በረዶ እስከ መጣል የደረሰው የበልግ ዝናብ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለምን በረታ?

የፎቶው ባለመብት, social media
የበልግ ዝናብ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በጣም በርትቷል፣ በከባድ ፀሐይ ሲቃጠሉ የነበሩ ቦታዎች በከባድ ዝናብ እና ጎርፍ እየተመቱ ነው።
ዝናቡ ከመደበኛው ከፍ ያለ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች የበረዶ ግግር እስከ መፍጠር ደርሷል። እንዲሁም ጎርፉ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ሪፖርት ተደርጓል።
በዚህም ሳቢያ ከየካቲት 17/2015 ዓ.ም. በኋላ በነበረው የበልግ ወቅት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌ፣ በደቡብ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ እና በአዲስ አበባ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ በርካታ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ አጋጥሟቸዋል።
የበልጉ የአየር ሁኔታ በተጠቀሱት ክልሎች እና ከተሞች ውስጥ በሚገኙ 48 ቦታዎች ከሚጠበቀው በላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንዲያስተናግዱ ምክንያት እንደሆነ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለቢቢሲ ገልጻል።
በተለይ ባለፉት 10 ቀናት በእነዚህ አከባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ መመዝገቡን በኢንስቲትዩቱ ሚቲዎሮሎጂ ትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ይህ የበልግ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በአዲስ አበባ አራት ሰዎች እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል።
ከየካቲት 1 እስከ ግንቦት 30/2015 ዓ.ም. በሚዘልቀው የበልግ ወቅት አጋማሽ ከ30 እስከ 150 ሚሊ ሜትር መመዝገቡንም ኃላፊው ገልጸዋል።
ምን ማለት ነው?
አሳምነው (ዶ/ር) በሚቲዎሮሎጂ ቋንቋ የዝናብ መጠን በሦስት እንደሚከፈል ያስረዳሉ። ከ1 እስከ 10 ሚሊ ሜትር ያለ ዝናብ ቀላል መጠን ያለው በመባል ይገለጻል።
ከ10 እስከ 29 ሚሊ ሜትር ያለው ዝናብ መካከለኛ የዝናብ መጠን ተብሎ ሲቀመጥ፣ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ የሆነ ዝናብ መጠን ደግሞ ከፍተኛ ተብሎ ይጠቀሳል።
ያለፉት 10 ቀናት [ከመጋቢት 2 አስከ 12/2015 ዓ.ም] የዝናብ የነበረው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ከዚህ ቀደም ከነበሩት የበልግ ወቅቶች ጋር ሲነጻጸር “በጣም ከመደበኛ በላይ ሆኗል” ይላሉ ባለሙያው።

የፎቶው ባለመብት, South Radio and Television Agency
የበልግ ዝናብ እና የድርቅ አካባቢዎች
የበልግ ወቅት ለአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች እስከ 55 በመቶ የሚሆን ድርሻን የሚይዝ ዋነኛ የዝናብ ወቅት መሆኑን የሚያነሱት አሳምነው (ዶ/ር) ሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው።
ጨምረውም አሁን በድርቅ የተጉዱት እና በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ አካባቢዎች ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ወቅቶች ከመደበኛ በታች የሆነ የዝናብ መጠን እንደነበራቸው ያስታውሳሉ።
በሶማሌ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ ክልሎች እንዲሁም በኦሮሚያ በጉጂ እና በቦረና ዞኖች ይህ የበልግ ወቅት ዋነኛ የዝናብ ወቅት ነው።
ለአፋር እና ለሐረሪ ክልሎች፣ ለደቡብ ትግራይ፣ ለምሥራቅ አማራ፣ ለድሬዳዋ፣ ለአዲስ አበባ እና ለሌሎች የማዕከላዊ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ደግሞ ሁለተኛ የዝናብ ወቅት ነው።
አሳምነው (ዶ/ር) የበልግ ወቅት ዋነኛ የዝናብ ምንጫቸው የሆኑ አካባቢዎች ዝናብ ዘግይቶ ቢጀምርም “ጥሩ” መደበኛ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ ኢንስቲትዩቱ ቀደም ብሎ እንደተነበየ ገልጸዋል።
በዚህ መሠረትም በተለይ በድርቅ ተጽዕኖ ስር ያሉ አካባቢዎችን ጨምሮ በልግ ዋነኛ የዝናብ ምንጭ በሆነባቸው አብዛኛው አካባቢዎች ከየካቲት 30 ጀምሮ ቀላል እና መካከለኛ ዝናብ ተመዝግቧል። እንዲሁም በተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ጥሏል።
በሶማሌ ክልልም ፊቅ፣ ቀብሪ ደሃር እና ጎዴ በሚሊ ሜትር እስከ 150 የደረሰ “እጅግ ከባድ ዝናብ” የጣለ ሲሆን፣ በተለይ በፊቅ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የጣለ ከባድ ዝናብ ተመዝግቧል።
በተመሳሳይ በቦሬ ከ30 እስከ 80 ሚሊሜትር ለሦስት ተከታታይ ቀናት ዝናብ ተመዝግቧል።
በሌላ በኩል በሞያሌ 43 እና 32 ሚሊሜትር መጠን ያለው ዝናብ ለሁለት ተከታታይ ቀናት አስተናግዷል። በሜጋ 35 እንዲሁም በያቤሎ 65 ሚሊ ሜትር መጠን ያለው ዝናብ የጣለ ሲሆን፣ በጉጂ እና በቦረናም የበልግ ዝናብ መጣሉን ኃላፊው ተናግረዋል።
እናም በዚህ የበልግ ወቅት አካባቢዎቹ ከቀላል እስከ ከባድ ዝናብ ማስተናገዳቸው ለገጠማቸው ድርቅ “ለጊዜውም ቢሆን” መፍትሄ እንደሚያስገኝ ነው ኃላፊው የገለጹት።
የሰው እና የእንስሳት የመጠጥ ውሃን ለማሻሻል እንዲሁም በአጭር ጊዜ ሊሰበሰብ የሚችል የእንስሳት መኖን ለመዝራት ያግዛል ብለዋል። በተጨማሪም የበልግ እርሻን ለመጀመር “ምቹ ሁኔታን” ይፈጥራል።

የፎቶው ባለመብት, gofa zone communication
የበልግ ዝናብ እና ያስከተለው የጎርፍ አደጋ
ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የትንበያ እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር)፣ በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆነባቸው አከባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ መመዝገቡን አመልክተው በአንዳንድ አካቢዎች ከፍተኛ ዝናብ መጣሉን ጠቁመዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች ባሉ በርካታ ቦታዎች ላይ ቀላል እና መካከለኛ ዝናብ ቢመዘገብም በ48 አካባቢዎች ላይ ከባድ ዝናብ ጥሏል።
በአፋር ክልል ጭፍራ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ በ24 ሰዓት ውስጥ 104 ሚሊ ሜትር የሆነ ከፍተኛ ዝናብ አስተናግዷል።
በዚህ ስፍራ 104፣ 51፣ 42ና 30 ሚሊ ሜትር የሆነ የዝናብ መጠን ለአራት ተከታታይ ቀናት መዝነቡን የጠቀሱት ባለሙያው በሰመራ እና ዱብቲም ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ መመዝገቡን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢም ለሦሶስት ተከታታይ ቀናት በ24 ሰዓት ውስጥ 51፣ 41 እና 37 ሚሊ ሜትር ዝናብ የጣለ ሲሆን፣ በልግ ሁለተኛ የዝናብ ምንጭ በሆነባቸው በሌሎችም አካባቢዎች ከየካቲት 17 ጀምሮ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ተከስቷል።
በአዲስ አበባ የዘንድሮ የበልግ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን የከተማዋ የእሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ንጋቱ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 09/2015 ዓ.ም. ምሽት በንፍስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በአንድ ቤት ውስጥ ጎርፍ ገብቶ፣ የአራት ሰዎች አስክሬን በማግስቱ ዕሁድ መገኘቱን ገልጸዋል።
ኃላፊው በበልግ ዝናብ ምክንያት በተከሰተ አደጋ በአዲስ አበባ የሰው ሞት በኮሚሽናቸው ተመዘግቦ እንደማያውቅ ገልጸው፣ ካለፉት ጊዜያት አንጻር የዘንድሮው ከባድ መሆኑን አንስተዋል።
አዲስ አበባ የፍሳሽ ማሰወገጃ የላትም ያሉት አቶ ንጋቱ፣ ቀደም ሲል የተሰሩት የፍሳሽ መሰመሮች ከተማዋ አሁን ካለችበት ሁኔታ ጋር የማይመጣጠኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
እነዚህ መስሮች “ትንሽ ምክንያት ነው የሚፈልጉት” የሚሉት ኃላፊው ከሚጣልባቸው “ባዕድ ነገሮች” ጋር ተዳምሮ ከተማዋ ላይ በትኛውም ወቅት የሚጥል ከባድ ዝናብ የጎርፍ አደጋ ስጋት እንደሚጭር ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ወንዝ ዳርቻዎች ላይ “በተለምዶ ጨረቃ ቤት የሚባሉት” ጥልቀት በሌለው መሠረት ላይ የሚገነቡ በመሆናቸው የአደጋ መነሻ እንደሆኑ አስረድተዋል።
በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ባለፈው ሰኞ መጋቢት 11/2015 ዓ.ም. ምሽት የጣለው ዝናብ ለአንድ ሰው ህልፈት ምክንያት መሆኑን የዞኖ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስፍሯል።
ጎርፉ አንድ ሰው ላይም ከባድ የአካል ጉዳት ያደረሰ ሲሆን ሁለት የቀንድ ከብቶችንም ገድሏል።
በትምህርት ቤት፣ በጤና ኬላ እና በቀበሌ አስተዳደር ጸህፈት ቤት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱም የተገለጸ ሲሆን፣ በሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱም ተገልጿል።
በተጨማሪም በድርቅ ክፉኛ በተጎዳው በደቡብ ኦሞ በናጸማይ ወረዳ ከአራት ዓመታት በኋላ የጣለው ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ “ታይቶ የማይታወቅ” ሁኔታ በንብረት ላይ ጉዳት ማስከተሉን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
የዘንድሮ የበልግ ዝናብ ለምን በረታ?
እንደ አሳምነው (ዶ/ር) ገለጻ በዝናብ ሁኔታ ላይ በውቂያኖሶች፣ በከባቢ አየር ውስጥ እና በየብስ የሚከሰቱ የአየር ሁኔታዎች ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያሳርፋሉ።
ጉዳዩን በድርቅ በተጎዱት እና የበልግ ወቅት ዝናብ ዋነኛ የዝናብ ምንጫቸው ከሆነ አከባቢዎች ጋር አያይዘው ሲያስረዱ፣ ባለፉት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች የተከሰቱ ተፈጥሯዊ ለውጦችን ይጠቅሳሉ።
ባለፉት አምስት የዝናብ ወቅቶች የምሥራቅ እና መካከለኛው ፓስፊክ እንዲሁም የምዕራባዊ ሕንድ ውቅያኖስ ከመደበኛው በታች ቀዝቅዘው እንደነበር አሳምነው (ዶ/ር) ይናገራሉ።
በተለይም ይህ ሁኔታ ባለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ የጠነከረ ነበር። ይህም ማለት በኢትዮጵያ የሚጠበቀው ዝናብ እንዳይከሰት ያደርጋል።
ሆኖም በዚህ ወቅት ውቅያኖሶዎቹ ወደ መደበኛ ሁኔታ በመመለሳቸው ለዝናብ መፈጠር ምቹ የሆነ ሁኔታ አስከትሏል።
በሌላ በኩል በአረብ ባሕር እና በቀይ ባሕር ላይ የመሞቅ ሁኔታ ታይቷል። በዚህም ምክንያት የተጠናከረ እርጥበት አዘል አየር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ አድርጓል።
በዚህም ሳቢያ አካባቢዎቹ “ጥሩ” ዝናብ ማግኘት ችለዋል፤ በማለት ዶክተር አሳምነው ተሾመ የዘንድሮው የበልግ ወቅት ዝናብ የበረታበተን ምክንያት አስረድተዋል።












