ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕንድ በጸሐይ ላይ የምታደርገውን ታሪካዊ ተልዕኮ በስኬት ጀመረች
ታሪካዊ በተባለ የጨረቃ ተልዕኮ በጨረቃ ደቡብ ዋልታ በማረፍ የመጀመሪያዋ አገር የሆነችው ሕንድ በጸሃይ ላይ የምታደርገውን ታሪካዊ ተልዕኮ በስኬት ጀመረች።
አድትያ- ኤል 1 የተሰኘችው መንኮራኩር ቅዳሜ ነሐሴ 27/ 2015 ዓ.ም በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር 11፡50 ላይ ከስሪሃሪኮታ ጣቢያ ተነስታለች።
ከምድርም በ1.5 ሚሊዮን ኪሎሜትር ርቀት ላይ ታንዣብባለች ተብሏል።
የሕንድ የጠፈር ኤጀንሲ መንኮራኩሯ ይህንን ርቀት ለመጓዝ አራት ወራት እንዲሚፈጅባትም ነው ያሳወቀው።
ሕንድ በፀሐይ ላይ የምታደርገውን ተልዕኮ የሰየመችው በሱሪያ ስም ነው።
ሱሪያ (አዲትያ) የሂንዱ የፀሐይ አማልክት ናት።
ኤል 1 የሚባለው ደግሞ መንኮራኩሯ በፀሐይ እና በምድር መካከል የምትቀመጥበት ትክክለኛውን ስፍራ የሚያሳየው ላግራንጅ ፖይንት የተሰኘው መለኪያ ነው።
ቅዳሜ ማለዳ የህንድ የጠፈር ምርምር ኤጀንሲ ባዘጋጀው የመመልከቻ ስፍራ ላይም በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መንኮራኩሯ ስትነሳ ተከታትለዋል።
በአገሪቱም ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያም በቀጥታ ተላልፏል። ሳይንቲስቶች የመንኮራኩሯ መነሳት የተሳካ እንደነበር አንደነበር መግለጻቸውንም ኤጀንሲው አስታውቋል።
መንኮራኩሯ ለአንድ ሰዓት ከአራት ደቂቃ ከተጓዘች በኋላ ኢስሮ “ተልእኮው ስኬታማ ሆኗል” ብሏል።
“መንኮራኩሯ ለ135 ቀናትም ያህል ረጅም ጉዞዋን ትቀጥላለች። መልካም እድል እንመኝላታለን” ሲሉም የኤጀንሲው ኃላፊ ስሬድራ ፖኒከር ሶማናት ተናግረዋል።
እንደ አውሮፓ የጠፈር ኤጀንሲ ገለጻ ላግራንጅ ፖይንት የሚሰኘው እንደ ፀሐይ እና ምድር ያሉ ትላልቅ ፕላኔቶች ያላቸው የስበት ሃይል እርስ በርስ የሚጠፋፋበት ስፍራ ነው።
ይህም ማለት መንኮራኩሮች በዚህ ስፍራ መንሳፈፍ እንዲሁም ማንዣበብ ያስችላቸዋል።
አዲትያ ኤል1 መንኮራኩር በዚህ ስፍራ ላይ ከደረሰች በኋላ ከምድር ጋር በተመሳሳይ ፍጥነት ፀሐይን መዞር ትችላለች።
የሚያስፈልጋትም ነዳጅ አነስተኛም ነው ተብሏል።
የሕንድ የጠፈር ምርምር ኤጀንሲ (ኢስሮ) እንደገለጸው መንኮራኩሯ ወደ ኤል 1 ከመውጣቷ በፊት በርካታ ጊዜ በምድር ዛቢያ ላይ እንድትሽከረከር ትደረጋለች ።
ኤል 1 ላይ ከደረሰች በኋላም ያለማቋረጥ ፀሐይን መከታተል ትችላለች። ግርዶሽ በሚያጋጥመበትም ወቅት የማይቋረጥ ሲሆን በዚህም ሳይንሳዊ ጥናቶችን ታካሂዳለች።
ኢስሮ ለዚህ ተልዕኮ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስወጣ ባይገልጽም የሕንድ ሚዲያዎች ግን 3.78 ቢሊዮን ሩፒ ወይም 46 ሚሊዮን ፓውንድ እንደፈጀ ዘግበዋል።