ሩሲያ በኑክሌር ኃይል ሚሠራ አዲስ ተወንጫፊ ሚሳኤል በተሳካ ሁኔታ መሞከሯን አስታወቀች

ሩሲያ በኑክሌር ኃይል የሚሠራ አዲስ የተወንጫፊ ሚሳኤል “የመጨረሻ ስኬታማ ሙከራ” ማድረጓን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስታወቁ።

ከአምስት ዓመት በፊት በሙከራ ደረጃ ላይ መሆኑ ሲገለጽ የነበረው ይህ ተወንጫፊ ሚሳኤል፣ ያልተገደበ ርቀት ተጉዞ ጥቃት ማድረስ የሚችል መሆኑ ተነግሮለታል።

ነገር ግን የጦር መሳሪያው ያለው ብቃት ምን እንደሆነ በይፋ የሚታወቀው የተወሰነ ነገር ነው። ከዚህ ቀደም የተደረጉ ሙከራዎች ከሽፈው እንደነበር ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

አዲሱን ሚሳኤል በተመለከተ ፕሬዝዳንት ፑቲን አሁን ይፋ ያደረጉት መረጃ በገለልተኛ ወገን ያልተረጋገጠ እና የሩሲያም መከላከያ ሚኒስቴርም ምንም አይነት መግለጫ ያለስጠበት ነው።

በዚህ የመስከረም ወር የወጡ የሳተላይት መስሎች እንደሚያሳዩት ግን ሶቪየት ኅብረት የኑክሌር መከራ ታደርግበት በነበረው የአርክቲክ ደሴት ላይ ሩሲያ አዲስ የኑክሌር የሙከራ ማዕከል መገንባቷን አመልክተዋል።

“ከጥቂት ዓመታት በፊት ባሳወቅኩት መሠረት አሁን ዘመናዊ ስልታዊ የጦር መሳሪያ አይነቶችን የመገንባት ሥራችንን አጠናቀናል” ሲሉ ፕሬዝዳንት ፑቲን በጥቁር ባሕር የመዝናኛ ከተማ ከተማ ሶቺ በተደረገ ስብሰባ በቀጥታ በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው ይፋ አድርገዋል።

ፑቲን ጨምረውም በኑክሌር ኃይል የሚሠራው እና በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝን ኢላማ ሊመታ ይችላል ያሉት “ቡሬቬስተኒከ” የተባለው ይህ እጅግ ዘመናዊ ሚሳኤል “የመጨረሻ እና የተሳካ ሙከራ ተደርጓል” ብለዋል።

የጦር መሳሪያ ቁጥጥር እንዲደረግ ዘመቻ የሚያደርገው ቡድን፣ ሩሲያ ይህንን ተወንጫፊ ሚሳኤል እውን ለማድረግ ቀደም ሲል ያደረጋቻቸው 13 ሙከራዎች የተሳኩ እንዳልነበሩ ለኒው ዮርክ ታይምስ ገልጿል።

ፑቲን በንግግራቸው ጨምረው እንዳመለከቱት “ሳርማት” ተብሎ የሚጠራ አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳኤል ለመገንባት እየተከናወነ ያለው ሥራ ከሞላ ጎደል ተጠናቋል።

ፕዝዳንቱ ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያን ጥቅም ላይ የምታውልባቸውን ሁኔታዎች በተመለከተ የተለወጠ አቋም እንደሌለ ገልጸው፣ አገራቸው ምንም የሚያሰጋት ነገር እንደሌለ እና “ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው” በሩሲያ ላይ የኑክሌር ጥቃት ለመፈጸም አያስብም ብለዋል።

ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 1996 ካጸደቀችው አጠቃላይ የኑክሌር ሙከራ እገዳ ስምምነት ልትወጣ እንደምትችል ያመለከቱት ፑቲን፣ ለዚህም አሜሪካ ስምምነቱን ብትፈርምም አለማጽደቋን በመከራከሪያነት ጠቅሰው ሩሲያም ተመሳሳይ መንገድን እንደምትከተል ተናግረዋል።

በዚሁ ስብሰባ ላይ ፑቲን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ በአውሮፕላን አደጋ ሕይወቱ ያለፈው የቫግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን እና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሞት ምክንያቱ የሚሳኤል ጥቃትን የመሰለ “ውጫዊ እርምጃ አይደለም” ሲሉ ተናገረዋል።

“ከአንድ ቀን በፊት የመርማሪ ኮሚቴው መሪ ሪፖርት እንዳደረገልኝ በአደጋው በሞቱ ሰዎች አካል ላይ የፈንጂ ፍንጣሪዎች ተገኝተዋል።”

ነገር ግን ፑቲን እንዴት ፈንጂ አውሮፕላኑ ውስጥ ሊፈነዳ እንደቻለ ያላብራሩ ሲሆን፣ በአደጋው ሰለባዎች አስከሬን ላይ መርማሪዎች የዕጽ እና የአልኮል ምርመራ ማድረግ አለባቸው ብለው እንደሚያስቡ ገልጸዋል።

አስካሁን የቫግነር ቡድን መሪ እና የቡድኑ አባላትን ይዞ በነበረው አውሮፕላን ላይ ለደረሰው አደጋ ምክንያቱ ምን እንደሆነ የሚገልጽ የወጣ ይፋዊ ሪፖርት የለም።