የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች በሜክሲኮ ማረሚያ ቤት ላይ ተኩስ ከፍተው አስረኞች አስመለጡ

ጥቃቱ በተፈጸመበት ማረሚያ ቤት ወዳጅ ዘመድ ያላቸው ሰዎች ሲላቀሱ ታይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጥቃቱ በተፈጸመበት ማረሚያ ቤት ወዳጅ ዘመድ ያላቸው ሰዎች ሲላቀሱ ታይተዋል።

የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን አባላት ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በሰሜን ሜክሲኮ በሚገኝ ማረሚያ ቤት ላይ ጥቃት ሰንዝረው በርካታ እስረኞችን አስመለጡ።

ታጣቂዎች ቺሁዋቺሁዋ ወደተባለው ማረሚያ ቤት ንጋት ላይ በብረት ለበስ ተሸካርካሪዎች ከመጡ በኋላ በእስር ቤቱ ጥበቃዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

በዚህ ጥቃት 10 ጥበቆች እና 4 እስረኞች መሞታቸው ተዘግቧል።

ፖሊስ እንዳለው ከሆነ ታጣቂዎቹ ወደ 24 እስረኞችን አስመልጠዋል።

በዚህ ማረሚያ ቤት ውስጥ የዕጽ ዝውውርን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀለኞች ጥፋተኛ ተብለው የታሰሩ እስረኞች ይገኙበታል።

አንዲት የዓይን እማኝ ጥቁር የለበሱት ታጣቂዎች ከፖሊስ የበለጠ በኃይል የታጣቁ ነበሩ ብላለች።

የጥቃቱን መፈጸም ተከትሎ የአገሪቱ ጦር እና ብሔራዊ ዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ በአካባቢው ባለሥልጣናት ጥሪ ቀርቦለት ነበር።

ጥቃቱ የተፈጸመባት ኪዩዳድ ሁዋሬዝ ከተማ ባለፉት አስርት ዓመታት ሲናሎዋ እና ጁአሬዝ በተባሉ ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

ጥቃት የተከፈተበት ማረሚያ ቤት ከዚህ ቀደምም እስረኞች ያስነሱት አመጽ ከእስር ቤት ውጪ አልፎ ለ11 ሰዎች ሕይወት ህልፈት ምክንያት ሆኖ ነበር።

እነዚህ በማረሚያ ቤቶች ላይ ያሚያገጥሙት ክስተቶች ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድኖች ያላቸው ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑን ነው።

የከተማዋ ዐቃቤ ሕግ ከአሜሪካዋ ኤል ፓሶ አቅራቢያ በምትገኘው ከተማ ማረሚያ ቤት ላይ የተከሰተው እንደሚመረምሩ ቃል ገብተዋል።

ታጣቂዎቹ በፀጥታ ኃይል አባላት ላይ ተኩስ ከፍተው እስረኞችን ካስለቀቁ በኋላ ፖሊስ ዕጽ አዘዋዋሪዎቹን በመኪና አሳዶ 4 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል።

ፖሊስ በከተማ ዙሪያ በተደገረ የተኩስ ልውውጥ ደግሞ ሁለት አሸከርካሪዎች መገደላቸውን የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ ክስተት በማረሚያ ቤቱ ላይ ከተከፈተው ጥቃት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።