የኳታሩ ሼክ ጃሲም ማንችስተር ዩናይትድን ለመግዛት መዘጋጀታቸውን አስታወቁ

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጉልህ ታሪክ ያለው እና በዘንድሮው የውድድር ዘመን ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንችስተር ዩናይትድን ለመግዛት ባለሃብቶች ጥያቄያ አቅርበዋል።

ከኳታር ትልልቅ ባንኮች የአንደኛው ሊቀ መንበር የሆኑት ሼክ ጃስሚ ቢን ሃማድ አል ታኒ ፋውንዴሽናቸው ማንችስተር ዩናይትድን ለመግዛት ጥያቄ ማቅረቡን አረጋግጠዋል።

ቢቢሲ መረዳት እንደቻለው የሰር ጂም ራትክሊፍ ንብረት የሆነው ኢኒዎስም ማንችስተር ዩናይትድን ለመግዛት ፍላጎት እንዳለው አሳውቋል።

ቢሊዮነሩ ራትክሊፍ ማንችስተር ዩናይትድን የመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ቀድመው አሳውቀው ነበር።

በ2005 (እአአ) ማንችስተር ዩናይትድን የገዙት የግሌዘር ቤተሰቦች “ስትራቴጅክ አማራጮችን መፈለግ” በሚል ክለቡን ለመሸጥ አስበዋል።

የኳታሩ ሼክ ጃሲም ክለቡን ወደ ቀድሞ ክብሩ የመመለስ ዕቅድ አለን በማለት ቡድኑን ቢገዙ ሊያደርጉ ያሰቡትን ገልጸዋል።

የእግር ኳስ ቡድኑን ማጠናከር፣ የልምምድ ማዕከሉን ማስፋት፣ ስታዲየሙን ማዘመን እና ሰፊ መሠረተ ልማትን ማሟላት የሼክ ጃሲም ‘ናይን ቱ ፋውንዴሽን’ ትኩረት ከመሆኑ በተጨማሪ ካለዕዳ በቀጥታ ክፍያ ቡድኑን ለመግዛት መታሰቡ ተነግሯል።

“የግዢ ጥያቄያችን ራዕይ የማንችስተር ዩናይትድን የእግር ኳስ ልዕልና ማሳደግ እና በዓለም ትልቁ የእግር ኳስ ቡድን ማድረግ ነው” ብለዋል።

ኢኒዎስ እስካሁን መግለጫ ባይሰጥም፣ ማንችስተር ተወልደው ያደጉት ራትክሊፍ ለክለቡ ባለቤትነት እንግሊዛዊ ተመራጭ ከመሆናቸውም በላይ “ማንችስተርን ወደ ማንችስተር ዩናይትድ የመመለስ ፍላጎት ይኖራቸዋል” የሚል ግንዛቤ አለ።

በ70 ዓመቱ እንግሊዛዊ የሚመራው ኢኒዎስ ግሩፕ በስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋእ የማፍሰስ ታሪክ ያለው ሲሆን፣ የፈረንሳዩን ኒቼ እና የስዊድኑን ሉዛን ክለቦች በባለቤትነት ያስተዳድራል።

በሌሎች የስፖርት ዘርፎች በመሳተፍም ውጤታማ እንደሆነም ይነገራል።

በሌላ በኩል የዕድሜ ዘመን የማንችስተር ዩናይትድ ደጋፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሼክ ጃሲም፣ ኳታር ውስጥ የሚገኘው ኪውአይቢ ባንክ ሊቀ መንበር ሲሆኑ፣ የቀድሞው የኳታር ጠቅላይ ሚንስትር ልጅም ናቸው።

ማንችስተር ዩናይትድን በምን ያክል ገንዘብ ለመገግዛት እንዳሰቡ ግን የታወቀ ነገር የለም።

ዩናይትድን ለመግዛት ከሳዑዲ አረቢያም ፍላጎት እንዳለ ይነገራል። ከዚህ በተጨማሪ ግን ከአሜሪካ በኩል ቢያንስ ሁለት ጥያቄዎች እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

ይህም ማለት ክለቡን ለመግዛት ቢያንስ አምስት ተፎካካሪዎች ይኖራሉ ማለት ነው። በሌላ በኩል የ20 ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ሻምፒዮና በመጠቅለሉ ሂደት ውስን ድርሻ ለመግዛት ጥያቄ ያቀረቡ ባለሃብቶችም አሉ ተብሏል።

ምንም እንኳ በቀጥታ ከክለቡ ጋር ተሳትፎ ባይኖራቸውም ከኳታር በኩል ለሚመጣው የግዢ ጥያቄ የፓሪስ ሴይንት-ዠርሜኑ ፕሬዝዳንት ናስር አል-ከላይፊ ቁልፍ ሰው እንደሚሆኑ ይታመናል።

በአል-ከላይፍ የሚመራው የኳታር ስፖርትስ ኢንቨስትመንት ተቋም ፕሪሚየር ሊጉ ውስጥ የተወሰነ ድርሻ የሚገዛበትን ሁኔታ እያፈላለገ ነው።

ቢሆንም ግን የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር የብዙ ክለቦች ባለቤት መሆንን ስለማይፈቅድላቸው በሌሎች ግለሰቦች ወይም በተለየ ድርጅት ስም ካልሆነ ራሳቸው መግዛት አይችሉም።

የኳታር በፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ማፍሷ እና በአውሮፓ ሁለት ትላልቅ ክለቦችን በባለቤነት መያዟ በአገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት እና የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ቡድኖችን አሰሳስቧል።