ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
‘በአንድ ወቅት የሚያስደስቱኝ ነገሮች በሙሉ ትርጉም አጡብኝ፣ ከሰዎችም መሸሽ ጀመርኩ’
ቃለአብ በሰዎች የተከበበ ወዳጀ ብዙ ነው።
እሱ ባለበት ጨዋታ ይደምቃል። መሳቅ እና ሳቅ መፍጠር ልማዱ ነው። በእሱ ዙሪያ ያሉ ሁሉ ይህንን ያውቃሉ።
እሱም “በጣም ተጫዋች አይነት ሰው ነበርኩኝ” ይላል።
የሆነ ጊዜ ግን ደበተው። የሚያስደስቱት ነገር በሙሉ ‘አስጠሉት’። ለሁሉም ነገር ያለው ፍላጎት አሽቆለቆለ። ከጓደኞቹ መራቅ እና ብቸኝነት ምርጫው እየሆነ ሄደ።
“በጣም እነጫነጭ ነበር። ብቻዬን ስሆን በጣም ይከፋኛል። በጣም አለቅስ ነበር” ይላል ለሁለት ዓመት ገደማ የቆየበትን ሁኔታ ሲያስታውስ።
ቃለአብ በርካታ ወዳጆች ቢኖሩትም ችግሩን የተረዱለት ጥቂት ናቸው፤ ሁለት ጓደኞቹ ብቻ።
ለገባበት ችግር መነሻው ማስታወስ የማይፈልጋቸው የልጅነት ትዝታዎቹ እንደሆኑ ይናገራል። ይህም ከጊዜ በኋላ በተለይም በ22 እስከ በ23 ዓመቱ ከፍተኛ ድባቴ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆኗል።
ለመሆኑ ድባቴ [ዲፕሬሽን] ምንድን ነው?
በዚህ ችግር ውስጥ ያለፈው ቃለአብ ሰለሞን ድባቴ “በሕይወት ያለ ሰው ማድረግ የሚገባውን ነገር እንዳያደርግ ወደኋላ የሚጎትት ስሜት” ነው ይላል። ይህ እራሱ ካለፈበት ሁኔታ በመነሳት የሰጠው ትርጓሜ ነው።
ሰላም አታላይ ደግሞ “ከትላንት የምናመጣው ቁስል ተደራርቦ የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን ሲጎዳ፣ ትላንት የሚያስደስተን ነገር ትርጉሙ በደንገት ጥያቄ ውስጥ ከገባ” ያ ድባቴ ሊሆን እንደሚችል ትናገራለች።
“ድባቴ ውስጥ ስንሆን ‘እዚህ ምድር ላይ ብኖርም፣ ባልኖርም የምጨምረው የምቀንሰው ነገር የለም፤ ስለእኔ ግድ ያለው ሰው የለም፤ ወይም በሕይወት ውስጥ እየኖርኩ እየሞላሁት ያለሁት ነገር የለም...በሕይወት ውስጥ ያለኝ ዋጋ ምንም አይደለም’ የሚለው ክፉ ድምጽ በጣም እየጎላ ይመጣል” ስትል ታስረዳለች።
ሰላም የሥነ ልቦና አማካሪ ናት። እሷም በአንድ ወቅት በድባቴ ውስጥ አልፋ ይህንን ስሜት አስተናግዳለች።
የሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለች ነበር ይህ ያጋጠማት።
“የመጀመሪያ ዓመትን እንደቀልድ ነበር የተማርኩት” ትላለች - ሰላም። የከባቢዋ መቀየር ድባቴ ውስጥ ለመግባቷ ምክንያት እንደሆነ ትጠቅሳለች።
ብዙ ሰዎች ድባቴን ቀላል አደርገው ይቆጥሩታል የሚለውን ሀሳብ ቃለአብ እና ሰላም ይስማሙበታል።
“አንዳንድ ሰዎች ‘እንዴ እንዲህ አይነት ጥሩ ኑሮ እየኖርክ እንዴት ታማራለህ? ምን ጎድሎብህ ነው? እኛ’ኮ ከዚህ የባሰ ነገር ውስጥ አለፈናል’ ይላሉ” ሲል ያስታውሳል ቃለአብ።
ሰላም ደግሞ “ድባቴ ውስጥ ከመግባት በላይ፣ በዙሪያችን ያለን ሰው የማይታይ ነገር ማስረዳት ነው የከበደኝ። ምክንያቱም እኛ አገር አንድ ሰው ‘ድባቴ ውስጥ ነኝ’ ካለ እንደቅብጠት ነው የሚታየው።...ስለዚህ ለማምለጥ የምሞክረው ለማንም ሰው ባለመናገር ነው” ትላለች።
ሰላም በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ያጠናችው ሥነ ልቦና ነው። በዙሪያዋ ያሉ ሰዎችም በተመሳሳይ የትምህርት መስክ እያሉ ያለችበትን ሁኔታ ለመረዳት አለመቻላቸው ድባቴን ምን ያህል ‘እንዳቀለልነው’ ያመለክታል ስትል ገልጻለች።
እውነታው ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው።
የሥነ አእምሮ ሐኪሙ ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ፣ በድባቴ ከተያዙ ሰዎች 15 በመቶዎቹ ራሳቸውን እንደሚያጠፉ በጥናቶች መረጋገጡን ይናገራሉ። ይህንን መሠረት አድረገው “ድባቴ ገዳይ በሽታ ነው ልንል እንችላለን” ይላሉ።
ስለዚህ ድባቴ በቀላሉ የሚታይ የአእምሮ ጤና እክል አይደለም።
ፕሮፌሰር ሰለሞን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ አእምሮ ሐኪም ሲሆኑ፣ የሬናይሰንስ የአእምሮ ጤና እና የሱስ ተሃድሶ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ናቸው።
ፕሮፌሰሩ ድባቴ ከአእምሮ ህመሞች አንዱ እንደሆነ ጠቅሰው ከተለመዱ የአእምሮ ጤና መታወኮች (common mental disorders) ውስጥ እንደሚካተት አስረድተዋል።
ይህ የአእምሮ ጤና ችግር ከአጠቃላይ ሕብረተሰቡ ከ5 እስከ 10 በመቶው የሚሆነው ላይ ሊከሰት እንደሚችል ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ይናገራሉ።
አእምሮ የማሰብ፣ የስሜት እና የባህሪ ተግባራት አሉት። ድባቴ ከእነዚህ ውስጥ የስሜት ተግባርን የሚያስተጓጉል (mood disorder) እንደሆነም ፕሮፌሰሩ ጠቅሰዋል።
ድባቴ ከባድ፣ መካከለኛ እና ቀላል ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፣ ከባድ ድባቴ በራሱ የተለያዩ ደረጃዎች ያሉት ነው።
የድባቴ መነሻ እና መገለጫዎቹ ምንድን ናቸው?
“ከልጅነቴም የብቸኝነት ስሜት በጣም ይሰማኛል” የሚለው ቃለአብ፣ በልጅነት ዘመኑ ያሳለፋቸው ‘መጥፎ ጊዜያት’ የድባቴው መነሻ ናቸው።
በዚህ ዘመን ቃለአብ ‘የመጣል’ አይነት ስሜት ተሰምቶታል። ያም ቅያሜን ወልዷል።
ከዓመታት በኋላ በፍቅር ሕይወቱ የገጠመው ችግር ከልጅነቱ መጥፎ ትዝታዎች ጋር ተዳምረው ለድባቴ አጋልጠውታል።
ይህን “ወደ ኃይለኛ ጭንቀት (anxiety) ተቀየረ። ነፍሴ ይቁነጠነጣል። ሀሳቤ ሁሉም ቦታ ይበታተናል - አንድ ቦታ አያርፉም። ከልቤ የማደርገው አንድ ነገር የለም” ሲል ይናገራል።
ብቸኝነትን፣ መከፋት፣ ማልቀስ እና ትዕግስት ማጣት መገለጫዎቹ ሆነው ነበር።
ቃለአብ ብቸኝነቱን አጥብቆ ይሸሸው ነበር። ለምን?
“[ብቻዬን ስሆን] ሀሳቦቼን አልወዳቸውም። እነዙያን ሀሳቦች አጉልቼ ማሰብ አልፈልግም።...ከሰው ጋር ስሆን ደግሞ ከትክክለኛው ሰው ጋር መሆን ባለብኝ ጊዜ እና ቦታ እንዳለሁ አይሰማኝም።...ጭንቅላቴ ከትክክለኛው ሰው ጋር አይደለህም የሚል ኃይለኛ ሀሳብ ያስባል” ይላል።
ብቻውን ሲሆን ወደ አእምሮ የሚመጡ ሀሳቦች ከባድ ናቸው። አብዛኛቹ አሉታዊ መልክም አላቸው።
“በዚያ ሰዓት አስበው የነበረው ትልቁ ነገር ራስን ስለማጥፋት ነው። ‘የመኖሬ ትርጉም ምንድን ነው? ማነኝ?’ የሚሉ ጥያቄዎች ናቸው። ይሄ ደግሞ የመጣው በልጅነቴ የነበረው የመተው እና የብቸኝነት ስሜት ነው፤ [ቤተሰቦቼ] እንክብካቤ ያደረጉልኝ አይመስለኝም። ይህ ሁሉ ሀሳብ ከዚያ የመነጨ ነው” ይላል።
ሰላም አራት ወራት በቆየችበት የድባቴ ስሜት ወቅት የሚመጡባት ሀሳቦች ‘የሚወጡና የሚወርዱ’ ናቸው።
“ራሴን ያገለልኩ ሰሞን ‘ከሰው ጋር መሆን ሸክም ስለሆነ ከሰው ጋር መሆን የለብኝም’ የሚል ነበር። ከዚያ ቀስ እያለ እየተቀየረ መጣ። ግን ብዙ ጊዜ [ሃሳቦቹ] አሉታዊ ናቸው” ስትል ታስተውሳለች።
ፕሮፌሰር ሰለሞን ድባቴ በርካታ መገለጫዎች አሉት ይላሉ። ሁለቱ ግን መሠረታዊ ናቸው።
የመጀመሪያው “በከፍተኛ ሁኔታ የመደበት፣ የማዘን እና ደስታ የማጣት ስሜት” ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ “በፊት ያዝናኑ እና ያስደስቱ በነበሩ ነገሮች መደሰት ያለመቻል” እንደሆነ ያስረዳሉ።
“ከእነዚህ ሁለት ነገሮች አንዱ ካለ ድባቴ [መኖሩን] ጠቋሚ ነው።”
በአንጎል ውስጥ የሚመላለሰው የኃይል መጠን ስለሚያንስ የማሰብ ፍጥነት የመዘግየት ወይም “በአካልም ቀሰስተኛ ሆኖ መታየት” ሌላኛው የድባቴ ምልክት ነው።
የምግብ ፍላጎት ማጣት ወይም ደግሞ አልፎ አልፎ ከፍተኛ የምግብ ፍላጎት ማሳየትም የድባቴ ገጽታ ሊሆን ይችላል ይላሉ - ፕሮፌሰር ሰለሞን።
ምክንያት አልባ የድካም ስሜት፣ የትኩረት ማጣት/መርሳት፣ የአንቅልፍ መቀነስ/መዛባት ወይም አልፎ አልፎ መብዛት፣ አሉታዊ በሆኑ ሀሳቦች በከፍተኛ ሁኔታ መጠመድ እና የተጋነነ የጥፋተኝነት ስሜት፣ መኖርን መጥላት/ሞትን መመኘት እንዲሁም “የከፋ ደረጃ ሲደርስ” ራስን ስለማጥፋት ማሰብ ወይም መሞከር ሌሎቹ የድባቴ መገለጫዎች ናቸው።
እነዚህ ስሜቶች ቢያንስ ከሁለት ሳምንት በላይ በተከታታይ ሲታዩ ድባቴ መኖሩን ሊያመላክቱ ይችላሉ።
ፕሮፌሰር ሰለሞን እዚህ ጋር ሁለት መሠረታዊ ነጥቦችን ማስታወስ ያስፈልጋል ይላሉ፡
አንደኛ “ጊዜያዊ የሆኑ እና ለአጭር ጊዜ የሚሆኑ የስሜት መውረዶች ወይም የድብርት ስሜት ማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት ይችላል።”
ሁለተኛ በእነዚህ የስሜት ለውጦች “በከፍተኛ ሁኔታ የሚረብሽ፣ ሥራ መሥራት እና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ መሳተፍ በሚያስቸግር ደረጃ” ተጽዕኖ ካለው ከድባቴ ጋር ሊያያዝ ይችላል።
እናም ድባቴ በአንድ ነጠላ ስሜት የሚገለጽ ሳይሆን የብዙ ስሜቶች ድምር ነው።
ፕሮፌሰር ሰለሞን የድባቴ መንስኤዎችን ሲያስረዱ በዘር ሊተላለፍ እንደሚችል ይጠቅሳሉ።
ይህ ማለት ግን የድባቴ ተጋላጭነትን ይወርሳሉ እንጂ በቀጥታ በድባቴ ይያዛሉ ማለት አይደለም።
ሌላኛው ለከፍተኛ የአእምሮ ጫና/ጭንቀት መጋለጥ፣ የአእምሮ ጥቃት (Trauma)፣ በኑሮ ላይ የሚከሰት ጭንቅት፣ አካላዊ ጥቃቶች፣ መደፈርን ጨምሮ ጾታዊ ጥቃቶች ለድባቴ እና ለሌሎች የአእምሮ ጤና መታወክ ሊያጋልጡ የሚችሉ ምክንያቶች ናቸው።
በሌላ በኩል አልኮል እና አደንዛዥ ዕጾች፣ እንደ ካንሰር ያሉ ‘ስር ሰደድ’ በሽታዎች እና “አንዳንድ መድኃኒቶች” ለድባቴ ሊያጋልጡ እንደሚችሉም ተናግረዋል።
እነዚህ ውጪያዊ የድባቴ መንስኤዎች ተደርገው ሲቆጠሩ ውስጣዊ ምክንያቶችም አሉ።
“አንዳንድ ሰዎች ምንም አይነት ውጫዊ ምክንያት ሳይኖራቸው የድባቴ ምልክት ሊያሳዩ ይችላሉ። እነዚህ በአንጓላቸው ውስጥ ያሉ የአእምሮ መነቃቃትን የሚያስከትሉ አንዳንድ ንጥረ ነገሮች በሚጎድሉበት ጊዜ ወይም መጠናቸው በሚያንስ ጊዜ” ድባቴ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ፕሮፌሰር ሰለሞን ያስረዳሉ።
ከድባቴ መዳን ይችላል?
ሰላም ድባቴ ውስጥ በነበረችባቸው ጊዜ ከሰው ጋር ተቆራርጣለች።
ሰዎች የሚረዷት ሰለማይመስላት ስልክ አትመልስም ነበር።
“ያኔ ተራርቄ እስካሁን የቀሩብኝ ሰዎች አሉ” ትላለች። ሆኖም በድባቴ የቆየችባቸው ወራት ብዙ እንዳስተማሯት ትገልጻለች።
የቃለአብም ተመሳሳይ ነው።
እሱም በድባቴ ምክንያት ከሰዎች ጋር ተራርቋል፣ ‘ራሱን እንዳይሆን’፣ ‘ተነጫናጭ እንዲሆን’፣ ከሰዎች ጋር እንዳይነጋገር ሆኗል።
በቤተሰብ፣ በሥራ እና በፍቅር ሕይወቱ ላይም መስተጓጎል ተፈጥሯል።
እነዚህን የድባቴ ተጽዕኖ ብሎ ይዘርዝራቸው እንጂ “የተጠቀምኩት ይበልጣል” ይላል።
ከዚህ ስሜት ከወጣ በኋላ ራሱን እንዲረዳ፣ ለሰዎች ቦታ እንዲኖረው እና ይበልጥ ለመኖር እንዲጓጓ አደርጎታል።
ጥያቄው ከድባቴ እንዴት ወጣ የሚል ነው?
ቃለአብ ሌላ ከተማ ሊዝናና ወጥቶ ሳይዝናና ይመለሳል።
“አስታውሳለሁ እያለቀስኩ ነው ወደቤት የተመለስኩት። ይሄን ያህል ርቀት ሄጄ ደስተኛ መሆን ካልቻልኩኝ መቼ ነው ደስተኛ መሆን የምችለው? የሚል ስሜት ተሰማኝ። ያ [ለመውጣት] እንድወስን ረዳኝ” ይላል።
ከዚያም የሥነ አእምሮ ሐኪም አፈላልጎ አገኘ። ሐኪም ማግኘት ግን ቀላል እንዳልሆነ ይነናገራል - “ቢያንስ ሁለት ወር አፈላልጌያለሁ።”
“[የድባቴ ሕክምና] የት እንደሚገኝ አላውቅም፤ ማን እንደሚሰጥ አላውቅም። ኦንላይንም ብፈልግ የለም፣ ብጠይቅም የሚያውቅ ሰው አላገኘሁም” ሲል ይነገራል።
ይህም ሕክምናው ምን ያህል እንደ “ቅንጦት” እንደሚቆጠር አሳይቶታል።
“እኛ አገር ብዙ ችግር እና የተቸገሩ ሰዎች ስላሉ [ከአእምሮ ጋር የተገናኘ የጤና እክል] ሰዉ እንደቀልድ ነው የሚያየው። ይህ ነገር ያጋጠመው ሰው ካልሆነ በስተቀር ሌላው ሰው እንደቅንጦት ነው የሚመለከተው።”
የሆነው ሆኖ ቃለአብ የሥነ አእምሮ ሐኪም አገኝቶ የተደረገለትን ሕክምና በሚገባ ተከታትሏል። በዚህም ውጤት አግኝቷል።
“አሁን ከዚያ ጊዜ በጣም የተሻለ ሁኔታ ላይ ነኝ። አሁን ደስተኛ ነኝ። በድባቴ ምክንያት ያጋጥመኝ የነበረው ነገር አሁን የለም” ይላል።
ሰላምም በሌላ መንገድ ድባቴን ማሸነፍ ችላለች።
“የተማርኩት አክሱም ዩኒቨርሲቲ ነው። አክሱም ጽዮን ማሪያም እሄድ ነበር። እዚያ መሄድ ቀላል አደረገልኝ” ስትል ጠቅሳለች።
በተጨማሪም “ሰዎችን ማዋራት ጀመርኩኝ። ቀላል አልነበረም ግን ስልክ ማንሳት እና ከልቤ ማውራት ጀመርኩኝ” የምትለው ሰላም፣ የሕይወት ዘይቤዋን መቀየሯም ከድባቴ ለመውጣት ረድቷታል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መጀመሯን፣ ወደ ትምህርቷ ብቻ ለማተኮር መሞከሯ አራት ወር የቆየችበትን የድባቴ ስሜት ለመርታት አግዟታል።
ቃለአብም ይሁን ሰላም ከድባቴ ለመውጣት ቁልፍ የሚሉት ግን ‘ድባቴ ውስጥ ነኝ ብሎ’ ማመን ነው።
ፕሮፌሰር ሰለሞን ድባቴ በፍጥነት ከታከመ እንደሚድን ይናገራሉ። ጊዜ እየወሰደ በመጣ ቁጥር ሁኔታው ስር እየሰደደ ይሄዳል። ይህም ሕክምናውን አስቸጋሪ እያደረገው ይሄዳል።
ድባቴ የመጣበትን መሠረታዊ ምክንያት ለይቶ ማወቅ ችግሩን ለመቅረፍ ወሳኝ ነው ይላሉ።
ፕሮፌሰሩ ይህንን የአእምሮ ጤና እክል ለማከም ከዕለታዊ የሰውነት እንቅስቃሴ እስከ ኤሌክትሪክ ንዝረት ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ያስረዳሉ።
ከቀላል እስከ መካከለኛ ድባቴ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በሳምንት ሦስት ቀን ከ30 እስከ 40 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅቃሴ በማድረግ ድባቴን መግታት ይችላል።
“ጠንካራ የአካል ብቃት ማድረግ በራሱ ከድባቴ ለመላቀቅ የሚያግዝ አንድ ትልቅ ሕክምና ነው” ይላሉ ሐኪሙ።
ሆኖም ራስን እስከማጥፋት የሚያስቡ ወይም የሚሞከሩ ከባድ የድባቴ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች በመድኃኒት የታገዘ ወይም በሆስፒታል ውስጥ በመተኛት የሚሰጥ ሕክምና ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ይገልጻሉ።
በድባቴ ምክንያት መድኃኒት የጀመሩ ሰዎች ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት በአግባቡ መድኃኒት መውሰድ እንደሚገባ የሚጠቅሱት ፕሮፌሰር ሰለሞን “ብዙ ጊዜ ሰዎች ትንሽ ሲሻላቸው መደኃኒቱን ያቋርጡታል። ከዚያ ድባቴው ተመልሶ ሊመጣ ይችላል።”
በሌላ በኩል ድባቴ ሊያስከስት የሚችለው አደጋ በጣም ከፍ ያለ እና የከፋ ደረጃ ከደረሰ ደግሞ በኤሌክትሪክ ንዝረት አእምሮን የማነቃቃት ሕክምናን ጨምሮ ሌሎች “ጠንከር ያሉ” ድጋፎች ሊያስፈልጉ ይችላሉ።
ቃለአብ እና ሰላም ዛሬ
ቃለአብ ከ20 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት የቲክቶክ ገጹ ስለድባቴ መናገር ከጀመር ወራትን አስቆጥሯል።
እሱ ሕክምናውን ከመከታተል ባለፈ በሌሎች አገራት በዩቲዩብ አማካይነት ስለድባቴ ገለጻ የሚያደርጉ ሰዎችን መከታተሉ ከድባቴ ለመላቀቅ ረድቶታል።
እናም በአገሩ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች ‘ብቻቸውን እንዳልሆኑ’ ለመንገር እና ስለ ጉዳዩ የሚያውቀውን ለመግለጽ መነሻ ሆኖታል።
ይህ ተግባሩ ውጤት ማሳየት ጀምሯል።
የሚከታተሉት ሰዎች ‘እኔን የሚሰማኝን ነገር ስለምትናገር በጣም ደስ ይለናል፤ አንተ ከእንዲህ አይነት ነገር ወጥተህ ማየታችን፣ እኛም ነገ ከዚህ በመውጣት የተሻለ ነገር ላይ እንደምንደርስ ተስፋ ይሰጠናል’ የሚሉ አስተያየቶች ይደርሱታል።
ሰላምም እንዲሁ ቡና በተሰኘው የፖድካስት ፕሮግራም፣ እንዲሁም በሬዲዮ ከምታነሳቸው ሀሳቦች አንዱ ድባቴ ነው። ስለድባቴ ስታወራ ደግሞ ራሷ ያለፈችበትን መንገድ ጨምራ ነው።
“ራስ ምታት ሊያመን እንደሚችል ሁሉ፣ ድባቴም ሊከሰት ይችላል።...የተለመደ ነገር እንደሆነ ሲታሰብ ድባቴ ውስጥ የሚገቡ ሰዎችም እርዳታ መጠየቅ ይጀምራሉ። ለዚያ ነው እኔም እዚህ [ድባቴ] ላይ መሥራት የፈለኩት” ብላለች።