ዩክሬን በአስችኳይ የአውሮፓ ሕብረት ዕጩ አባል እንድትሆን ድጋፍ አገኘች

የአውሮፓ አገራት መሪዎች ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ጋር

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የአውሮፓ አገራት መሪዎች ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ጋር

የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያ እና የሩሜኒያ መሪዎች ዩክሬን የአውሮፓ ሕብረት አባል እንድትሆን የተዘጋጀውን ረቂቅ የደገፉት ሲሆን “በአስቸኳይ” የሕበረቱ ዕጩ አባል መሆን አለባትም ብለዋል።

በኪዬቭ በተደረገው የጋራ ስብሰባ ላይ የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ “ዩክሬን የአውሮፓ ቤተሰብ መሆን ይገባታል” ብለዋል።

ሆኖም አሁንም ዩክሬን ማሟላት የሚጠበቅባት መስፈርቶችን አላሟላችም ብለዋል።

በሌላ በኩል የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን 27ቱ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ዩክሬን ሩሲያ ላይ ድል እስክትቀዳጅ ድርስ ከጎኗ ልንቆም ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የሩሲያ በአውሮፓ አንድነት ላይ ጦርነት አውጃለች ያሉ ሲሆን፣ እጅግ ውጤታማው መሳሪያም አንድነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዩክሬን ራሷን እንድትከላከል እና በሞስኮ የተያዙባትን ቦታዎች ለማስመለስ በአስቸኳይ ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎች እንዲቀርቡላት ተማጽነዋል።

ትላንትና አራት የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች ከኪዬቭ አቅራቢያ የምትገኘውን እና በሩሲያ ቁጥጥር ስር የነበረቸውን ኢርፒን የተሰኘችውን ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባትን ከተማ ጎብኝተዋል።

በዚህችም ከተማም ይሁን በአቅራቢያዋ ባለችው ቡቻ በተባለችው ከተማ የሩሲያ ወታደሮች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ስትል ዩክሬን ትከሳለች። ሆኖም ሞስኮ ይህንን ክስ ታስተባብላለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች ኪዬቭን በሚጎበኙበት ወቅት የሩሲያ ወታደሮች በምሥራቅ ዩክሬን በምትገኘውን ሴቬርዶንስቲክ ከተማ ላይ ጥቃት መፈጻማቸውን ቀጥለዋል።

ሴቬርዶንስቲክ እና ሊሲሼንክ ከተሞች መቆጣጠር ለሳምንታት የሩሲያ ቀዳሚ ወታደራዊ ግብ ሆኖ የቆየ ሲሆን ሞስኮ ሉሃንሳክ የተባለውን ክልለ ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ፍላጎቷ አካል ነው ተብሏል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ማክሮን፣ የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ሾልዝ፣ የጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪዮ ድራጊ እና የሩሜኒያው ፕሬዝዳንት ክሉስ ለሆኒስ በጋራ ኪዬቭን የጎበኙ ሲሆን፣ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ አገሪቱን ሲጎበኙ ይህ የመጀመሪያ ነው ተብሏል።

መሪዎቹ ኪዬቭን ከመጎብኘታቸው አንድ ቀን ቀድም ብሎ የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ዩክሬንን በዕጩነት ደረጃ የሕበረቱ አባል እንደትሆን ምክረ ሃሳብ አቅርቦ ነበር።

በሚቀጥለው ሳምንት 27ቱ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት እንደሚገናኙ ይጠበቃል።

የተወሰኑ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ዩክሬን አባል እንድትሆን ፍላጎታችው እምብዛም ነው ሲሆን፣ በሕብረቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣሊያን ቀስ በቅስ አቋማቸውን ሊቀይሩ እንደሚችል ይታመናል።

ሆኖም በዕጩነት ደረጃ ተቀባይነት ማግኘት ዓመታትን ሊፈጅ ለሚችለው ሙሉ አባልነት የሚረዳ እርምጃ እንጂ ከዚያ የዘለለ ጥቅም አይኖረውም።

የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች ኪዬቭን ከመጎብኘታቸው በፊት የዩክሬን ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣሊያን በፍጥነት መሳሪያ አላቀረቡልንም በሚል ሲወቀሱ ቆይተዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ፕሬዝዳንት ማክሮን ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯ ልናዋርዳት አይገባም ሲሉ ተደምጠዋል። ፕሬዝዳንት ፑቲን ለፈጸሙት “መሰረታዊ ስህተት” መውጫ ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።