በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እየተሰማ ያለው አነጋጋሪው “የአልበሽር ድምጽ”

ሱዳንን ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በፈላጭ ቆራጭነት የገዙት ኦማር ሐሰን አል በሽር በቅርቡ “ድምጻቸው” ተሰምቷል።

የቀድሞው የሱዳን መሪ አልበሽርን አስመስሎ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) በመጠቀም የተላለፈው መልዕክት ቲክቶክ ላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዕይታ ነበረው።

ይህ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ለምትገኘው ሱዳን ሌላ የኢንተርኔት ውዥንብር ምክንያት ሆኗል።

ማንነቱ ባልታወቀ የቲክቶክ ገጽ ከነሐሴ መገባደጃ ወዲህ “በድብቅ ተቀርጸው የወጡ” የቀድሞው ፕሬዝዳንት ናቸው ያላቸውን ድምጾች እየለጠፈ ነው። ገጹ የበሽርን በርካታ ድምጾችን ቢለቅም ድምጾቹ ግን ትክክለኛ አይደሉም።

የጦር ወንጀሎችን በመፈጸም የተከሰሱት እና በ2019 በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን የተገረሰሱት አልበሽር ለአንድ ዓመት ያህል በአደባባይ አልታዩም።

በጠና እንደታመሙም ይታመናል። አልበሽር የቀረቡባቸውን የጦር ወንጀሎች አይቀበሏቸውም።

ያሉበት ቦታ እንቆቅልሽ በሆነበት በዚህ ወቅት አገሪቱ በጦር ሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል በሚደረገው ጦርነት እየተናጠች ትገኛለች።

አዳዲስ ዘዴዎችን በመጠቀም የሐሰተኛ መረጃዎችን በፍጥነት እና ርካሽ በሆነ መንገድ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች እንዴት እንደሚያሰራጩ ስለሚያሳዩ እንደዚህ አይነት ዘመቻዎች ጠቃሚ ናቸው ይላሉ ባለሙያዎች።

በካሊፎርኒያ በርክሌይ ዩንቨርስቲ የዲጂታል ፎረንሲክ ጥናት ያደረጉት ሃኒ ፋሪድ “የተራቀቀ የድምጽ እና የተንቀሳቃሽ ምስሎች ማጭበርበር የቴክኖሎጂ ለሁሉም ተደራሽ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ያስጨንቀኛል” ይላሉ።

“የተራቀቁ ጥቂቶች ለብዙ አሥርት ዓመታት እውነታውን በማጣመም ይጠበቡበት ነበር። አሁን ግን ትንሽ የቴክኒክ ዕውቀት ያለው ማንኛውም ሰው በፍጥነት እና በቀላሉ ሐሰተኛ ይዘት መፍጠር ይችላል” ብለዋል።

ቅጂዎቹ “ዘ ቮይስ ኦፍ ሱዳን” በሚባል ገጽ ላይ ተለጥፈዋል። ልጥፎቹ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት ከተሰጡ ጋዜጣዊ መግለጫዎች የተወሰዱ የቆዩ ቅጂዎች፣ የዜና ዘገባዎች እና አልበሽር ተናግረዋቸዋል የተባሉ በርካታ “በድብቅ ተቀርጸው የተለቀቁ ቅጂዎችን” ያሰባጠረ ይመስላል።

አብዛኞቹ የድምጽ ልጥፎች ከስብሰባ ወይም ከስልክ ውይይት የተወሰዱ ይመስላሉ። ድምጾቹም ጥራት የሌላቸው እና ከመጥፎ የስልክ መስመር የተቀረጹ ይመስላሉ።

ትክክለኛነታቸውን ለማረጋገጥ የቢቢሲ ሞኒተሪንግ የሱዳን ባለሙያዎችን ተጠይቀው ነበር። በዚህም ኢብራሂም ሃይታር የቅርብ ጊዜ ላይሆኑ እንደሚችሉ ተናግሯል።

“ድምፁ የበሽርን ቢመስልም ላለፉት ጥቂት ዓመታት በጣም ታመዋል። በመሆኑም ጥርት አድርጎ ስለመናገራቸው ያጠራጥራል።”

ይህ ግን እሱ አይደለም ማለት አይደለም።

ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች አማራጮችንም መርምረናል። ቅጂዎቹ ዳግም የተለቀቁ የድሮ ድምጽ አይደሉም። ድምጽ በሚያስመስል ሰውም የተሠራ ሊሆን የመቻሉም ነገር አጠራጣሪ ነው።

የተሻለ የሚባለው መደምደሚያ ያለው ማስረጃ የመጣው ኤክስ (በቀድሞ አጠራሩ ትዊተር) ላይ ካለ ተጠቃሚ ነው።

የመጀመሪያዎቹ የበሽር የድምጽ ቅጂዎች በነሐሴ 2023 ነበር የተለጠፉት። በዚህም የቀድሞው ፕሬዝዳንት የሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃንን ይተቻሉ።

የበሽር ድምጽ አል ኢንሲራፊ ተብሎ የሚጠራው ታዋቂ ሱዳናዊ የፖለቲካ ተንታኝ ከሁለት ቀናት በፊት ካስተላለፈው የፌስቡክ ቀጥታ ስርጭት ጋር ተመሳሳይ ነው። የግለሰቡ መኖሪያ አሜሪካ ነው ይባል እንጂ ፊቱን አሳይቶ አያውቅም።

ሁለቱ ተመሳሳይ ባይሆኑም ግን የሚናገሩት ነገር አንድ ነው። ሁለቱንም ድምጾች አንድ ላይ ቢያጫውቱ እኩል ይጫወታሉ።

የድምጽ ሞገዶችን በማወዳደርም በንግግር እና በዝምታ ወቅት ተመሳሳይ ዘይቤዎች እንዳላቸው ያሳያል ሲል ፋሪድ ይናገራል።

በዚህም በድምጽ መለወጫ መተግበሪያ (ሶፍትዌር) የበሽርን ንግግር ለማስመሰል ጥቅም ላይ እንደዋለ ማስረጃው ይጠቁማል። መተግበሪያው አንድን ድምጽ በመጫን ወደሚፈልጉት ሰው የድምጽ ዓይነት መቀየር የሚያስችል ኃይለኛ መሳሪያ ነው።

ከተጨማሪ ምርመራ በኋላም በተመሳሳይ መልኩ ጥቅም ላይ የዋሉ ድምጾች ተገኙ። ከተመሳሳይ ጦማሪ የቀጥታ ስርጭቶች የተወሰዱ ቢያንስ አራት ተጨማሪ የበሽር ድምጾችን ተገኝተናል። ግለሰቡ በዚህ ጉዳይ ስለመሳተፉ ምንም ማስረጃ አልተገኘም።

የቲክቶክ ገጹ ትኩረቱን ፖለቲካ ላይ ብቻ አድርጓል። በሱዳን ውስጥ ስላለው ሁኔታ ጥልቅ ዕውቀትን ቢፈልግም ከዚህ ዘመቻ የሚጠቀመው ማን ነው? የሚለው ለክርክር የሚቀርብ ነው። ወጥ የሆነው ጉዳይ ግን የጦሩን መሪ ጄኔራል ቡርሃንን መተቸቱ ነው።

ዓላማው በሽር በጦርነቱ ውስጥ የራሳቸውን ሚና ለመጫወት ብቅ ብለዋል ብለው እንዲያምኑ ተመልካቾችን ለማታለል ሊሆን ይችላል።

ወይም ደግሞ የቀድሞውን መሪ ድምጽ በመጠቀም የተለየ የፖለቲካ አመለካከትን ሕጋዊ ለማድረግ እየሞከረም ሊሆን ይችላል። ይህ ምን ሊሆን እንደሚችል ግን ግልጽ አይደለም።

ዘ ቮይስ ኦፍ ሱዳን ሕዝቡን እያሳሳተ ነው መባሉን አስተባብሏል። ከየትኛውም ቡድን ጋር ግንኙነት እንደሌለውም ተናግሯል። ገጹን አነጋግረን “ሃሳቤን ማስተላለፍ እና ስለአገሬ በራሴ መንገድ የገባችበትን እውነታ ማስረዳት እፈልጋለሁ” የሚል የጽሁፍ ምላሽ ደርሶናል።

በሽርን ለማስመሰል የሚደረገው ጥረት ተመልካቾችን የማታለል አቅም እንዳለው የቢቢሲ ሬዲዮ 4 ባልደረባው ሄንሪ አጀድር ይናገራል።

ሐሰተኛ ቪዲዮዎች እና ድምጾች ብጥብጥ ሊያስከትሉ እንዲሁም ምርጫዎችን ሊያደናቅፉ ወደሚችሉ የሐሰት መረጃ ማዕበል ሊመሩ እንደሚችሉ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ባለሙያዎች ለረዥም ጊዜ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።

“በጣም የሚያስደነግጠው እነዚህ ድምጾች፣ እውነተኛ ድምጾችን ጭምር የማይታመኑበትን ከባቢ መፍጠር መቻላቸው ነው” ሲሉ በኖርዝኢስተርን ዩኒቨርስቲ የሲቪክ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቤተሙከራ ተመራማሪው መሐመድ ሱሌይማን ይገልጻሉ።

ሐሰተኛ የድምጽን እንዴት እንለይ?

ሰዎች በተለያዩ መንገዶች በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት የሚያገኟቸውን መረጃዎች ከማጋራታቸው በፊት ስለትክክለኛነታቸው ማጣራት እና ማረጋገጥ አለባቸው።

በቀዳሚነት መረጃው ከሚታመን ምንጭ የተለቀቀ መሆኑን ማረጋገጥም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።

በተለይ በመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎች ላይ የሚዘዋወሩ ድምጾችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ከባድ ነው። አሁን በሱዳን እያለፈችበት ካለው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የሚፈጥሩት ችግር የበለጠ ፈታኝ ይሆናል።

ሰው ሠራሽ ድምጽ ለመለየት የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎች ገና በጅምር ላይ የሚገኙ ናቸው። ድምጾችን የማስመሰል ቴክኖሎጂ ደግሞ በጣም የላቀ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ይህንን አወዛጋቢ ድምጽ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያጋራ የነበረው ቲክቶክን ገጽ፣ ቢቢሲ ማብራሪያ ፈልጎ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ገጹ በአሁኑ ጊዜ ታግዷል።