ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጋናዊው እግር ኳሰ ተጫዋች ክርስቲያን አትሱ በቱርክ ርዕደ መሬት ሳቢያ መሞቱ ተነረ
በቱርክ በደረሰው ርዕደ መሬቱ ምክንያት ደብዛው ጠፍቶ ሲፈለግ የነበረው ጋናዊው እግር ኳስ ተጫዋች ክርስቲያን አትሱ ሕይወቱ ማለፉ ተነገረ።
ርዕደ መሬቱ ከተከሰተ በኋላ ለሁለት ሳምንታት ተጫዋቹን ለማግኘት ፍለጋ ሲደረግ ቢቆይም ዛሬ የተጫዋቹ ወኪል ይፋ እንዳደረገው ክርስቲያን አትሱ በቤቱ ፍርስራሽ ውስጥ ሕይወቱ አልፎ ተገኝቷል።
ከአንድ ሳምንት በፊት የክርስቲያን አትሱ የፍቅር ጓደኛ ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቃለ መጠይቅ “አሁንም ጸሎት ላይ ነኝ። ደግሞም በሕይወት እንደማገኘው ተስፋ አደርጋለሁ” ብላ ነበር።
የመሬት መንቀጥቀጡን ተከትሎ አትሱ “ጉዳት ደርሶበት ተርፏል”ሲል የሚጫወትበት ክለብ ሃታይስፖር አሳውቆ የነበረ ቢሆንም፤ በኋላ ላይ በተደረገ ማጣራት እግር ኳስ ተጫዋቹ አለመገኘቱ ተረጋግጦ ቆይቷል።
“በሕይወት እንዲገኝ መልካም ምኞታችሁን ስትገልጹ ለነበራችሁ ሁሉ፤ ዛሬ ጠዋት የክርስቲያን አትሱ አስከሬን መገኘቱን የምነግራችሁ በታላቅ የልብ ስብራት ውስጥ ሆኜ ነው” በማለት የተጫዋቹ ወኪል ናና ሰቸሬ ትዊተር ላይ አስፍሯል።
“ለቤተሰቦቹ እና ለአፍቃሪዎቹ መጽናናትን እመኛለሁ። በጸሎት ያገዙንን ሁሉም ማመስገን እፈልጋለሁ” ብሏል ናና።
አትሱ የመጨረሻ ጨዋታውን በፈረንጆቹ የካቲት 05/2023 ሲያደርግ ለክለቡ የማሸነፊያዋን ግብ አስቆጥሮ ነበር። በማግስቱም ርዕደ መሬቱ ተከስቶ ያለበት ሁኔታ ሳይታወቅ ለሁለት ሳምንታት ያህል ቆይቷል።
የ31 ዓመቱ ክርስቲያን አትሱ ከእንግሊዙ ኒውካስል ዩናይትድ ጋር 107 ጨዋታዎችን አድርጓል። በተጨማሪም በቸልሲ፣ በኤቨርተን እና ቦርንማውዝ ክለቦች ውስጥ ተጫውቷል።
አትሱ በተጨማሪም አንድ የውድድር ዘመን ከሳዑዲ አረቢያው አል-ራኢድ ጋር ካሳለፈ በኋላ ባለፈው መስከረም ወር ነበር የቱርኩን ሃታይስፖርን የተቀላቀለው።
ለክርስቲያን አትሱ ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆነው እና በዓለምችን ካጋጠሙ አስከፊ ርዕደ መሬቶች መካከል አንዱ የሆነው አደጋ በአስር ሺዎችን ለሞት ዳርጓል።
ተጎራባቾቹን ደቡባዊ ቱርክ እና ሰሜናዊ ሶሪያ በመታው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በሁለቱ አገራት ውስጥ ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ተቀጥፏል።