ሲመጡ ብዙ ድብደባ ይደርስባቸዋል። ድብደባ ከደረሰባቸው ሥጋቸው ይጠቁራል።

ሌላው አቶ አብረሃም እንደ አገር ብዙ ዋጋ የሚያስከፍለን የሚሉት ከብቶቹ በድንበር አካባቢ በሕገ ወጥ መንገድ በመኪና ተጭነው መውጣታቸው ነው።

ይህ ራሱን የቻለ ሌላ ሐተታ የሚፈልግ ስለሆነ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን።

1 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ምን እናድርግ?

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ሐላል ሥጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ልካ አገኘሁ ያለችው ጠቅላላ ገንዘብ 120 ሚሊዮን ዶላር እንኳ አልሞላም።

ይህ አሐዝ አቅማችንን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ምክንያቱም 22ሺህ ቶን ልከን 120 ሚሊዮን ዶላር መላክ ከቻልን እንደ ብራዚል በዓመት 350ሺህ ቶን ብንልክ ስንት ቢሊዮን ዶላር ማፈስ እንደምንችል ለመገመት የቀለም ቀንድ መሆን አይፈልግም።

ስለዚህ ምን እናድርግ?

ቢንመሊክ ይህን ለማሳካት የመጀመርያው የሐላል ዕውቅና ሠርተፍኬት ማግኘት ነው ይላሉ።

ለጊዜው ዓለም አቀፍ አክሪዲቴሽን ያለው የሐላል ሰርተፊኬሽን ተቋም ተቋቁሟል።

በዚያ ሠርተፍኬት ምርቶች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ መግባት እንዲችሉ ማለት ነው።

ይህ ሠርተፍኬት አንድ ምርት የሐላል መስመሮችን አልፎ መመረቱን የሚያረጋግጥ ይሆናል።

ቀጥሎ የሚመጣው የሐላል መሠረተ ልማትን መገንባት ነው

 ይህ ከቄራዎች ጀምሮ፣ ከብቶችን ማቆያ (ራንች)እንዲሁም ማጓጓዣን ይጨምራል።

እያንዳንዱ ቄራ የራሱ ሰፊ መሬት ኖሮት የራሱ መኖና ከብት ማቆያ እንዲኖረው ያሻል።

‘ዘመናዊ እርባታ መኖር አለበት፣ የከብቶችን ጤና፣ ክትባት፣ ውልደትና ጠቅላላ የሕይወት ታሪክ ሰንዶ መያዝ ያስፈልገናል’ ይላሉ አቶ አብረሃ።

‘ይሄ ከብት በሕይወት ሳለ ምን በሽታ ይዞት ነበር? ምን ተከተበ’ ብለው ሁሉ ይጠይቁኻል።‘

ሌላው ማነቆ የደላላ ሰንሰለት ነው።

‘አሁን ያለው ገበያ በደላላ የተተራመሰ ነው።‘ ይላሉ ቢንመሊክም አቶ አብረሃም።

 ለመሆኑ 1 ቢሊዮን ዶላር ከሐላል ሥጋ ማግኘት የሚደረስበት ርቀት ነው?

ቢንመሊክም ሆኑ አቶ አብረሃ በቁርጠኝነት ከተሠራ ይህ ገቢ ሩቅ እንዳልሆነ ያምናሉ።

አሁን አረቦቹ ለኪሎ ሥጋ 6 ዶላር አማካይ ይከፍላሉ።

አሁን እየላክን ያለነው 20ሺህ ቶን ብቻ ነው።

ከዚህ ያገኘነው ደግሞ 120 ሚሊዮን ዶላር ነው። ቄራዎቹ እየሠሩ ያሉት በ20 ከመቶ አቅማቸው ነው።

በዚህ ስሌት 200ሺህ ቶን ሐላል ሥጋ ከላክን 1 ቢሊዮን ዶላር በቀላሉ ይገኝበታል።

ሥጋን ከውጭ የሚያስገቡት የአዲስ አበባ ኤምባሲዎች

አቶ አብረሃ ደጋግመው የሚያሳስቡት የተቀባይ አገራት በኛ ላይ ያላቸውን እምነትን ማሳደግ ላይ ነው።

ይህ ሥራ መጀመር ያለበት ከአዲስ አበባ ይመስላል።

ቢንመሊክ በሥራ አጋጣሚ ያገኟቸው ኤምባሲዎች ለራሳቸው ፍጆታ እንኳ ሐላል ሥጋን ከውጭ አገር እንደሚያስገቡ ጠቀስ አድርገው አልፈዋል።

እርሳቸው ነገሩን እንደዋዛ አነሱት እንጂ ነገሩስ የዋዛ አይደለም።

120 ኤምባሲዎች የሚገኙባት፣ አፍሪካ ኅብረት ያለባት አገር የሐላል ፍላጎትን አለሟሟላት ቅር የሚያሰኝ ነው።

የአፍሪካ ህብረት ውስጥ ያሉ ዲፕሎማቶች በየሱፐርማርኬቱ የሥጋ ሸልፍጋ ቆመው ሐላል ከሆነ የታል ማህተም እያሉ ሲከራከሩ ማየት የተለመደ ነው።

ይህ ብቻ አይደለም የሚደንቀው።

ለሠራተኞቻቸው ከራሳቸው አገር ሐላል ሥጋ የሚያስመጡ ኤምባሲዎች መኖራቸው ነው የበለጠ አስገራሚው ነገር።

‘ብዙዎች የኤምባሲ ሰዎች ጥያቄ አላቸው። በትክክል ምንድን ነው የምንመገበው፣ ሥጋው ከየት የመጣ ነው፣ ከአሳማ ጋር ንክኪ ይኖረው ይሆን?’ ብለው ይጠይቁናል ይላሉ ቢንመሊክ።

የዲፕሎማቶችን መተማመን በአዲስ አበባ ሳንፈጥር የሐላል ሥጋ ላኩልን ጥሪ ከሪያድ እንዲደወል መጠበቅ ቋንጣ ሐሳብ ይመስላል።