በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከቧንቧ የተቀዳው ሰማያዊ ውሃ ምርመራ እየተደረገበት ነው

የፎቶው ባለመብት, @_ntombim_
ከደቡብ አፍሪካ ታላላቅ ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው ጆሃንስበርግ ውስጥ ውሃ ለመቅዳት ቧንቧዋን የከፈተች ነዋሪ ያጋጠማት ነገር ከእሷ አልፎ ሌሎችን አስደንግጧል።
ንጹህ ውሃ የፈለገችው የጆሃንስበርግ ከተማ ነዋሪዋ ያገኘችው ሰማያዊ ፈሳሽ ሲሆን፣ የከተማዋ ባለሥልጣናትም የዚህ ያልተጠበቀ ክስተት ምክንያቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ ምርመራ ማድረግ ጀምረዋል።
የደቡብ አፍሪካ ትልቋ የንግድ መናኸሪያ በሆነችው ከተማ በሚገኝ ሕንጻ ነዋሪ የሆነችው ሴት ሰኞ ዕለት ከቧንቧዋ ኩልል ያለ ውሃ ጥብቃ፣ ያጋጠማትን ሰማያዊ ቀለም የመሰለውን ውሃ የሚያሳዩ ምስሎች እና ቪዲዮዎችን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አጋርታለች።
በርካታ ነዋሪዎችም ለእራሳቸው እና ለቤተሰባቸው ደኅንነት በመስጋት ፍርሃታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ለጆሃንስበርግ ከተማ የውሃ አገልግሎት የሚያቀርበው ተቋም ቃል አቀባይ ክስተቱን አስመልክተው እንደተናገሩት፣ ውሃው በሕንጻው ውስጥ ባለ ንጥረ ነገር ተበክሎ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ እንዳለቸው ገልጸዋል።
ለውሃው ቀለም መቀየር ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ እና እርምጃ ለመውሰድ፣ ናሙና ተወሰዶ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የከተማዋ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ቃል አቀባዩ ፑሌንግ ሚፔሊ እንዳሉት በውሃ ናሙናው ላይ የሚደረገው የምርመራ ውጤት በ24 ሰዓታት ውስጥ ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የውሃው ቀለም መቀየርን ሪፖርት ያደረገችው ግለሰብም፣ ድንጋጤን የፈጠረባት ከቤቷ ቧንቧ ሲፈስ የነበረው ሰማያዊ ውሃ መቆሙንም ተናግራለች።
በውሃው ናሙና ላይ የሚደረገው ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ ውሃው ቀለም የተቀየረበት ምክንያት፣ ይህ እንዴት እንደተከሰተ እንዲሁም በጤና ላይ የሚያስከትለው ጠንቅን በተመለከተ ባለሥልጣናት ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።












