ኢትዮጵያ እና እንግሊዝን ጨምሮ በእግር ኳስ ዋንጫ ካነሱ አስርታትን ያስቆጠሩ 10 ሀገራት

በያዝነው ሳምንት የክለብ እግር ኳስ ጋብ ብሎ ብሔራዊ ቡድኖች የማጣሪያ እና የወዳጅነት ጨዋታ ወደ ማድረግ ተመልሰዋል።
በአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ግጥሚያ ሐሙስ ምሽት እንግሊዝ ከግሪክ ተጫውታ ድል ቀንቷታል። ቅዳሜ ደግሞ ውጤት የራቃቸው ዋሊያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከታንዛኒያ ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያ እና እንግሊዝ ዋንጫ ከበሉ ግማሽ ምዕተ ዓመትን አስቆጥረዋል። ደቡብ ኮሪያ እና ሞሮኮም እንዲሁ ዋንጫ ካዩ ብዙ ዓመታት ያስቆጠሩ አገራት ናቸው።
ባለፈው ዓመት በተደረገው የአውሮፓ ዋንጫ ለፍፃሜ ደርሳ የነበረችው እንግሊዝ የዘመናት የዋንጫ ጥሟን ትቆርጣለች ተብሎ ቢጠበቅም በስፔን ተሸንፋ የዋንጫ ሀሰሳዋን ለመቀጠል ተገዳለች።
ደቡብ ኮሪያ ዋንጫ ከበሉ በርካታ ዓመታት የሆነቸው አገራትን ትመራለች። እስኪ በእግር ኳሱ ሜዳ የዋንጫ ድርቀት ካጋጠማቸው አገራት መካከል አስሩን እንመልከት።
10. ኢራን - 48 ዓመታት
‘የኢራኑ ማራዶና’ በተባለ ቅፅል ስሙ የሚታወቀው አሊ ዳኢ በአውሮፓውያኑ ከ1993 እስከ 2006 ባለው ጊዜ በ148 ጨዋታዎች 108 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ነገር ግን ከሀገሩ ጋር ዋንጫ ማንሳት አልቻለም። ኢራን ጠንካራ ቡድን መገንባት ብትችልም ለ48 ዓመታት የቆየውን የዋንጫ ጥማቷን መቁረጥ ተስኗታል።
ኢራን ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫ ያነሳችው በአውሮፓውያኑ 1976 ነው። በእስያ ዋንጫ ከኩዌት ጋር የተገጠመችው ኢራን ዋንጫውን ያነሳችው በደጋፊዎቿ ፊት ነበር።
ኢራን በተከታታይ በዓለም ዋንጫ በእስያ ዋንጫ ውድድሮች ብትሳተፍም እነሆ ዋንጫ ካነሳች 48 ዓመታት አልፈዋታል።
9. ቼክ ሪፐብሊክ - 48 ዓመታት
ቼክ ሪፐብሊክ የአህጉሩን ዋንጫ ያነሳችው በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1976 ነው። በወቅቱ መጠሪያዋ ቼኮዝሎቫኪያ ነበር።
ማዕከላዊ አውሮፓዊቷ ሀገር ቼክ ሪፐብሊክ በተሰኘ መጠሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓ ዋንጫ የተሳተፈችው በ1996 ሲሆን፣ ይህ ከመሆኑ ከሦስት ዓመታት በፊት ነው ቼኮዝሎቫኪያ በሰላማዊ መንገድ የተበታተነችው።
ምንም እንኳ ቼክ ሪፐብሊክ የአውሮፓ ዋንጫ ተሳትፎ እጥረት ባይኖርባትም ዋንጫ ማንሳት ግን አልቻለም።
በአውሮፓ ዋንጫ ተፎካካሪ በመሆን ለፍፃሜ መድረስ ችላለች። ለሩብ ፍፃሜ እና ለግማሽ ፍፃሜም በቅታለች። የ1976 ድል ግን መድገም ተስኗታል።
8. ሞሮኮ - 48 ዓመታት

የፎቶው ባለመብት, CAF
ሞሮኮ በአውሮፓውያኑ 2022 ኳታር ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ እጅግ መነጋገሪያ ከሆኑ ሀገራት መካከል ናት። የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ለግማሽ ፍፃሜ ደርሶ በፈረንሳይ ቢረታም ለዚህ ክብር የበቃ የመጀመሪያው የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ነው።
ሞሮኮ የአፍሪካን ዋንጫን ካነሳች 48 ዓመታት አልፈዋል።
በዓለም ዋንጫ ከተሳተፉ የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ስኬታማ የምትባለው ሞሮኮ 6 ጊዜ ወደ ዓለም ዋንጫ መድረክ ሄዳለች። በዓለም ዋንጫ ታሪክ ከምድቧ ቀዳሚ ሆና ያለፈች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር ናት።
በአውሮፓውያኑ 1976 ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ከጊኒ ጋር ገጥማ በመርታት ዋንጫውን ማንሳት ችላለች።
ሞሮኮ ከዚህ ድሏ በኋላ በበርካታ የዋንጫ ውድድሮች ላይ ከመሳተፍ አልፎ ለዋንጫ ብትደርስም ዋንጫ ማንሳት ተስናቷል።
7. ፔሩ - 49 ዓመታት
የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ ሲነሳ ስማቸው የሚቀድመው ብራዚል፣ አርጀንቲና እና ኮሎምቢያ ናቸው። ብዙዎች የፔሩን የእግር ኳስ ታሪክ አያውቁት ይሆናል።
በአውሮፓውያኑ 1975 የመጀመሪያውን የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ያነሳችው ፔሩ ናት። ነገር ግን ከዚህ ዋንጫ በኋላ ከእግር ኳስ ዓለም ርቃ ቆይታለች።
ፔሩ በ2019 ለኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ፍፃሜ በቅታለች። በፍፃሜው ብራዚል ፔሩን 3-1 በመርታት ዋንጫውን አንስታለች። ፔሩ ለፍፃሜው መብቃቷ ምናልባትም እግር ኳሷ መነቃቃት እያሳየ እንደሆነ ማሳያ ነው ተብሏል።
6. ዲሞክራቲክ ኮንጎ - 50 ዓመታት
የዋንጫ ድርቀት ካለባቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪብሊክ ናት። ዲሞክራቲክ ኮንጎ በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ በአፍሪካ አሉ ከሚባሉ የእግር ኳስ አውራዎች መካከል ናት።
በወቅቱ ኮንጎ ኪንሻሳ በተባለ ስሟ ትጠራ የነበረችው ዲሞክራቲክ ኮንጎ በደርሶ መልስ ይደረግ በነበረው የፍፃሜ ጨዋታ ዛምቢያን በመርታት ነው ካይሮ የተዘጋጀውን ዋንጫ በአውሮፓውያኑ 1974 ማንሳት የቻለችው።
በፖለቲካዊ ውጥንቅጥ እና በምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ምክንያት እግር ኳሷ የቀጨጨው ዲሞክራቲክ ኮንጎ በ2023 የአፍሪካ ዋንጫ አራተኛ ሆና አጠናቃለች።
5. ሱዳን - 54 ዓመታት
በአንድ ወቅት አሉ ከሚባሉ የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል አንዷ የነበረችው ሱዳን የአህጉሪቱን ዋንጫ ያነሳችው በአውሮፓውያኑ 1970 ነበር።
ጋናን በመርታት ያዘጋጀችውን ዋንጫ ያነሳችው ሱዳን የመጀመሪያው እና የመጨረሻው ክብሯ ሆኖ ቀርቷል። ልክ እንደ ዲሞክራቲክ ኮንጎ በፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና በምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ምክንያት ነው የሱዳን እግር ኳስ ወደኋላ የቀረው።
ዋንጫ ካየች 54 ዓመታት ያለፏት ሱዳን በቅርቡ በወጣው የፊፋ የሀገራት ሰንጠረዥ ላይ 120ኛ ደረጃን ይዛለች።
4. እንግሊዝ - 58 ዓመታት

የፎቶው ባለመብት, Hulton Archive/Getty Images
ሦስቱ አናብስት ዋንጫ ካነሱ 60 ዓመታት ሊደፍኑ ተቃርበዋል። ለሁለት ተከታታይ ጊዜ ለአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ የደረሰችው እንግሊዝ ስኬት ከራቃት ቆይቷል።
በ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ ስፔንን ስትገጥም ምናልባት የዋንጫ ጥማቷን ትቆርጣለች ብለው ብዙቀዎች ቢጠብቁም ይህ ሳይሆን ቀርቷል።
እንግሊዝ ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫ ያነሳችው በአውሮፓውያኑ 1966 ነው። በወቅቱ ምዕራብ ጀርመንን 4-2 በመርታት ነበር የዓለም ዋንጫውን ያነሳችው።
ምንም እንኳ እንግሊዝ በዓለም ዋንጫውም ሆነ በአውሮፓ ውድድሮች የተሳትፎ እጥረት ባይኖርባትም ዋንጫ ለማንሳት ግን አሁንም በመጠባበቅ ላይ ናት።
3. እስራኤል - 60 ዓመታት
እስራኤል ዋንጫ ካነሱ በርካታ ዓመታትን ካስቆጠሩ ቀዳሚ ሦስት የዓለማችን ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1964 ሕንድ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ሆንግ ኮንግን በመርታት የእስያ ዋንጫን ማሸነፍ ችላለች። እስራኤል በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ውስጥ ታቅፋ ነው የምትጫወተው።
በአውሮፓ ዋንጫ እና በኔሽንስ ሊግ ማጣሪያዎች ላይ የምትጫወተው እስራኤል አሁንም እግር ኳስ ብዙ የሚቀረው ከሚባሉ ሀገራት መካከል ናት።
2. ኢትዮጵያ - 62 ዓመታት

የፎቶው ባለመብት, CAF
ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ማኅበር መሥራች ናት። የአህጉሪቱን የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካልን የመሠረቱት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ግብፅ እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው። ይድንቃቸው ተሰማ ከአውሮፓውያኑ 1972 - 87 ድረስ ካፍን መርተዋል።
ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የካፍ መሥራች ብትሆንም የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳችው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
ዋሊያዎቹ ትልቁን ዋንጫውን ያነሱት በአውሮፓውያኑ 1962 ነበር። ሉቺያኖ ቫሳሎ እና መንግሥቱ ወርቁ ባስቆጠሯቸው የተጨማሪ ደቂቃ ግቦች ነው ኢትዮጵያ ግብፅን በመርታት የመጀመሪያውን እና የመጨረሻውን ዋንጫዋን ያነሳችው። በወቅቱ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ይድነቃቸው ተሰማ ነበሩ።
በ1957 የአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ ተሳታፊ የነበሩት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ነበሩ።
ዋልያዎቹ ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ከምድባቸው ማለፍ የቻሉት በ1968 ነው። በዚህ ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው ውድድር አራተኛ ሆና ማጠናቀቋ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2013 የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፋለች። ነገር ግን ከምድቧ ማለፍ አልቻለችም። ዋሊያዎቹ በ2022 ካሜሩን ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍ ቢችሉም ከምድባቸው ሳያልፉ ተመልሰዋል።
1. ደቡብ ኮሪያ - 64 ዓመታት
የቶተንሀሙ ሂዩንግ-ሚን ሶን የእስያ ምርጡ እግር ኳስ ተጫዋች ተብሎ በመሸለም የሚደርሰው የለም። ስድስት ጊዜ የእስያ ምርጡ የተባለው ሶን ሀገሩ ከምንም በላይ የምትፈልገውን ድል ሊያጎናፅፋት ግን አልቻለም።
ደቡብ ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ የእስያ ዋንጫን ያነሳችው በአውሮፓውያኑ 1960 ነበር። ከዚህ ጊዜ በኋላ 4 ጊዜ ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። በርካታ ጊዜ ደግሞ ሦስተኛ ሆና ጨርሳለች።
ምናልባት ደቡብ ኮሪያ ከእንግሊዝ በበለጠ ዕደለ ቢስ ሳትሆን አትቀርም ቢባል ማጋነን አይሆንም።












