አርሰናል ነጥብ እንዲጥል አድርገዋል የተባሉት ዳኛ ሊ ሜሰን ከፕሪሚየር ሊግ ዳኝነት ተሰናበቱ

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን በተደረገው የአርሰናል እና ብሬንትፎርድ ጨዋታ ላይ ስህተት ፈጽመዋል የተባሉት ዳኛ በስምምነት ከዳኝነት ተሰናበቱ።

በዚህም በርካታ የአርሰናል ደጋፊዎችን ያስቆጡት ሊ ሜሰን ከአሁን በኋላ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ዳኛ ሆነው አያጫውቱም።

ዳኛው የፕሪሚየር ሊጉን የዳኝነት ሚና ከሚመራው የፕሮፌሽናል የዳኞች ማኅበር (ፒጂኤምኦኤል) ጋር በተደረገ የሁለትዮሽ መግባባት በዳኝነት ሥራቸው እንዳይቀጥሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የ51 ዓመቱ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዳኛ ሜሰን፣ አርሰናል ከብሬንትፎርድ ጋር ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ሲለያዩ ከሰሩት የቫር [የቪዲዮ ዳኝነት] ስህተት ከቀናት በኋላ ነው ስንብታቸው የተሰማው።

የቪዲዮ ዳንነቱን ሲመሩ የነበሩት ሜሰን በጨዋታው ወቅት የመለያ መስመር ማስቀመጥ ሲገባቸው መስመሩን በመተው ብሬንትፎርድ ያስቆጠራትን ግብ አጽድቀዋል።

እንደ ቫር ዳኛ የቫር መመሪያ በሚያዘው መሠረት ሜሰን የኢቫን ቶኒን የአቻነት ግብ ከማጽደቃቸው በፊት መስመር ከማስመር ተቆጥበው ነበር።

“ሊ ሜሰን ለፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላበረከቱት ሁሉ እናመሰግናለን፣ ወደፊትም መልካሙ ሁሉ እንዲገጥማቸው እንመኛለን” ብሏል የዳኞች ማኅበሩ።

አርሰናል ከብሬንትፎርድ ጋር ነጥብ ተጋርቶ በሳምንቱ አጋማሽ በማንችስተር ሲቲ ሽንፈትን ሲያስተናግድ ለወራት ከነበረበት የመሪነት ደረጃ ተንሸራትቶ ሁለተኛ ላይ ተቀምጧል።

የፔፕ ጋርዲዮላው ማን ሲቲ ደግሞ በእኩል 51 ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ ፕሪሚየር ሊጉን የሚመራበት አጋጣሚ ተፈጥሮለታል።

ፕሮፌሽናል የዳኞች ማኅበር ሰብሳቢ ሃዋርድ ዌብ ከአርሰናል ጋር በመነጋገር የተሰራውን ስህተት እውቅና ሰጥተው ጉዳዩን አብራርተዋል።

የመድፈኞቹ አለቃ ማኬል አርቴታ ግን ይቅርታው ተቀባይነት የለውም፣ “ሰው ሰራሽ ስህተት አልነበረም፣ ሥራህን የማወቅ ችግር ነው።

“ይህም አርሰናል መልሶ የማያገኘውን ሁለት ነጥብ አሳጥቶታል። ያ በመሆኑም እነዚህን ነጥቦች ለማግኘት ሌላ ዋጋ ለመክፈል ተገደናል” ብሏል።

በቦልተን ተወልደው ያደጉት ሊ ሜሰን ለ15 ዓመታት የፕሪሚየር ሊግ ዳኛ በመሆን አገልግለዋል። 287 ታላላቅ ጨዋታዎችንም በዳኝነት መርተዋል።